የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ሳይጠበቁ ኬንያ ገቡ

ሰርጌይ ላቭሮቭ በናይሮቢ

የፎቶው ባለመብት, MFA Russia/Twitter

የምስሉ መግለጫ, ሰርጌይ ላቭሮቭ በናይሮቢ
ታትሟል

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ቀድሞ ይፋ ባልተደረገ ጉብኝት ኬንያ ገብተዋል።

የሞስኮ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሚኒስትሩን ሰኞ ንጋት ላይ ናይሮቢ መግባት ይፋ ያደረገ ቢሆንም ለምን እንደመጡ ግን ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጠም።

በናይሮቢ የሩሲያ ኤምባሲ በትዊተር ገጹ “ፍሬያማ የሁለትዯች ግንኙነት ለሩሲያና ኬንያ” የሚል መልዕክት አስፍሯል።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ዛሬ ሰኞ የናይጄሪያው አዲሱ ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ በዓለ ሲመት ጉዟቸውን በላቭሮቭ ጉብኝት ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፣ ሰርዘዋል።

ላቭሮቭ ወደ ኬንያ የመጡት የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲመትሪ ኩሌባ አዲስ አበባን ጨምሮ በአፍሪካ አገራት ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።

ላቭሮቭ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ወደ አፍሪካ ሲመጡ ይህ የመጀመርያቸው አይደለም።

በፈረንጆች በሐምሌ ወር 2022፣ ግብጽን የጎበኙት ላቭሮቭ ወደ ኮንጎ ብራዛቪል አቅንተው ከዚያ ኢትዮጵያን እና ኡጋንዳን ጎብኝተው ነበር።

በጥር ወር 2023 ዓ/ም ደግሞ ኤርትራን መጎብኘታቸውና ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር መምከራቸው አይዘነጋም።

በጥር ወር በነበራቸው ጉብኝት ወደ ኤርትራ ከማቅናታቸው በፊት ደቡብ አፍሪካን፣ ኢስዋቲኒን እና አንጎላን ጎብኝተው ነበር።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መክፈቷን ተከትሎ ከምዕራባዊያን ውግዘት የገጠማት ሲሆን አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ግን ገለልተኛ አቋም ይዘው ቆይተዋል።

በሩሲያ ጉዳይ ላይ በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ድምጽ በተሰጠባቸው ጊዜያት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ሩሲያን ከመቃወም ተቆጥበዋል።

ላቭሮቭ ከዚያ የአፍሪካ ጉብኝት ቀደም ብሎ ስድስት ቀናት የፈጀ የአፍሪካ ጉብኝት አድርገው ነው አዲስ አበባን የመጨረሻ መዳረሻቸው ያደረጉት።

በአዲስ አበባው ቆይታቸው ደግሞ ለዓለም የምግብና ነዳጅ ዋጋ ቀውስ ምዕራባዊያን አገራት ተጣያቂ ናቸው ብለው ነበር።

ሩሲያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በሚል "የሩሲያ አፍሪካ" ስብሰባን ከጀመረች ሦስት ዓመት አልፏታል።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በ2020 ሩሲያ በውጭ ፖሊሲዋ ለአፍሪካ ቅድሚያ እንደምትሰጥ ገልጠው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ በዚህ ቆየት ባለ ንግግራቸው አገራቸው ሩሲያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደምታጠናክር፣ አልፎ ተርፎም የመከላከያ እና የደኅንነት እንዲሁም የኢኮኖሚ ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቁመው ነበር።

አፍሪካ ትልቋ የሩሲያ የጦር መሣሪያ ገበያ ባትሆንም ሞስኮ ለበርካታ አገራት የጦር መሣሪያ በብዛት ታቀርባለች።

ከ2017 ዓ/ም ጀምሮ ሩሲያ ከአንጎላ ከናይጄሪያ ከሱዳን ከማሊ ከቡርኪናፋሶና እና ከኢኳቶሪያ ጊኒ ጋር የጦር መሣሪያ ስምምነት አድርጋለች።

ሩሲያ በበኩሏ እንደ ማግኒዥየም፣ ቦክሳይት ክሮሚንየም ያሉ ለኢንዱስተሪ አስፈላጊ የሆኑ ማዕድናት እጥረት ስላለባት ለአፍሪካ ግልጽ የኢኮኖሚ ፍላጎት አላት።