ቢቢሲ ወጪ ለመቆጠብ ሲል ለውጦችን ለማድረግ ማቀዱን አስታወቀ

ቢቢሲ ሰቱዲዮ
የምስሉ መግለጫ,  የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት በአማካይ በሳምንት 148 ሚሊየን ሰዎችን ይደርሳል።
ታትሟል

ቢቢሲ ለዓለም አቀፍ አገልግሎቱ በዓመት 28.5 ሚሊየን ፓውንድ ለመቆጠብ ሲል 382 ሠራተኞቹን ለመቀነስ ማቀዱን አስታወቀ።

በአረብኛ ፣ በፐርሺያ፣ በቻይና፣ በቤንጋሊ የሚያሰራጫቸውን የራዲዮ ፕሮግራሞችን ጨምሮ በአስር ቋንቋዎች የሚያሰራጫቸውን የራዲዮ ፕሮግራሞቹ እንደሚቋርጡም ተገልጿል።

ምንም እንኳን የሚዘጋ የቋንቋ አገልግሎት ባይኖርም ወደ ታዳሚው ያለውን ተደራሽነት ለመጨመር አብዛኞቹ አገልግሎቶች ወደ በይነ መረብ (ኦንላይን) ይሸጋገራሉ ተብሏል።

ከዚህም ባሻገር በቢቢሲ እና ቢቢሲ ፎር ወደ ኦንላይን በማሸጋገር በዓመት 500 ሚሊየን ፓውንድ እየቆጠበ እንደሆነም አስታውቋል።

ባለፈው ዓመት ጥር ላይ የቀድሞ የባህል ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናዲን ዶሪስ፣ ቢቢሲ ከፈቃድ ከሚሰበሰብ ክፍያ የሚያገኘው ገንዘብ ለሁለት ዓመት ያህል 159 ፓውንድ እንደሚሆን አስታውቀው ነበር።

ይህም ካለው የዋጋ ግሽበት እና የዋጋ ንረት ጋር ተደማምሮ ወደ ከባድ ምርጫ ውስጥ እንዳስገባው ኮርፖሬሽኑ ገልጿል።

ጨምሮም እቅዱ “ዘመናዊ፣ ዲጂታል መር እና የቀጥታ ሥርጭት” ፕሮግራሞቹን ለመፍጠር ያለውን ስትራቴጂ ይደግፋል ብሏል።

በዕቅዱ መሠረት ኪርኪዝ፣ ኡዝቤክ፣ ሂንዲ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ታሚል እና ኡርዱ የራዲዮ ፕሮግራሞቹ ይዘጋሉ።

ቻይንኛ፣ ጉጃራት፣ ኢግቦ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ፒጂን፣ ኡርዱ እና ዮሩባ ደግሞ ወደ ኦንላይን ይዛወራሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙኃን ተቋም - ቢቢሲ፣ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሲሆን በበርካታ የዓለም ቋንቋዎች እና ቀጠናዊ አገልግሎቶቹን በራዲዮ፣ በቴሌቪዥን እና በዲጂታል ያቀርባል።

ቢቢሲ በአሁኑ ወቅት በሳምንት ወደ 364 ሚሊየን ሰዎችን ይደርሳል። ከእነዚህ መካከል ግማሽ ያህሉ አገልግሎቱን የሚያገኙት በኦንላይን ነው።

ይፋ ባደረገው ዕቅዱ የሚዘጋ አገልግሎት ባይኖርም፣ ዓለም አቀፍ አገልግሎት አሁንም በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ለተከታታዮቹ ፕሮግራሞቹን እያቀረበ ሲሆን በሩሲያ፣ በዩክሬን እና በአፍጋኒስታን ያሉ ተከታታዮቹ አሁንም የቢቢሲ የዜና አገልግሎትን መጠቀም እንደሚችሉ አረጋግጧል።

ዓለም አቀፉ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አገልግሎት አሁንም ዜናዎቹን ማቅረቡን የሚቀጥል ሲሆን፣ በሁሉም የዓለም ክፍሎች ሥርጭቱን ይቀጥላል።

ከዚህም በተጨማሪ ኮርፖሬሽኑ አዲስ መርሃ ግብሮቹን እና ፖድካስቶቹን አስታውቃለሁ ብሏል።

የቢቢሲ የዓለም አቀፉ አገልግሎት ዳሬክተር ሊሊያን ላንደር፣ “የቢቢሲ ሚና ቀላል አይደለም። ቢቢሲ በተለይ ደግሞ ብዙ የሚዲያ አማራጭ በሌለባቸው አካባቢዎች ሚዛናዊ እና ገለልተኛ በሆኑ ዜናዎቹ በመቶ ሚሊዮኖች ሰዎች ዘንድ ይታመናል” ብለዋል።

“በቀውስ ወቅት ሰዎችን ረድተናል። አሁንም ለአድማጮች ምርጥ የጋዜጠኝነትን ውጤቶችን ለማቅረብ በእንግሊዝኛ እና ከ40 በላይ ቋንቋዎች አገልግሎቱን ይቀጥላል። ከዚህም በተጨማሪ ዘገባዎቻችንን የበለጠ በማጠናከር በሙያው የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ማሳደጉን ይቀጥላል።”

ዳሬክተሯ አክለውም የዲጂታል አገልግሎቱን ለማስፋት አሳማኝ ምክንያቶች እንደነበሩም አስታውሰዋል።

ዓለም አቀፉ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አገልግሎት፣ በካርዲፍ ከሚገኘውና የአንድ ሰዓት ቆይታ ካለው ቢቢሲ ኒውስ ሳይንስ እንዲሁም የቀጥታ ዜና አገልግሎት እና የስፖርት ፕሮግራሞቹ በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ ላሉ ወጣት አድማጮቹ አዲስ የፖድካስት ፕሮግራም ያቀርባል።

ሌሎች እቅዶቹስ ምንን ያካትታል?

  • የተወሰኑ ፕሮዳክሽኖችን ከለንደን በማስወጣት ለአድማጮቹ ቅርብ ወደ ሆኑ ቦታዎች ማዛወር። ለምሳሌ የታይላንድ አገልግሎትን ከለንደን ወደ ባንኮግ፣ የኮሪያን አገልግሎትን ወደ ሴኡል፣ የባንግላዴሽ አገልግሎት ወደ ዳካ እና ፎከስ ኦን አፍሪካ የቴሌቪዥን ዜና አገልግሎት ወደ ናይሮቢ ይዛወራሉ።
  • የምርመራ እና የዘጋቢ ፕሮግራሞቹ ብዙ እንዲራመዱ ማስቻል።
  • ተቀማጭነቱን በለንደን ያደረገ አዲስ የቻይና ክፍል መፍጠር
  • ያልተነገሩ፣ የተለዩ፣ ለዲጂታል የተሰሩ ተፅእኖ ፈጣሪ አፍሪካዊ ይዘት ያላቸው ፕሮግራሞች ክፍል መፍጠር
  • በአረብኛ እና በፐርሺያን ቋንቋዎች የቴሌቪዥን ሥርጭቶች መቀጠል ከዚህም በተጨማሪ በሁለቱ ቋንቋዎች የነበረውን የራዲዮ ፕሮግራም ለመተካት የኦዲዮ እና ሌሎች ዲጂታል አቅምን መገንባት

እነዚህ እቅዶች ግን ከሠራተኞቹ እና ከሠራተኞች ማኅበሩ ጋር ለመመካከር ክፍት መሆኑን ቢቢሲ ገልጿል።

የብሮድካስቲንግ ማኅበር ኃላፊ ፊሊፓ ቻይልድስ፣ የታቀዱትን ለውጦች በማየታቸው ቅር መሰኘታቸውን ተናግረዋል።

ኃፊዋ አክለውም  “ቢቢሲ በለውጥ የሚዲያ ገጽታ ላይ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች ለመወጣት መላመድ እንዳለበት የምንገነዘበው ቢሆንም፣ አሁንም በመንግሥት ደካማ ውሳኔ የሚጎዱት ሠራተኞቹ ናቸው። የፍቃድ ክፍያውን ማቆሙ እና ያስከተለው የገንዘብ ድጋፍ ችግሮች እነዚህን ሀሳቦች ለማምጣት አስገድዶታል” ብለዋል።