ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አዲሱ የዩናይትድ ባለድርሻ ኤሪክ ቴን ሃግን ያሰናብቱ ይሆን? የጄደን ሳንቾ መጨረሻስ?
የሰር ጂም ራትክሊፍ ንብረት የሆነው ኢኒዮስ ግሩፕ 25 በመቶ ድርሻ ለመግዛት ከዩናይትድ ጋር ከስምምነት ደርሷል።
የግሌዘረ ቤተሰብ ማንቸስተር ዩናይትድን ከተቆጣጠረ ከአውሮፓወያኑ ከ2005 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ከፍተኛ ድርሻ የሸጠው።
ምንም እንኳ አሁንም መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የግሌዘር ቤተሰብ አባላጫውን የክለቡን ድርሻ ቢይዝም ሰር ጂም ራትክሊፍ የዩናይትድን የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ይቆጣጠራሉ።
ቢቢሲ ስፖርት እንደሰማው ሰር ጂም ራትክሊፍ ሙሉ በሙሉ ውሳኔ ሰጭ ሆነው ብቅ እስኪሉ ድረስ ከ6-8 ሳምንታት ሊወስድባቸው ይችላል።
የጥር ወር በጀት
ራትክሊፍ ሥልጣናቸውን የሚረከቡት በሚቀጥለው የአውሮፓውያኑ ዓመት ሁለተኛው ወር ሊሆን ይችላል። ይህ ማለት በጥር ወር የዝውውር መስኮት እጃቸውን ማስገባት አይችሉም ማለት ነው።
የግሌዘር ቤተሰብ ላለፉት 18 ወራት ዩናይትድን ሲያስተዳድር ለተጫዋቾች ዝውውር 2.21 ቢሊዮን ዩሮ አፍስሷል።
በተመሳሳይ ጊዜ ከዩናይትድ በላይ ለተጫዋቾች ዝውውር ብዙ ገንዘብ ያወጡት ቼልሲ [2.7 ቢሊዮን ዩሮ] እና ማንቸስተር ሲቲ [2.33 ቢሊዮን ዩሮ] ናቸው።
የግሌዘር ቤተሰብ ከትርፍ ከሚያገኙት ገቢ በተጨማሪ ከራሳቸው ኪስ ገንዘብ ቢያወጡ ወጪው ከዚህም ይልቅ ነበር።
በጥር ወር የዝውውር መስኮት ጥራት ያለው ተጫዋች ማግኘት ከባድ ነው። ኤሪክ ቴን ሃግ በአነስተኛ በጀት ያላቸውን አብቃቅተው እንዲጠቀሙ ሊገደዱ ይችላሉ የሚሉ ዘገባዎች አሉ።
ግብ ጠባቂው ጃክ በትላንድ፣ ሳቢትዘር፣ ዌግሆርስት፣ ሬጊዮን እና ሶፍያን አምራባት በውሰት ዩናይትድን ከተቀላቀሉ ተጫዋቾች መካከል ናቸው።
የ23 ዓመቱ ጄደን ሳንቾ ጉዳይ ሌላው የኤሪክ ቴን ሃግ ራስ ምታት ነው።
የቴን ሃግ ዕጣ ፈንታ
ምንም እንኳ ማንቸስተር ዩናይትድ ዘንድሮ በውጤት ቀውስ ቢንገዳገድ የአሠልጣኙ ዕጣ ፈንታ አደጋ ላይ መሆኑን የሚጠቁም ነገር የለም።
ነገር ግን እንደማንኛውም አሰልጣኝ የኔዘርላንዳዊው ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው ሜዳ ላይ በሚያሳዩት ብቃት ነው።
ባለፈው ቅዳሜ በዌስት ሀም ሽንፈት የቀመሰው ዩናይትድ ከ1930 ጀምሮ የውድድር ዘመን መባቻ ላይ እንዲህ ያለ አቋም አሳይቶ አያውቅም።
ባለፈው ኅዳር የፕሪሚዬር ሊግ የወር ምርጥ አሰልጣኝ ተብለው ቢሸለሙም ካለፉት ሰባት ጨዋታዎች አንድ ጨዋታ ብቻ ነው የረታው።
ከቻምፒዮንስ ሊግ እና ሊግ ዋንጫ ውድድሮች በጊዜ ተሰናብተዋል።
ዩናይትድ በሚቀጥሉት ቀናት በሜዳቸው ከአስተን ቪላ እና ቶተንሀም ይጫወታሉ። በእነዚህ ጨዋታዎች ተፈትነው ማለፋቸው ምናልባት ከአንድ እስከ አራት ደረጃ ያጠናቅቃሉ የሚለውን ጥያቄ ሊመልስ ይችላል።
ቴን ሃግ ባለፉት ሶስት የዝውውር መስኮቶች 400 ሚሊዮን ዩሮ ለተጫዋቾች ዝውውር አውለዋል።
የጄደን ሳንቾ ጉዳይ
የጄደን ሳንቾ ዕጣ ፈንታ በጣም አነጋጋሪ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።
ጄደን ሳንቾ “ማምለጫ ምክንያት ሆኛለሁ” ሲል በማሕበራዊ ሚድያ ገፁ የፃፈው መልዕክት ነው ከኤሪክ ቴን ሃግ ጋር ያለውን ግንኙነት ያቆረፈደበት።
መስከረም ወር ዩናይትድ ከሜዳው ውጭ ከአርሰናል ጋር ሲጫወት ጄደን ሳንቾ አልተሰለፈም ነበር።
ይህን ተከትሎ ነው ቴን ሃግ እንግሊዛዊውን ተጫዋቸች ይቅርታ ካልጠየቀኝ አላሰልፈውም ብለው የቆረጡት። በዚህ ምክንያት የጄደን ሳንቾ ጉዳይ ያበቃለት ይመስላል።
የሰር ራትክሊፍ ቀኝ እጅ የሆኑት ሰር ዴቭ ብሬይልስፎርድ የሳንቾን ደሞዝ መክፈል አሊያም ከቦሩሲያ ዶርትመንድ በ73 ሚሊዮን ፓውንድ የተገዛውን ተጫዋች በኪሳራ መሸጥ ይጠበቅባቸዋል።
ኦልድ ትራፈርድና ደጋፊዎች
በስምምነቱ መሠረት ሰር ራትክሊፍ ኦልድ ትራፈርድ ስታድየምን ለማሳደስ 300 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ያደርጋሉ።
ምንም እንኳ ይህ ገንዘብ ትልቅ ቢሆንም ኦልድ ትራፈርድን ለማደስ የሚበቃ ነው ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።
የዩናይትድ ደጋፊዎች1 ቢሊዮን ፓውንድ ያክል ዕዳና የተለያዩ ወጪዎች ክፍያ ያሉበት የግለዜር ቤተሰብ ገንዘቡን ተጠቅሞ ቡድኑን ማሻሻል ይችል ነበር ሲሉ ይከራከራሉ።
እርግጥ ነው ክለቦች ስታድየም ሲገነቡ ገንዘብ ከኪሳቸው ብቻ ሳይሆን ከሌላ ምንጭም መፈለግ አለባቸው። የቶተንሃም ሆትስፐርስን የ1 ቢሊዮን ዶላር አዲስ ስታድየም እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል።
ነገር ግን በዕዳ ለተዘፈቀ እንደ ዩናይትድ ያለ ክለብ ለስታድየም እደሳ ገንዘብ መበደር አለበት የሚለው ሐሳብ ለደጋፊዎች የሚዋጥ አይደለም።
የዩናይትድ ደጋፊዎች ከ12 ወራት በፊት የግሌዘር ቤተሰብ ክለቡን ሊለቁ ነው ሲባል ዜናውን በደስታ ነበር የተቀበሉት።
የግሌዘር ቤተሰብ ግን በቅርቡ የሚለቁ አይመስሉም። የካታሩ ሃብታም ሼኽ ጃሲም ክለቡን የመግዛታቸው ጉዳይም ያከተመለት ይመስላል።