አንቶኒ ብሊንከን የቻይና ፊኛ በአሜሪካ ሰማይ ላይ መንሳፈፉ “ሉዓላዊነትን የጣሰ ነው” አሉ

ታትሟል

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን፣ ቻይና የስለላ ፊኛዋን በአሜሪካ ሰማይ ላይ እንዲንሳፈፍ ማድረጓ “ተቀባይነት የሌለው እና ኃላፊነት የጎደለው” መሆኑን ተናገሩ።

ይህንን ክስተት ተከትሎም ከፍተኛ ዲፕሎማቱ ከዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ ነው ለተባለው የአሜሪካ እና የቻይና ስብሰባ ወደ ቤይጂንግ የሚያደርጉትን ጉዞ በድንገት ሰርዘዋል።

ቻይና ቀደም ብላ “ወደ አሜሪካ የአየር ክልል የገባው ፊኛ የአየር ሁኔታን የሚያጠና የአየር መርከብ ነው” ስትል በድርጊቷ መጸጸቷን ገልጻለች።

ይህ ያጋጠመው አሜሪካ እና ቻይና ውጥረት ውስጥ ባሉበት ወቅት ነው።

አርብ ዕለት የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት (ፔንታገን) ሁለተኛው የቻይና የስለላ ፊኛ በላቲን አሜሪካ ሰማይ ላይ መታየቱን ገልጿል።

የፔንታገን ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል ፓትሪክ ራይደር፣ “ወደ ላቲን አሜሪካ የሚሻገር ፊኛ እንዳለ የሚያመላክቱ ሪፖርቶችን እያየን ነበር። አሁን ግን ይህ ሌላኛው የቻይና የስለላ ፊኛ መሆኑን ገምግመናል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ ቃል አቀባዩ ፊኛው የት እንደሚገኝ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

ብሊንከን የቻይና ግዙፍ ፊኛ በአሜሪካ የአየር ክልል ላይ መንሳፈፉን “የሉዓላዊነት ጥሰት ” ብለውታል።

“ይህ ተቀባይነት የለውም።ድርጊቱም ኃላፊነት የጎደለው ነው” ያሉ ሲሆን ድርጊቱ የተፈፀመው ለረጅም ጊዜ በታቀደው ስብሰባ ዋዜማ ላይ መሆኑ ደግሞ "እጅግ ኃላፊነት የጎደለው" ነው ብለዋል።

ከፍተኛ ዲፕሎማቱ ከቻይናው ዢ ዢንፒንግ ጋር ተገናኝተው በታይዋን ጉዳይ እንዲሁም ኮቪድ-19 ጨምሮ በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ላይ ለመምከር እሁድ እና ሰኞ በቤይጂንግ ጉብኝት ለማድረግ አቅደው ነበር።

ሐሙስ ዕለት የአሜሪካ መከላከያ ባለሥልጣናት በአሜሪካ የአየር ክልል እጅግ በራቀ ከፍታ ላይ የሚንሳፈፍ የስለላ ፊኛ እየተከታተሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ፔንታገን ፊኛው አውሮፕላኖች ከሚበሩበት ከፍታ በላይ እና በምድር ላይ ላሉ ሰዎች ወታደራዊም ሆነ አካላዊ ስጋት አለማሳየቱን የገለጸ ቢሆንም፣ በአሜሪካ ክልል መገኘቱ ግን ቁጣን ቀስቅሷል።

አርብ ዕለት ቻይና ፊኛው የእርሷ ንብረት እንደሆነና ለአየር ሁኔታ (ሜቲዮሮሎጂ] ምርመር የሚያገለግል መሆኑን እና ባጋጠመው መጥፎ የአየር ጠባይ አቅጣጫውን ስቶ ወደ አሜሪካ የገባ የሲቪል የአየር መረከብ መሆኑን አምናለች።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም፣ ባጋጠመው ክስተት መጸጸቱን እና ችግሩን ለመፍታት ከአሜሪካ ጋር እንደሚሰራ አስታውቋል።

ሆኖም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን “ቻይና ስለ ፊኛው ዓላማ ያቀረበችውን ምክንያት ቢረዳም፣ በተደረገው ግምገማ ግን ለስለላ እየዋለ ነው” ብለዋል።

ሌላ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን እንዳስታወቁት፣ ብሊንከን ወደ ቻይና የሚያደርጉት ጉዞ አሁን ላይ ቢሰረዝም ሌላ ጉዞ እንደሚታቀድ ገልጸው፣ ዋሽንግተን ስለክስተቱ በግልጽ ለመነጋገር ማቀዷንም ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ አክለውም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የአሜሪካ የአየር ክልል ስለመጣሱ የአሜሪካ የቅርብ አጋሮች እንዲያውቁት ተደርጓል ብለዋል።

የካናዳ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ፣ የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ የቻይናን አምባሳደር ጠርቶ ለቻይና ባለሥልጣናት ያለውን ጠንካራ አቋም እንደሚገልጽ አስታውቋል።

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ በበኩላቸው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “በዚህ ሰዓት ወደ ቻይና መጓዝ ትክክል አይደለም” በማለት ብሊንከን የቻይና ጉዟቸውን መሰረዛቸው ትክክል ነው ማለታቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም ፕሬዝዳንት ባይደን አርብ ዕለት ስለ አሜሪካ ምጣኔ ሃብት ንግግር ሲያደርጉ ፊኛውን የተመለከቱ ጥያቄዎችን አልተቀበሉም።

እንደ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከሆነ ፊኛው የበርካታ የኒዩክሌር ሚሳኤሎች መገኛ በሆነችው በአሜሪካዋ ግዛት ሞንታና ላይ ከመታየቱ በፊት በአላስካ እና ካናዳ ሲበር ነበር።

የአየር ኃይል ብርጋዲየር ጄኔራል ፓት ራይደር፣ አርብ ዕለት ጠዋት ፊኛው ወደ 60 ሺህ ጫማ (18 ሺህ 200 ሜትር) ከፍታ ወደ ምሥራቅ በማምራት በአህጉረ አሜሪካ መሃል ላይ ይንቀሳቀስ ነበር ብለዋል።

የካንሳስ ሴናተር ሮጀር ማርሻል በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍም፣ ፊኛው በግዛታቸው ሰሜን ምሥራቅ አካባቢ እንደሚበር አርብ ከሰዓት በኋላ አስታውቀዋል።

ጄኔራል ራይደር ጨምረውም የአሜሪካ ባለሥልጣናት ቁሱን እየተከታተሉ እና አማራጮችን እየተመለከቱ እንደሆነ ተናግረዋል።

ጄኔራሉ እንዳሉት ፊኛው በምድር ላይ ላሉ ሰዎች ወታደራዊም ሆነ አካላዊ አደጋ ስጋት አይሆንም ብለዋል።

ምንም እንኳን ተዋጊ አውሮፕላኖች በተጠንቀቅ ላይ ቢሆኑም፣ በስብርባሪው ሳቢያ አደጋ ሊከሰት ይችላል በሚል ስጋት አሜሪካ ፊኛውን መትቶ ላለመጣል መወሰኗን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።