የብራዚል ተጫዋቾች ዘረኝነትን በመቃወም ሙሉ ጥቁር የሆነ መለያ ለብሰው ሜዳ ገቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የብራዚል ብሔራዊ ቡድን በእግር ኳስ ዘረኝነትን በመቃወም ከጊኒ ጋር በነበራቸው የወዳጅነት ጨዋታ ሙሉ በሙሉ ጥቁር ለብሰው ወደ ሜዳ ገቡ።
የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾቹ የመጀመሪያውን አጋማሽ ብቻ ጥቁር የለበሱ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ብራዚል የምትታወቅበትን ቢጫ በሰማያዊ መለያ ለብሰው ተመልሰዋል።
ባርሴሎና በተካሄደው የወዳጅነት ጨዋታ ብራዚል አፍሪካዊቷ ጊኒን 4-1 አሸንፋለች።
የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ለዘረኝነት ቦታ የለንም የሚለውን መልዕክት ያስተላለፉት የብሔራዊ ቡድኑ አባል ቪኒሺየስ ጁኒየር በተደጋጋሚ የዘረኝነት ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ነው።
ኮከብ ተጫዋቹ ቪኒሺየስ ጁኒየር በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ለክለቡ ሪያል ማድሪድ በስፔን እየተጫወት በተደጋጋሚ የቆዳ ቀለሙን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ሲሰነዘሩበት ቆይቷል።
ግንቦት ወር ላይ ማድሪድ ከቫሌንሺያ ሲጫወት ቪኒሺየስ ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ከተሰነዘረበት የበርናቤዩ ክለብ ለስፔን ዓቃቤ ሕግ የጥላቻ ወንጀል ተፈጽሟል ሲል ሪፖርት አድርጎ ነበር።
ይህን ተከትሎ ከጥቂት ሳምንታት በፊት 7 ግለሰቦች ብራዚላዊ ተጫዋች ላይ የዘረኝነት ጥቃት አድርሰዋል ተብለው ቅጣት ተላልፎባቸዋል።
ከእነዚህ መካከል 4ቱ በድምሩ 60ሺህ ዩሮ የገንዘብ ቅጣት እና ለሁለት ዓመታት ወደ ስታዲየም ዝር እንዳይሉ የተቀጡ ሲሆን ከ18-21 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት ቀሪ ሦስት ግለሰቦች ደግሞ በድምሩ 5ሺህ ዩሮ እና የአንድ ዓመት በስታዲየም የመገኘት እግድ ቅጣት ተላልፎባቸዋል።
በትናንትው ጨዋታ ቪኒሺየስ በፍጹም ቅጣት ምት የመጨረሻዋን 4ኛ ጎል ለቡድኑ አስቆጥሯል።
የኒውካስል አማካይ ጆሊንተን ለብራዚል ተሰልፎ በተጫወተበት የመጀመሪያው ጨዋታ ቀዳሚዋን ጎል አስቆጥሮ አገሩን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ሮድሪጎ ሁለተኛዋን ጎል ካስቆጠረ በኋላ የጊኒው ጉአራሳይ በጭንቅላቱ ኳስን ከመረብ አገናኝቶ አፍሪካዊቷ አገር ወደ ጨዋታው ተመልሳ ነበር ይሁን እንጂ ብራዚል በሚሊታኦ አማካይነት ጎል አስቆጥራ በድምሩ 4-1 በሆነ ውጤት አሸንፋለች።












