በኮምፒውተር ብልሽት ምክንያት ስዊትዘርላንድ የአየር ክልሏን ዘጋች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስዊትዘርላንድ በአየር ትራፊክ የመቆጣጠሪያ አገልግሎት ኮምፒውተር ላይ ባጋጠመ እክል ምክንያት ወደ ግዛቷ የሚገቡና የሚወጡ በረራዎችን አገደች።
ዛሬ ረቡዕ ጠዋት በበረራ መቆጣጠሪ ኮምፒውተር ላይ ባጋጠመ የቴክኒክ ችግር ምክንያት “ለደኅንነት ሲባል” የስዊትዘርላንድ የአየር ክልል እንዲዘጋ ተደርጓል።
በዚህም ሳቢያ አንዳንድ በረራዎች በሰሜን ጣሊያን ወደሚገኘው የሚላን አየር ማረፊያ እንዲየቀኑ ተደርጓል።
የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪው ተቋም ቃል አቀባይ ቭላዲ ባሮሳ ለአንድ የዜና ድረ ገጽ እንደተናገሩት ችግሩ በኮምፒውተር ላይ የተከሰተ እንጂ የኮምፒውተር ሥርዓታቸው በመረጃ ሰርሳሪዎች ተጠቅቶ እንዳልሆነ ገልጸው “የቴክኒክ ሙያተኞቻች ችግሩን ለመፍታት እየተረባረቡ ነው” ብለዋል።
የጄኔቫ አየር ማረፊያ እንዳለው በረራዎች ለበርካታ ሰዓታት አይኖሩም፣ ነገር ግን የአገሪቱ የአየር ክልል የሚከፈት ከሆነ በሚል ዙሪክ የሚገኘው አየር ማረፊያ ተሳፋሪዎችን እየተቀበለ ነው።
በዓለም ዙሪያ የሚደረጉ በረራዎችን እና መስመራቸውን በበይነ መረብ የሚከታተለው ‘ፍላይትራዳር’ ላይ የሚታየው ምስል፣ በምዕራብ አውሮፓ በስዊትዘርላንድ ላይ የሚደረጉ በረራዎች ከረቡዕ ማለዳ ጀምሮ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ያሳያል።
በጄኔቭ የሚገኘው የአውሮፕላን ማረፊያ በረራዎች በአጭር ጊዜ መልሰው ይጀመራሉ ብሎ እየጠበቀ ቢሆንም፣ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪው አካል እንዳለው “ተጨማሪ መግለጫ አስኪሰጥ ድረስ የአገሪቱ የአየር ክልል ዝግ ሆኖ ይቆያል” ብሏል።
በዙሪክና በሌሎች በርካታ የስዊትዘርላንድ አየር ማረፊያዎች ውስጥ አውሮፕላኖች በመንደርደሪያዎች ላይ ቆመው እየተጠባበቁ ሲሆን፣ ከውጪም ምንም አይነት አውሮፕላን ወደ አገሪቱ አይገባም።
የስዊትዘርላንድ አየር ክልል መዘጋቱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ መንገደኞችን ለመጉላላት የሚዳርገው በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ብቻ ሳይሆ፣ ከሌሎች አገራት የሚመጡትንም ጭምር ነው።
ወደ ስዊትዘርላንድ መግባት ያልቻሉ አውሮፕላኖችም ወደ አቅራቢያ አገራት አየር ማረፊያዎች ለመጓዝ ስለሚገደዱ ጫናው ሌሎችም አገራትንም መንካቱ አይቀርም ተብሏል።












