አነጋጋሪው የፊፋ ፕሬዝዳንት 24 ጨዋታዎችን ለማየት ያደረጓቸው 27 በረራዎች

የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በሁለት ሳምንት ውስጥ 24 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ተመልክተዋል። በሰሜን አሜሪካ ያደረጉት የአውሮፕላን ጉዞ ሲደመር ሺዎች ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍን ነው።
በአሜሪካ፣ በካናዳ እና በሜክሲኮ የሚገኙ 16 ከተሞች የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ያስተናግዳሉ። በቡድን ማጣሪያ ጨዋታዎች መራዘም ምክንያት የሚካሄዱት ግጥሚያዎች ቁጥር ጨምሯል።
ፊፋ ለ2026 የዓለም ዋንጫ ባወጣው የዘላቂነት እና ሰብአዊ መብቶች ስትራቴጂ ላይ ፕሬዝዳንቱ "በአየር ንብረት፣ ሰብአዊ መብት፣ በሽታን ወይም የአካል ጉዳትን በተመለከተም የድርሻችንን ለመወጣት ቁርጠኛ ነን" ብለዋል።
የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ (ቢቢሲ ቬሪፋይ) እና ቢቢሲ ስፖርት ከፊፋ እንዲሁም ከፕሬዝዳንቱ ኢንፋንቲኖ ጋር የተያያዙ የጄት ጉዞዎችን ተከታትለዋል።
ኢንፋንቲኖ ፎቶ የተነሱባቸው የዓለም ዋንጫ ግጥሚያዎችን በመከታተል የአውሮፕላን ጉዟቸው ምን ያህል በከባቢ አየር ላይ ጫና እንዳሳደረ ፈትሿል።
ጉዞው ያስከተው ተጽዕኖ በአማካይ 78 ሰዎች በዓመት ውስጥ ከሚያካሂዱት የአውሮፕላን በረራ ጋር የሚስተካከል ነው።
የፊፋ ፕሬዝዳንት ምን ያህል ተጉዘዋል?
አገራት ከቡድናቸው ለማለፍ ጨዋታ በሚያደርጉበት ወቅት ኢንፋንቲኖ አብዛኛውን ጊዜ በአንድ ቀን ሁለት ግጥሚያ ተመልክተዋል።
ከጨዋታዎቹ አብዛኞቹ በመቶ ማይል ርቀት ላይ በሚገኙ ከተሞች ነው የተካሄዱት። በአንዳንድ ቀናት የፊፋ ፕሬዝዳንት በአንድ ቀን ሦስት የተለያዩ በረራዎች አድርገዋል።
ኢንፋንቲኖ በኳታር አየር መንገድ ጄት ሲጓዙ የሚያሳይ ምሥል ወጥቷል። በዓለም ዋንጫ እየተጠቀሙ ያሉት አውሮፕላን ገልፍስትሪም ጂ650ኢአር (Gulfstream G650ER) ነው።
ቢቢሲ ይሄንን ለማረጋገጥ ፊፋን ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።
የአውሮፕላኖችን ጉዞ የሚከታተል መረጃን በመጠቀም በረራዎቹን ተከታትሏል። በአንድ ቀን በተለያዩ ከተሞች የተካሄዱ ጨዋታዎች ላይ የፊፋ ፕሬዝዳንት የተነሷቸውን ፎቶዎች በመከታተል መዳረሻቸውን ለማወቅም ተችሏል።

ረዥሙን በረራቸውን ያደረጉት በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ሲሆን፤ ሰኔ 7/2018 ዓ.ም. የአውስትራሊያ እና ቱርክን ግጥሚያ ተመልክተው ከቫንኩቨር ወደ ማያሚ 2,800 ማይል (4,507 ኪሎሜትር) ተጉዘዋል።
አጫጭር ጉዞዎችንም አድርገዋል። በአውሮፓውያኑ ሰኔ 15/2018 ዓ.ም. ከፊላደልፊያ ወደ ኒው ጀርሲ ተራቦሮ አውሮፕላን ማረፊያ 92 ማይል (148ኪሎሜትር) ተጉዘዋል።
ኢንፋንቲኖ ጨዋታውን የተመለከቱት በዚህ ከተማ አይደለም። በነጋታው ግን በአጎራባቿ ከተማ ኒው ዮርክ ከፎክስ ኒውስ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።
በዚያኑ ቀን ጨዋታዎች ለመታደም ወደ ቦስተን እና ቶሮንቶ ሄደዋል።
በአንድ ቀን ውስጥ ያደረጉት ረዥም በረራ ሰኔ 8/2018 ዓ.ም. ያደረጉት ሲሆን፣ 2,700 ማይል (4,000 ኪሎሜትር) ተጉዘዋል።

የቤልጂም እና ግብፅ ጨዋታን ለመመልከት ከማያሚ ወደ ሲያትል የሄዱ ሲሆን ይህም ወደ 960 ማይል (1,545 ኪሎሜትር) ርቀት ነው።
ከዚያም ወደ ሎስ አንጀለስ ተጉዘው የኢራን እና ኒው ዚላንድን ግጥሚያ ተከታትለዋል።
አውሮፕላኑ ከአምስት ሰዓት በኋላ በድጋሚ ተነስቶ ወደ ሲያትል 2,700 ማይል (4,345 ኪሎሜትር) ተጉዞ ከዚያም በነጋታው ጠዋት ወደ ማያሚ ተመልሷል።
24ኛውን እና የመጨረሻውን የቡድን ጨዋታ የተመለከቱት በነጋታው በማያሚ ሲሆን፣ ተጋጣሚዎቹ ፖርቹጋል እና ኮሎምቢያ ነበሩ።
የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ከተጀመሩበት ቀን አንስቶ እስከ ሰኔ 20/2018 ዓ.ም. ድረስ አጠቃላይ የግል ጄት ጉዟቸው ቢያንስ 31,144 ማይል (50,122 ኪሎሜትር) እንዲሁም ከ66 ሰዓታት በላይ እንደሚደርስ ቢቢሲ ለማወቅ ችሏል።

በረራዎቹ ምን ያህል የካርን ልቀት አስከተሉ?
በግል አውሮፕላን መብረር ከፍተኛ የካርበን ልቀት ከሚያስከትሉ የጉዞ ዓይነቶች መካከል ይጠቀሳል።
የሚለቅቀው በካይ ጋዝ (ግሪንሀውስ ጋዝ) ከባቢ አየር እንዲግል በማድረግ እና የአየር ንብረት ለውጥን በማባባስ ይታወቃል።
ኢንፋንቲኖ የሚጠቀሙበት የአውሮፕላን ዓይነት (ገልፍስትሪም ጂ650ኢአር) በአንድ ሰዓት እስከ 1,817 ሊትር ነዳጅ ያስፈልገዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀት ስሌትን በመጠቀም፤ የፊፋ ፕሬዝዳንት በቡድን ጨዋታዎች ወቅት ያደረጉት ጉዞ በአጠቃላይ ከ516 ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋር ይስተካከላል።
ይህ አሐዝ የካርቦን ዳይኦክሳይድ እና ሌሎችም በቀጥታ የሚለቀቁ ጋዞችን አንድ ላይ ያሳያል። በእጅ አዙር በከባቢ አየር ላይ የሚያደርሰው ጉዳትም ተጨምሯል።
ትክክለኛ የልቀት መጠንን ለማወቅ ስለማይቻል እነዚህ አሐዞች ግምት ናቸው።
አውሮፕላን ሲነሳ እና ሲያርፍ ያለው የልቀት መጠን ከፍተኛ ነው።
በመላው ዓለም አንድ ሰው በአማካይ 6.56 ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቅት እንዳለው የአውሮፓ ኅብረት መረጃ ይጠቁማል።
ስለዚህ የፊፋ ፕሬዝዳንት ጉዞዎች በአጠቃላይ 78 ሰዎች በዓመት ውስጥ ከሚኖራቸው የካርን ዳይኦክሳይድ ልቀት ጋር ይስተካከላሉ።
በአውሮፕላናቸው ውስጥ ምን ያህል ሰዎች እንደነበሩ ባናውቅም 19 ሰዎች መጫን ይችላል። ምን ያህል ሰዎች አብረዋቸው እንደበረሩ ስለማይታወቅ ልቀቱን በተጓዦች ልክ ማወቅ አልተቻለም።
የፊፋ ተወካይ ለቢቢስ ስፖርት "የፊፋ ፕሬዝዳንት ከከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ለቢዝነስ እና ከግጥሚያ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ብዙውን ጊዜ ይጓዛሉ። ሲመቻቸውም የፊፋ አባል ማኅበራትን ይጎበኛሉ" ብለዋል።
"አንዳንዴ በአነስተኛ ወጪ የንግድ በረራዎች ሲከናወኑ አንዳንዴ የግል ጄት ይመደባል። ይህ የሚወሰነው በየሁኔታው እና የትኛው ጉዞ ወጪ ይቀንሳል የሚለው ታይቶ ነው" ሲሉም አክለዋል።
በዓለም ዋንጫ የተካሄዱ በረራዎች በንግድ አውሮፕላን ስለመሆናቸው፣ ምን ያህል ሰዎች በኳታር ጄት እንደበረሩ እና ፊፋ በጉዞዎቹ የሚከሰተውን ልቀት ለማካካስ ይሞክር እንደሆነ ተጠይቀው ምላሽ አልሰጡም።
'ኩል ዳውን' በተባለው የስፖርት እና አየር ንብረት ለውጥ ተቋም ውስጥ የሚሠራው፣ የሰሴክስ ዩኒቨርስቲ አጥኚ ፍሬዲ ዴሊ እንደሚለው ኢንፋንቲኖ በዓለም ዋንጫ በግል ጄት መጓጓዛቸው "ፊፋ በከባቢ አየር ጥበቃ እና ዘላቂነት ላይ ስኬታማ ያለመሆኑ ማሳያ ነው" ብለዋል።
"ኢንፋንቲኖ በግል ጄት ለመብረር መምረጣቸው ፊፋ መሪዎች ደረጃ የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ ማሳየት ካለበት ምሳሌ ጋር የሚጻረር ነው" ሲልም ያስረዳል።
በአውሮፓ የትራንስፖርት እና ከባቢ አየር ፌደሬሽን ዘላቂነት ያለው ጉዞ ባለሙያ ዴኒስ አውክሌር በግል አውሮፕላን መጓዝ "ከልክ ያለፈ ጉዳት አለው" ትላለች።
"ከንግድ አውሮፕላኖች አንጻር ከአምስት እስከ 14 እጥፍ በካይ ናቸው። ከባቡር አንጻር ደግሞ 50 እጥፍ ይበክላሉ" ስትልም ታብራራለች።

ፊፋ በዓለም ዋንጫ ስለ አካባቢ ጥበቃ ምን ብሎ ነበር?
ፊፋ በአውሮፓውያኑ 2030 የበካይ ጋዝ የልቀት መጠኑን 50 በመቶ ለመቀነስ ቃል ገብቷል። በ2040 ደግሞ የልቀት እና ልቀትን ከከባቢ አየር የማስወገድ ምጣኔውን (net-zero) እንደሚያስተካክል አስታውቋል።
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ፊፋ ቃል የገባቸውን ነጥቦች እንመልከት፦
- የታዳሚዎችን ረዥም ርቀት ጉዞ ለመቀነስ ብሔራዊ ቡድኖች በቀጣናቸው እንዲጫወቱ ማድረግ
- ኤሌክትሪክ መኪና እና የሕዝብ ትራንስፖርት በመጠቀም እንዲሁም ውሃ በመቆጠብ የኢነርጂ ብክነትን መቀነስ
- ጥቅም ላይ እየዋሉ በሚገኙ ስቴድየሞች መገልገል
ሆኖም ግን ጨዋታው ከመጀመሩ በፊትም እነዚህ ቃሎች ስለመከበራቸው የአየር ንብረት ለውጥ ሳይንቲስቶች ጥያቄ ነበራቸው።
'ግሎባል ሳይንቲስትስ ፎር ግሎባል ሪስፖንስብሊቲ' በ2025 ባወጣው ሪፖርት የዓለም ዋንጫ አጠቃላይ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት ዘጠኝ ሚሊዮን ቶን እንደሚሆን ገምቷል።
ይህም ካለፉት አራት የዓለም ዋንጫዎች ጋር እኩል እንደሆነ በመጥቀስ የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ እጅግ በካዩ መሆኑን ገልጸዋል።
በአውሮፓውያኑ 2023 የስዊትዘርላንድ ተቆጣጣሪ ተቋም እንዳለው ፊፋ የ2022 የኳታር የዓለም ዋንጫ "ከካርበን ልቀት የጸዳ" እንደሚሆን የገለጸው ሐሰት ነው።
የኳታር የዓለም ዋንጫ አነስተኛ የካርበን ልቀት እንዲኖረው እንደሚደረግ እና የካርበን ልቀት እንደሚካካስ ፊፋ ገልጿል።
ፊፋ ለስዊትዘርላንዱ ተቋም በሰጠው ምላሽ "የአየር ንብረት ለውጥ የዘመናችን አንገብጋቢ ችግር መሆኑን እናውቃለን። እያንዳንዳችን አፋጣኝ እና ዘላቂነት ያለው እርምጃ መውሰድ እንዳለብንም እናምናለን" ብሏል።
የፊፋው ፕሬዝዳንት ኢንፋንቲኖ በኳታር 64ቱንም ጨዋታዎች ተመልክተዋል።
ግጥሚያዎችን ያስተናገዱት ስምንትስ ስቴድየሞች አንዳቸው ከሌላቸው በአንድ ሰዓት ርቀት ላይ ይገኛሉ።
የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ግን አህጉርን የሚያዳርስ መሆኑ ፈታኝ ያደርገዋል።















