"በሕይወቴ እንዲህ ያለ ፍፁም ቅጣት ምት አይቼ አላውቅም" - ሚኬል አርቴታ

ሚኬል አርቴታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ቅዳሜ ምሽት በነበረው ፍልሚያ ውጤት ደስተኛ አይመስልም። ሁኔታውን "ግራ የሚያጋባ" ሲሉ ገልጾታል።

ቅዳሜ ምሽት አርሰናል ወደ ብራይተን ሜዳ አቅንቶ አንድ አቻ ተለያይቶ ተመልሷል።

ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት አርሰናሎች በመጀመሪያው አጋማሽ በ17 ዓመቱ ታዳጊ ኢተን ንዋኔሪ ጎል እየመሩ ሶስት ነጥብ ለማግኘት አስበው ነበር።

ነገር ግን የአርሰናሉ ተከላካይ ዊሊያም ሳሊባ በአጥቂ ጃዎ ፔድሮ ላይ በሰራው ጥፋት ምክንያት ዳኛው ለብራይተን ፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል።

ፔድሮ ፍፁም ቅጣት ምቱን ወደ ጎል በመቀየት ሁለቱ ቡድኖች ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

"በውሳኔ እጅግ ተበሳጭተናል። እኔ እንዲህ ያለ [ፍፁም ቅጣት ምት] በሕይወቴ አይቼ አላውቅም" ሲል ሚኬል አርቴታ ለቢቢሲ ስፖርት ተናግሯል።

"[ሳሊባ] ኳሱን ነክቶታል። በጣም ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። እኔ በእግር ኳስ ዘመኔ እንዲህ አጋጥሞኝ አያውቅም። ተጫዋቾቼንም ስጠይቃቸው አይተን አናውቅም ነው ያሉኝ። አዲስ ነገር ይሆናል።"

ስፔናዊው አሰልጣኝ በመሐል ዳኛው አንተኒ ቴይለር ውሳኔ ደስተኛ ባይሆንም የብራይተኑ አሰልጣኝ ፋቢያን ሁርዝለር ግን ውሳኔው ተገቢ ነው ይላል።

"ግልፅ ፍፁም ቅጣት ምት ነው። ጭንቅላት ለጭንቅላት ነው የተጋጩት" ሲል ጀርመናዊው አሰልጣኝ ሐሳቡን ሰጥቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አርሰናል በመጀመሪያው አጋማሽ ጎል አስቆጥሮ ነው ወደ መልበሻ ክፍል የገባው።

በሁለተኛው አጋማሽ አቻ የሚያደርጋቸውን ጎል እየፈለጉ የነበሩት ብራይተኖች ተጭነው እየተጫወቱ ሳለ ጃዎ ፔድሮ በአርሰናል ሳጥን ውሰጥ ያገኘውን ኳስ በጨንቅላቱ ከገጨ በኋላ ነው ከሳሊባ ጋር የተላተመው።

የመሐል ዳኛው ጥቂት ሰከንዶች ከወሰዱ በኋላ እጃቸውን ወደ ፍፁም ቅጣት ምት መምቻው ሰደዋል። ቪኤአር ሁኔታውን ከመረመረ በኋላ በዳኛው ውሳኔ ተስማምቷል።

ከጨዋታው በኋላም ቢሆን ውሳኔው አከራካሪነቱ ቀጥሏል። በርካታ ተንታኞች በሁለት ጎራ ተከፍለው ሲወያዩበት ተስተውሏል።

የቢቢሲ ማች ኦፍ ዘ ደይ አቅራቢ ጋሪ ሊኒከር "በጭንቅላት ግጭት ምክንያት ፍፁም ቅጣት ምት ሲሰጥ አይቼ አላውቅም" ብሏል።

ምንም እንኳ አርሰናል ፍፁም ቅጣት ምቱ አይገባንም ቢሉም በርካታ ተንታኞች አርሰናል በጨዋታው ከአቻ በላይ አይገባውም ሲሉ ሞግተዋል።

ታዳጊው ንዋኔሪ በሊጉ ሁለተኛ ጎሉን አስቆጥሯል። 18 ዓመት ሳይሞላው ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ዌይን ሩኒ 18 ዓመት ሳይሞላው 6 ጎሎች በማስቆጠር የመጀመሪያውን ሥፍራ ይዟል።

አርሰናል በ20 ጨዋታዎች 40 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ያሉት መሪው ሊቨርፑል እሑድ ምሽት በሜዳው ማንቸስተር ዩናይትድን ያስተናግዳል። ሊቨርፑል በ45 ነጥብ የሰንጠረዡ አናት ላይ ተቀምጧል።

በሌሎች ጨዋታዎች ቶተንሀም በሜዳው በኒውካስል 2-1 ሲረታ ሲቲ ዌስት ሀምን አስተናግዶ 4-1 አሸንፏል። ቼልሲ ከፓላስ 1 አቻ ወጥቷል። ቪላ፣ ቦርንመዝ እና ብሬንትፈርድ ድል ቀንቷቸዋል።

እሑድ ተጠባቂው ጨዋታ በአንፊል ሊቨርፑል ከዩናይትድ የሚያደርጉት ነው። ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ ፉልሀም ኢፕስዊችን ያስተናግዳል።