ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእስራኤል ምርጫ ቅድመ ውጤት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እየመሩ እንደሆነ አመላከተ
የቀድሞ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ትላንት ማክሰኞ በሀገራቸው በተከናወነው ምርጫ እየመሩ መሆናቸውን የቅድመ ምርጫ ውጤቶች አመላክተዋል።
ከይፋዊ የምርጫ ውጤት በፊት ይፋ የሆኑ ቅድመ ውጤቶች እሳቸው የሚመሩት የቀኝ አክራሪ ፓርቲ በአነስተኛ አብላጫ ድምጽ እየመራ እንደሚገኝ አመላክቷል።
ውጤቱም ለተከታታይ 12 ዓመታት በስልጣን ከቆዩ በኋላ ሃላፊነታቸውን ለቀው የነበሩትን ኔታንያሁ ወደ ፖለቲካው መድረክ የመለሰ ነው ተብሏል።
በእየሩሳሌም ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግርም “ለታላቅ ድል ተቃርበናል” ብለዋል።
ምርጫው ኔታንያሁን መደገፍ ወይመ አለመደገፍ ተደርጎ በስፋት ሲታይ ቆይቷል።
ከሰዓታት በኃላ ይፋ እንደሚሆን የሚጠበቀው ዋናው ውጤት ከተጠበቀው በተቃራኒ ሊሆን የሚችልበት ዕድል አለ ተብሏል።
ዋነኛ ተፎካካሪያቸው እና የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ያይር ላፒድ እስካሁን የተወሰነ ነገር የለም ብለዋል።
የቅድመ ውጤቱ ይፋ ሲሆን በእየሩሳሌም ከሚገኘው የኔታናንያሁ ፓርቲ ቢሮ የተከፈተ ከፍ ያለ ሙዚቃ ተሰምቷል።
የ73 ዓመቱ ኔታንያሁ በእስራኤል ፖለቲካ ውስጥ በአወዛጋቢነት ከሚነሱ ፖለቲከኞች አንዱ ናቸው። ጠንካራ ተቺዎች እንዳሏቸው ሁሉ ሰፊ ድጋፊም አላቸው።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1967 ከመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በኃላ እስራኤል በተቆጣጠረችው ዌስት ባንክ ላይ የዘረጉት የሰፈራ ፕሮግራም ጠንካራ ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል።
ምንም እንኳን እስራኤል ባትቀበለውም ይህ የሰፈራ ፕሮግራም ከዓለም አቀፍ ህግ አንጻር ህገ ወጥ እንደሆነ ይገመታል።
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በዌስት ባንክ እና በጋዛ ሰርጥ የፍልስጤምን እንደ ሀገር መመስረት የእስራኤል እና ፍልስጤምን ግጭት ለመፍታት የቀረበውን እና የባይደን አስተዳደርን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ የሚሰጠውን የመፍትሄ ሃሳብ ይቃወሙታል።
ኔታናንያሁ በጉቦ፣በማጭበርበር እና የተጣለባቸውን እምነት በማፍረስ ተከሰው ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ ሲሆን የሚቀርብባቸውን ክስ በሙሉ አይቀበሉትም።
በእስራኤል ቴሌቪዥን የተላለፉ የቅድመ ምርጫ ውጤቶች በሀገሪቱ ፓርላማ ካለው 120 መቀመጫ የሳቸው ፓርቲ 61 ወይም 62ቱን እንዳገኘ ይፋ አድርገዋል።