ታዋቂው ራፐር ኤሚነም የሪፐብሊካኑ ፖለቲከኛ ዘፈኖቹን መዝፈን እንዲያቆሙ አሳሰበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታዋቂው ራፐር ኤሚኒም የሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዚዳንት እጩ ለመሆን እየተወዳደሩ ያሉትን ቪኬክ ራማስዋሚ ዘፈኖቹን መዝፈን እንዲያቆሙ አሳሰበ።
ራፐሩ የማሳሰቢያውንም ደብዳቤ በጠበቆቹ በኩል ለፖለቲከኛው እንዲደርስ አድርጓል።
በባዮቴክ ዘርፍ የስራ ፈጣሪ የሆኑት እና ፖለቲከኛው ቪቬክ በአዮዋ ግዛት በአንድ የንግድ መድረክ ላይ ‘ሉዝ ዩር ሰልፍ’ የተሰኘውን የራፐሩን ዘፈን ተጫውተዋል።
ከሳምንት በፊት የተጻፈው ደብዳቤ የተላከመው በኤሚነም የሙዚቃ ማሳተሚያ ኩባንያ ቢኤምአይ አማካኝነት ነው።
ቪቬክ አሜሪካ በመጪው ዓመት በምታደርገው ምርጫ የሪፐብሊካን እጩ ለመሆን ሌላኛው ተወዳዳሪ የሆኑትን ዶናልድ ትራምፕን እየተገደዳደሩ ይገኛሉ።
የፖለቲከኛው ቃለ አቀባይ የኤሚነም ወይም በትክክለኛ ስሙ ማርሻል ማተርስ የቀረበውን ጥያቄ እንደሚያከብሩ ተናግረዋል።
ከራፐሩ ኩባንያ የተላከው ደብዳቤ የሪፐብሊካኑ ፖለቲከኛ ማንኛውንም የኤሚነም ሙዚቃዎች በመድረኮች ላይ እንዳይዘፍኑም የሚያሳስብ ነው።
“ቪቬክ በ2024 በሚያደርጉት የምረጡኝ ቅስቀሳ ማንኛውንም የኤሚነም ሙዚቃዎች ቢያቀርቡ ቢኤምአይ እንደ ጥሰት ይመለከተዋል” ሲልም ያትታል።
የዘመቻው ቃለ አቀባይ ትሪሻ ማክላውሊን በበኩላቸው የኤሚነምን ግጥም በመጥቀስ ለአሜሪካ ሚዲያ መግለጫ ሰጥተዋል።
“የራፕ ሙዚቃውን ለኤሚነም ወይም ለሪል ስሊም ሼዲ[መጠሪያው በሆነው ታዋቂው ሙዚቃው] እንተውለታለን” በማለትም ተናግረዋል።
ፖለቲከኛውም ነገሩን ቀለል አድርገው ቀድሞ ትዊተር ተብሎ በሚጠራው ኤክስ ገጻቸው ላይ ‘ዘ ሪል ስሊም ሼዲ’ ብለው በመጥራትም ‘ ምን እንዳረግኩኝ አልተናገረም፤ ወይስ ተናግሯል’ በሚልም አስፍረዋል።
በፖለቲካው መድረክ ላይ ብቅ ያሉት አዲሱ ፖለቲከኛ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የሪፐብሊካን ክርክር ላይ ጠንከር ያለ ሃሳብ ማቅረባቸውን ተከትሎ እንደ ኮከብም እየታዩ ነው።
እሳቸውም ቢሆን ራሳቸውን ለፖለቲካው መድረክ አዲስ አድርገው የሚያቀርቡ ሲሆን የቀድሞውን የፕሬዚዳንት ትራምፕ ቅድሚያ ለአሜሪካ መስጠት (አሜሪካ ፈርስት) የሚለው ጽንሰ ሃሳባቸውን ለመገንባት ሃሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ፖለቲከኛች በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ሙዚቃችንን አትጠቀሙ የሚሉ ማሳሰቢያዎች አዲስ አይደሉም።
ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ዘመቻ እና ፐሬዚዳንታዊ ዝግጅቶቻቸው ላይ ሙዚቃችንን አትጠቀሙ የሚሉ በርካታ ደብዳቤዎች የደረሳቸው ሲሆን ከነዚህም ሮሊንግ ስቶን ባንድ፣ ኩዊን፣ አደሌ እና ፋረል ዊልያምስ ተጠቃሽ ናቸው።












