ህወሓት ለግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ያወጣውን ረቂቅ ሕግ "በዝባዥ" በማለት ሂውማን ራይትስ ዋች እንዲሰረዝ አሳሰበ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የትግራይ ክልል መሪዎች ለወታደራዊ ግዳጅ ምልመላ ለማድረግ "ኃይል የሚሰጣቸውን" እና ተቃዋሚዎችን እንዲቀጡ "መንገድ የሚጠርግላቸውን" ረቂቅ አዋጅ እንዲሰርዙ ሂውማን ራይትስ ዋች አሳሰበ።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ሰኔ 16/2018 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ ህወሓት ረቂቅ አዋጁን ያወጣው በፌደራል መንግሥቱ የተሾሙ የክልሉን አስተዳዳሪዎች ከሥልጣን አውርዶ "ከኤርትራ ብሔራዊ የውትድርና አገልግሎት ጋር የሚመሳሰል አፈሳ ከጀመረ በኋላ ነው" ብሏል።

የሂውማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሻ ባድር "የትግራይ ተወላጆች ከሁለት ዓመቱ አውዳሚ ግጭት እና ካስከተለው መዘዝ ገና እያገገሙ" እንደሆነ ጠቅሰው፤ "የክልሉ ባለሥልጣናት አሁን ባለው የፖለቲካ ውጥረት ሳቢያ ሲቪሎች ወታደራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስገደድ እና ጎን ለጎን ደግሞ የግዳጅ ምልመላውን የሚተቹትን መቅጣት የለባቸውም" ብለዋል።

"የትግራይ ሕዝብን ኅልውና እና ደኅንነት ለማረጋገጥ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ያወጣው አዋጅ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ረቂቅ ሰነድ በክልሉ ምክር ቤት እንደሚጸድቅ ቢቢሲ ትግርኛ ከምንጮቹ ያገኘው መረጃ ይጠቁማል።

በረቂቅ አዋጁ የመጀመሪያ ክፍል አንቀጽ 5 ላይ ዕድሜ እና ጤና የሚፈቅድለት ማንኛውም የትግራይ ተወላጅ የክልሉ መንግሥት የሚያቀርብለትን የክተት ጥሪ ተቀብሎ የመሳተፍ "ብሔራዊ ግዴታ" እንዳለበት ይገልጻል።

በሦስተኛው ክፍል ደግሞ "የወንጀል ተጠያቂነት" በሚለው የረቂቅ ሕጉ ክፍል ሥር፣ በትግራይ ጦር ውስጥ ለመቀላቀል ወይም ለመዋጋት ፈቃደኛ ያልሆነ ማንኛውም ሰው፤ በደጀን ወይም በግንባር ግዴታውን እንዲፈጽም ጥሪ ቀርቦለት ያልተቀበለ ከሆነ፤ ከ10,000 እስከ 50,000 ብር ተቀጥቶ ግዴታውን እንዲፈጽም ይደረጋል ሲል ይደነግጋል።

በትግራይ እየተካሄደ ያለው የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ በፈጠረው ስጋት ምክንያት በርካታ ወጣቶች ከክልሉ እየወጡ ወደ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል እየሸሹ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ እዚያው ተደብቀው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

አፈሳው ከነዋሪዎች እና ከመብት ተሟጋቾች ውግዘት እየገጠመው ቢሆንም ምልመላው በፈቃደኝነት የሚካሄድ ነው በማለት ህወሓት ማስተባበሉን የፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) መዘገቡ ይታወሳል።

በትግራይ በስፋት እየተካሄደ ያለው ወደታራዊ ምልመላ በአብዛኛው "በፈቃደኝነት ላይ ብቻ ተመሥርቶ" የሚካሄድ መሆኑን የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር አቶ አማኑኤል አሰፋ ተናግረዋል።

ነገር ግን ሁሉም የትግራይ ተወላጅ "ግዛቱን ከኅልውና ስጋት መከላከል ስላለበት ልዩ ሁኔታዎች አሉ" በማለት የግዳጅ ምልመላው እንዳለ በተዘዋዋሪ ገልጸዋል።

ሂውማን ራይትስ ዋች ባወጣው መግለጫ፤ ረቂቅ አዋጁ "አሻሚ እና በጣም የተለጠጠ ቋንቋ መያዙን" ይጠቅሳል።

ይህም "ለብዝበዛ ክፍት መሆኑን" እንዲሁም ለተለያዩ ጥፋቶች "እስራት እና የሞት ቅጣትን" ማካተቱን ገልጿል።

ረቂቁ የወጣው በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ያለው ውጥረት በመባባሱ የትግራይ ንጹኃን ዜጎችን "ለተጨማሪ የጭካኔ ድርጊት" ያጋልጣል የሚል ፍርሃት በተፈጠረበት ወቅት መሆኑን ያመለክታል።

ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች- ኢትዮጵያ የተባለው የሰብአዊ መብት ድርጅት "የትግራይ የፀጥታ ኃይሎች በክልሉ መጠነ ሰፊ አፈሳ እና የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እያካሄዱ መሆናቸውን" በመጥቀስ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ወጣቶችም ከሥራ ቦታቸው፣ ከመዝናኛ ሥፍራዎች እንዲሁም ከሕዝብ ትራንስፖርት ላይ በግዳጅ ተወስደው ወደተለያዩ ካምፖች መላካቸውን ተናግረዋል።

ውጥረቱ በተባባሰበት ወቅት፤ አሜሪካ "በኢትዮጵያ ያለውን ሰላም በማናጋት" ውስጥ ተሳታፊ ናቸው ባለቻቸው አክራሪ የህወሓት አባላት እና የቅርብ የቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ ክልከላ መጣሏን ማስታወቋ አይዘነጋም።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ በአክራሪ ህወሓት አባላት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት እንዲያገረሽ የሚያደርግ ውጥረት እየተባባሰ መምጣቱን በመግለጽ ይህም "በቀጣናው ያለውን ሰላም እና መረጋጋት የሚያናጋ ነው" ብሏል።

ህወሓት ባወጣው መግለጫ የአሜሪካን የቪዛ ክልከላ "ሚዛናዊ ያልሆነ" ሲል አውግዟል።

የአሜሪካ እርምጃ የትግራይን እውነታ እንደማያንጸባርቅ እና የፌደራል መንግሥቱን "ተጠያቂነት ያላደረገ" መሆኑን በመጥቀስም ኮንኗል።

የህወሓት የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ "ከኤርትራ ብሔራዊ የውትድርና አገልግሎት" ጋር እንደሚመሳሰል እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ተቀማትም ይሄንን ማውገዛቸውን ሂውማን ራይትስ ዋች ጠቅሷል።

"የግዳጅ ምልመላ፣ ገደብ የለሽ ወታደራዊ አገልግሎት፣ የእንቅስቃሴ ገደብ እና ከወታደራዊ ምልመላ የሚያመልጡ ሰዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን መቅጣትን" የተመድ መርማሪ ተቋማት "በተገቢው ሁኔታ መኮነናቸውን" በመግለጫው አካቷል።

የትግራይ ጦርነትን ያስቆመውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ያስተባበሩ ወገኖች፤ ማለትም የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ "የትግራይ መሪዎች የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላውን እና ረቂቅ አዋጁን እንዲሰርዙ በይፋ መጠየቅ አለባው" በማለት አሳስቧል።

የአፍሪካ ኅብረት የፕሪቶሪያ ስምምነት ትግበራን የሚቆጣጠርበትን አሠራር በመጥቀስ "የግዳጅ አፈሳውን እና የቀድሞ ተዋጊዎች ዳግመኛ መሰማራትን" መርምሮ ግኝቱን ለሕዝን ይፋ እንዲያደርግ ጠይቋል።

የሂውማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሻ ባድር "የትግራይ አስተዳዳሪዎች ተጋላጭ የሆነው የትግራይ ሕዝብ ወታደራዊ ዓላማውን እንዲደግፍ በማስገደድ ለተጨማሪ ብዝበዛ ማጋለጥ የለባቸውም" ብለዋል።

"የሚመለከታቸው መንግሥታት ያላቸውን ተጽዕኖ የማሳደር አቅም በመጠቀም አዲስ ግጭት እንዳይነሳ ማገዝ አለባቸው" ሲሉም አክለዋል።

ሂውማን ራይትስ ዋች ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ አሁን ባለው የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ የትግራይ ባለሥልጣናት እና የትግራይ ኃይሎች የቀድሞ ተዋጊዎች ለወታደራዊ ዕዛቸው ሪፓርት እንዲያደርጉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል ብሏል።

"ቤት ለቤት በመሄድም በጅምላ፣ በግዳጅ ተዋጊዎችን አፍሰዋል" ያለው ሂውማን ራይትስ ዋች፤ አገር በቀል የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማትን እና መገናኛ ብዙኃንን በመጥቀስ አፈሳው "ልጆችንም እንደሚጨምር" አስታውቋል።

የትግራይ የፀጥታ ኃይሎች "ከአፈሳ የሚያመልጡ የታዳጊ ልጆች ወላጆችን እየቀጡ" መሆኑን ጥቆማ እንደደረሰው ገልጿል። አፈሳውን በመሸሽ እና አዲስ ግጭት ሊነሳ ይችላል በሚል ስጋት ከክልሉ የሚሸሹ መኖራቸውንም አያይዞ ጠቅሷል።

ህወሓት ያወጣው ረቂቅ አዋጅ "የሕዝብ ትዝብትን" ያላካተተ መሆኑን የመብት ተሟጋቹ ገልጿል።

በረቂቅ አዋጁ ውስጥ እስከ ሞት እንደሚያስቀጡ የተቀመጡ ድርጊቶችን በመዘርዘርም "በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የሞት ቅጣትን አንቀበልም፤ የጭካኔ እና የመጨረሻ ውሳኔ ነው" ሲል ትችቱን አቅርቧል።

በረቂቅ አዋጁ ከአንቀጽ 29 እስከ 30፤ በተለይም በጦርነት ጊዜ በመሠረተ ልማት፣ በሕዝብ እና በመንግሥት ተቋማት ላይ የሚደርስ ጉዳት፣ ከጠላት ጋር መተባበር እና የምሥጢር ማሹለክ በእስራት እና በገንዘብ እንደሚያስቀጣ፤ ድርጊቱ ሆን ተብሎ ከተፈጸመ በዕድሜ ልክ እስራት ወይም ሞት እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል።

እንቅስቃሴው በሕዝቡ ላይ አለመረጋጋት ከፈጠረ፣ በሕግ እና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ ወይም በባለሥልጣናት ወይም በትግራይ ሠራዊት ላይ ጉዳት ማድረስ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም እስከ ሞት ሊያስቀጣ የሚችል ወንጀል ሆኖ ሰፍሯል።

ከውጭ መንግሥት ጋር በመተባበር "የትግራይን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት መፈጸም" እንደ ድርጊቱ ዓይነት ከባድ ከሆነ እስከ ሞት ድረስ የሚያስቀጣ እንደሆነ ተገልጿል።

በአንቀጽ 44 ላይ የተገለጸው እና እስከ ሞት ቅጣት የሚያደርሰው ወንጀል ከጠላት ጋር የኢኮኖሚ ትብብር ማድረግ ወይም መመካከር የሚል ነው።

ህወሓት ያወጣው ረቂቅ አዋጅ "የመስዋዕትነትን ክብር ማሳነስ፣ የተዋጊዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን ክብር መንካት በተለይም የተደራጀ የሚዲያ ቅስቀሳ ከሆነ እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት ያስቀጣል" ይላል።

ሂውማን ራይትስ ዋች ይሄንን አንቀጽ በመጥቀስ፤ ህወሓት ገለልተኛ ጋዜጠኞች እና መገናኛ ብዙኃን ላይ "አሁንም እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ" በመግለጽ ተችቷል።