በፕሪሚየር ሊጉ እና በኤፍኤ ዋንጫ የሚደረጉ ወሳኝ ጨዋታዎችን ማን ድል ያደርጋል?

ታትሟል

የሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ወሳኝ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና የኤፍኤ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎችን ያስተናግዳሉ።

በኤፍኤ ዋንጫ የወቅቱ አሸናፊ ሲቲ ከ ቼልሲ ይገናኛል። የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ተፎካካሪዎቹ አርሰናል እና ሊቨርፑል ከሜዳቸው ውጪ ተጋጣሚዎቻቸውን ይገጥማሉ።

የቢቢሲ የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን የጨዋታ ግምቱን እንደሚከተለው ሰጥቷል።

ሉተን ከ ብሬንትፈርድ

ይህ ጨዋታ ላለመውረድ ለሚታገው ሉተን ትልቅ ትርጉም ያለው ጨዋታ ነው። ለነገሩ ለብሬንትፈርድም ቢሆን ወሳኝ ጨዋታ ነው።

ሉተን ይህን ጨዋታ ካሸነፈ እራሱን ከወራጅ ቀጠና አውጥቶ ብሬንትፈርድ ላይ የመውረድ አደጋን ይደቅናል። ምናልባት ንቦቹ አንድ ተጨማሪ ጨዋታ የሚያሸንፉ ከሆነ ስጋቱ ይቀልላቸው ይሆናል።

ሉተን የተቻላቸውን ሁሉ አድርገው ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዘው ይወጣሉ የሚል ግምት አለኝ።

ግምት፡ ሉተን 1 - 1 ብሬንትፎርድ

ሼፊልድ ዩናይትድ ከ በርንሌይ

እነዚህ ሁለት ክለቦች በቅርብ ሳምንታት እራሳቸው ላይ ችግር ሲፈጥሩ ቆይተዋል።

የበርንሌይ ግብ ጠባቂ የሠራው ከባድ ስህተት ቡድኑን ሦስት ነጥብ አሳጥቶታል።

በዚህ ጨዋታ በርንሌይ የሚያሸንፍ ይመስለኛል።

በውድድር ዘመኑ ጅማሬ ላይ በርንሌይ ሜዳ ተርፍ ሞር ላይ ሼፊልድን 5 ለ 0 ማሸነፍ ችለው ነበር።

ከሊጉ መውረዳቸው የማይቀርላቸው የሚመስሉት ሼፊልዶች ብዙ ቢጥሩም ከዚህ ጨዋታ ምንም ነጥብ አያገኙም።

ግምት፡ ሼፊልድ 1 - 2 በርንሌይ

ማንቸስተር ሲቲ ከ ቼልሲ

በቅርብ ዓመታት ሲቲ በዝውውር መስኮቶች ስህተት ሲሠራ ተመልክቼ አላውቅም ነበር። ጋርዲዮላ ኮል ፓልመርን ለቼልሲ መሸጣቸው ግን ስህተት እንደሆነ አስባለሁ።

ጋርዲዮላ በዚህ ጨዋታ ለሠራው ስህተት ቅጣቱን ይቀበል ይሆናል።

ሲቲ ከቻምፒየንስ ሊጉ ተሸንፎ መውጣት አልነበረበትም። በዚያ ውድድር ያጡትን በኤፍኤ ዋንጫ ያካክሳሉ ብዬ አስባለሁ።

ጋርዲዮላ ኤፍኤ ዋንጫን ከዚህ ቀደም ቢያነሳም ለዋንጫ ካለው ፍቅር የተነሳ ዋንጫውን ዳግም የማንሳት ትልቅ ፍላጎት ይኖረዋል።

ምንም እንኳ የቼልሲ የዘንድሮ አቋም አስተማማኝ ባይሆንም ለሲቲ በቀላሉ እጅ አይሰጥም። ሁለት ጊዜ ከሲቲ ጋር አቻ ተለያይቷል።

በዚህ ጨዋታ ግን ድሉ ያለጥርጥር የሲቲ ይሆናል።

ግምት፡ ሲቲ 3 - 0 ቼልሲ

ዎልቭስ ከ አርሰናል

ይህ ለአርሰናል ትልቅ ጨዋታ ነው። በተከታታይ ሁለት ሸንፈትን ያስተናገደው ቡድን በዚህ ጨዋታ ለሦስተኛ ጊዜ ከተሸነፈ ከዋንጫ ፉክክሩ የመውጣቱ ነገር አይቀሬ ይሆናል።

አንዳንዶች መድፈኞቹ አቅማቸው ተዳክሟል ቢሉም እኔ ግን በዚህ አልስማማም። ከቪላ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ቅርጻቸው ተበለሻሽቶ ነበር።

ይህ ችግር ከዎልቭስ በሚኖራቸው ጨዋታ ይደገማል ብዬ አላስብም።

ግምት፡ ዎልቭስ 0 - 1 አርሰናል

ኤቨርተን ከ ኖቲንግሃም ፎረስት

ይህ ጨዋታ ላለመውረድ የሚደረግ ተጋድሎ ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። ጨዋታውን ማን ሊረታ እንደሚችል መገመትም ቀላል አይሆንም።

ኤቨርተን ከቼልሲ ጋር በነበረው ጨዋታ አቻ ይለያያል ብዬ ገምቼ በብዙ የግብ ልዩነት ተሸንፏል።

ይህ ጨዋታ ግን ሾን ዳይሽ ያን አሳፋሪ ሽንፈት የሚወጡበት ዕድል ሆኖላቸው ነው የምመለከተው።

ካላፉት 9 ጨዋታዎች 1 ጨዋታ ብቻ ያሸነፉት ፎረስት ከዚህ ጨዋታ ምንም ነጥብ አያገኙም።

ግምት፡ ኤቨርተን 2 - 1 ፎረስት

አስተን ቪላ ቦርንመዝ

አስተን ቪላ አራተኛ ደረጃን ይዞ ለመጨረስ ከቶተነሃም ጋር ትግል ውስጥ ይገኛል።

የኡናይ ኤምሪ ቡድን ይህን ጨዋታ አሸንፎ አራተኛ ደረጃን የሚያረጋግጥበት ዕድሉን እንደሚጠብቅ አምናለሁ።

ግምት፡ ቪላ 2 - 1 ቦርንመዝ

ክሪስታል ፓላስ ከ ዌስት ሃም

ፓላስ ሊቨርፑልን ያሸንፋል ብሎ ማን ጠብቆ ነበር?

ኤዜ እና ኦሊሴ ወደ ሜዳ ሲመለሱ ፓላስ አስደናቂ አቋም ያሳያል። የሁለቱ ጥምረት ፓላስን ለድል ያበቃል ብዬ አስባለሁ።

በቀጣይ ዓመት በአውሮፓ መድረክ የመጫወት ዕድል ያላው ዌስት ሃም በቀላሉ እጅ የሚሰጥ አይሆንም።

ግምት፡ ፓላስ 2 - 1 ዌስት ሃም

ኮቫንተሪ ከ ማንቸስተር ዩናይትድ

ብዙዎች ላይስማሙ ይችላሉ ነገር ግን ይህን ጨዋታ ኮቫንተሪ ያሸንፋል።

ዩናይትድ ይሸነፋል ብዬ ግምት ብሰጠሁ ቁጥር የዩናይትድ ደጋፈዎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየወጡ ብስጭታቸውን ይገልጻሉ።

በቻምፒየንሽፑ ካለፉት 4 ጨዋታዎች በሦስቱ ቢሸነፉም ኮቫንተሪ ይህን ጨዋታ የሚያሸንፍ ይመስለኛል። ግን በውድድር ዓመቱ በሙሉ ወጥ አቋም የሌላው ዩናይትድ ይህን ጨዋታ ያሸንፋል ብዬ አላስብም።

ግምት፡ ኮቫንተሪ 2 - 1 ዩናይትድ

ፉልሃም ከ ሊቨርፑል

እነዚህ ሁለት ቡድኖች በዚህ የውድድር ዓመት ሦስት ጊዜ ተገናኝተዋል። ሦስቱንም ጊዜ በጠባብ ውጤት ነው የተጠናቀቀው። በዚህ ጨዋታም የምጠብቀው ይህንኑ ነው።

ሊቨርፑል ሁለት ጊዜ በጠባብ ውጤት በሜዳው አሸንፏል። በፉልሃም ሜዳ በተደረገ የካራባዎ ዋንጫ ጨዋታ 1 ለ 1 ተለያይተው ነበር።

ይህ ጨዋታ ለየርገን ክሎፕ ቡድን የግድ ማሸነፍ ቢሆንም ጨዋታው አቻ የሚያልቅ ይመስለኛል።

ግምት፡ ፉልሃም 1 - 1 ሊቨርፑል