የሱዳን ጦርነት፡ በካርቱም የአየር ጥቃት ሕጻናትን ጨምሮ 17 ሰዎች ተገደሉ

ካርቱም

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በሱዳን መዲና ካርቱም በደረሰ የአየር ጥቃት ከሞቱት 17 ሰዎች መካከል 5 ሕፃናት እንደሚገኙበት ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ቅዳሜ ዕለት በርካታ ሰዎች በሚኖሩበት ያርሙክ አውራጃ በደረሰው ጥቃት 25 ቤቶች ሙሉ በመሉ ወድመዋል።

ይህ የአየር ጥቃት የተፈጸመው አንድ የሱዳን ጦር ከፍተኛ ጄኔራል ራፒድ ሰፖርት ፎርስስ [አርኤስኤፍ] የተሰኘው ታጣቂ ቡድን ላይ ጥቃት እንሰነዝራለን ብለው ቃል ከገቡ ከአንድ ቀን በኋ ነው።

በሱዳን ጦርና በራፒድ ሰፖርት ፎርስስ በተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል ግጭት የተጀመረው በፈረንጆቹ ሚያዚያ ወር አጋማሽ ነው።

ለጦርነቱ ምክንያት የሆነው ጉዳይ በሃገሪቱ ወታደራዊ አመራር መካከል የተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻ መሆኑ ይታወቃል።

በሰኔ ወር መባቻ አርኤስኤፍ ያርሙክ አውራጃን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን ይፋ አድርጎ ነበር።

በመዲናዋ ካርቱም የሚገኘው ሥፍራ የጦር መሣሪያ ማምረቻ የሚገኝበት ነው።

ከጥቃቱ በኋላ ሁለቱ ተዋጊ ቡድኖች ለ72 ሰዓታት የሚቆይት የተኩስ አቁም ስምምነት መግባታቸውን የዩናይትድ ስቴትስና የሳዑዲ ባለሥልጣናት ገልጠዋል።

ከዚህ ቀደም ሁለቱ ቡድኖች የገቧቸው የተኩስ አቁም ስምምነቶች ሳይከበሩ መቅረታቸው ይታወሳል።

ምንም እንኳ በጦርነቱ ምክንያት የሞቱ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር እስካሁን ግልፅ ባይሆንም ከ1000 በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መረጃ መሠረት 2.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ሃገራቸው ውስጥ የተፈናቀሉ ሲሆን ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ደግሞ ወደ ጎረቤት ሃገራት ተሰደዋል።

ሰላማዊ ዜጎች ሃገራቸውን ጥለው ይወጡ ዘንድ ከዚህ በፊት የተለያዩ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ተገብተው ተሽረዋል።

አርኤስኤፍ እንደሚለው በቅርብ ጊዜያት ማዮ፣ ያርሙክ እና ማንዴላ በተባሉ ሥፍራዎች የደረሱት ጥቃቶች ሰላማዊ ዜጎችን ዒላማ ያደረጉ ናቸው።

የመንግሥት ጦር እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ጎረቤት ሃገር ቻድ ተሰደዋል።

በሃገሪቱ የሚገኙ ዶክተሮችና ሆስፒታሎች የሕክምና እርዳታ መስጠት ከአቅማቸው በላይ ሆኗል።

አልፎም በምዕራባዊ ሱዳን ዳርፉር ግዛት ከሁለት አስርት ዓመታት ረግቦ የቆየውን ውጥረት እንደ አዲስ ተቀስቅሷል።