ጋርዲዮላ ከአርሰናል ጋር የሚኖረን ጨዋታ የፍጻሜ ይሆናል አሉ

ታትሟል

የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በሊጉ ከአርሰናል ጋር የሚኖራቸው ጨዋታ የሊጉን አሸናፊ የሚለይ ነው አሉ።

ቡድናቸው ትናንት ምሽት ሌስተር ሲቲን በቀላሉ 3-1 ያሸነፈው ጋርዲዮላ፤ ከአርሰናል ጋር የሚኖረው ጨዋታ “የፍጻሜ ይሆናል” ብለዋል።

ጋርዲዮላ ቡድናቸው በአርሰናል የሚሸነፍ ከሆነ የሲቲ የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነት ጉዞ የሚያበቃለት ይሆናል ብለዋል።

በፕሪሚየር ሊጉ ሁለቱም ክለቦች 30 ጨዋታዎችን አድርገው አርሰናል በሦስት ነጥብ ከሲቲ ከፍ ብሎ ሊጉን በ73 ነጥብ እየመራ ይገኛል።

ከሊጉ ፍጻሜ በፊት 8 ጨዋታዎች ብቻ የቀሩ ሲሆን ጋርዲዮላ የሊጉ አሸናፊን ይለያል ያሉት ጨዋታ በኢትሃድ ከ10 ቀናት በኋላ ይካሄዳል።

በኢሚሬትስ አርሰናልን ያሸነፈው ሲቲ በሜዳውም የሚያደርገውን ጨዋታ ሊያሸንፍ እንደሚችል ብዙዎች ግምት ቢሰጡም ፔፕ ጋርዲዮላ ግን ለጨዋታው ትልቅ ትኩረት በመስጠት ጠንካራ ዝግጅት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ሲቲ ከፕሪሚየር ሊግ በተጨማሪ በቻምፒየንስ ሊግ እና በኤፍኤ ዋንጫ ተሳታፊ ነው።

ከቀናት በፊት በቻምፒየንስ ሊጉ ሩብ ፍጻሜ ሙኒክን 3ለ0 ያሸነፈው ሲቲ የመልስ ጨዋታውን የፊታችን ረቡዕ ለማድረግ ወደ ሙኒክ ያቀናል።

“በዚህ የውድድር ዘመን አስደናቂ አቋም አሳይተዋል (አርሰናሎች)። ብዙ ነጥብ ይጥላሉ ብዬ አላስብም ለዚህም መዘጋጀት አለብን”

“ጨዋታዎችን ማሸነፍ ግድ ይለናል። [ከአርሰናል] የምናደርገው ጨዋታ በፕሪሚየር ሊጉ የፍጻሜ ይሆናል” ብለዋል ጋርዲዮላ።

አርሰናል ዛሬ እሁድ ከሰዓት 10 ሰዓት ላይ በለንደን ስታዲየም ዌስት ሃምን ይገጥማል። መድፈኞቹ ዌስት ሃምን ማሸነፍ የሚችሉ ከሆነ ሲቲ አንድ ቀሪ ጨዋታ እየቀረው የደረጃ ሰንጠረዡን በ6 ነጥብ ልዩነት መምራት ይችላሉ።

አርሰናል እየተሳተፈ ያለው በፕሪሚየር ሊጉ ብቻ ሲሆን ቼልሲን፣ ብራይተን፣ ኒው ካስል እና ማንቸስተር ሲቲ ከሊጉ ፍጻሜ በፊት ከሚጠብቁ ተጋጣሚዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ሲቲ ደግሞ በቻምፒየንስ ሊግ እና በኤፍኤ ዋንጫ እየተሳተፈ ይገኛል። ብራይተን፣ ቼልሲ፣ አርሰናል እና ብሬንትፎርድ ደግሞ ከቀሪ ተጋጣሚዎቹ መካከል ይገኙበታል።