የሲቪክ ማኅበራት የሰላም ጥሪ ዘግይቶ ይሆን?

እጃቸውን ለፀሎት የዘረጉ አባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ከሰሞኑ ከ30 በላይ ድርጅቶች የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲቆም ለማሳሰብ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ቢያቅዱም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት የቀሩት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በርካታ ሕይወት ቀጥፏል፤ ሚሊዮኖች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አስገድዷል።

ይህ ጦርነት ሊቆም ይገባል ያሉ 35 የሲቪል ማሕበረሰብ አባላት መገናኛ ብዙኃን የሚታደሙበት መግለጫ ቢያዘጋጁም እንዳሰቡት አልሆነም።

በሰብዓዊ መብት እንዲሁም በሰላምና ምክክር ላይ የሚሠሩት ድርጅቶች ይህ መሆኑ እንዳሳዘናቸው ገልጠዋል።

ድርጅቶቹ "አስቸኳይ የሰላም ጥሪ" ብለው በሰየሙት መልዕክታቸው በተለያዩ ቦታዎች ያሉ ጦርነቶችና ግጭቶች እንዲቆሙ ይጠይቃሉ።

ይህንን መልዕክት ለማስተጋባት ሊሰጡት ያቀዱት ጋዜጣዊ መግለጫ መለዮና ሲቪል በለበሱ የፀጥታ አካላት እንደተስተጓጎለ ይናገራሉ።

ጋዜጣዊ መግለጫውን የከለከለው ማን ነው? ሲቪል ማኅበራቱ ስለሰላም ለማውራት ዘግይተዋል ለሚሉ ምን ምላሽ አላቸው?

"የአደባባይ ስብሰባ እስካልሆነ ድረስ ማሳወቅ አይጠበቅብንም"

በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል ሰላም እንዲሰፍን ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ኦባሳንጆ ሊሳካላቸው አልቻለም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተጀመሩ ጥረቶች ተሳክተው መንግሥትና የትግራይ ኃይሎች ወደ ንግግር ጠረጴዛ መምጣት ሳይችሉ ድጋሚ ወደ ከፋ ጦርነት ገብተዋል።

ይህ አሳስቦናል ያሉት 35 የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት "አስቸኳይ የሰላም ጥሪ" የሚል መግለጫ ለቅቀዋል።

ከድርጅቶቹ አንዱ የሆነው የመብቶች እና የዴሞክራሲ እድገት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር በፍቃዱ ኃይሉ "አብዛኛዎቻችን ሰብዓዊ መብቶች ላይ አተኩረን የምንሠራ ነን" ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራል።

በፈቃዱ እንደሚለው በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች፣ በርካታ ንፁሐን ዜጎች ላይ እያደረሱ ያለውን ጥቃት በመቃወም ነው የሰላም ጥሪ የቀረበው።

"ዜጎች ለዘፈቀደ ግድያ፣ ለስደት፣ ለፆታዊ ጥቃት ተዳርገዋል፤ የመንቀሳቀስ መብታቸው እንዲገደብም ሆኗል" ሲል ያክላል።

"ይህ ጉዳይ በአስቸኳይ በሰላማዊ መንገድ ካልተፈታ አገራዊ ኅልውናችን አደጋ ላይ ይወድቃል የሚል ስጋታችንን ለመግለጥ ያደረግነው ነው።"

ድርጅቶቹ ይህንን መልዕክታቸውን በሚመለከት ጳጉሜ 1 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኝ አንድ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ለመገናኛ ብዙኃን አሳውቀው በሰዓቱ ቢገኙም በደኅንነት ሰዎች መከልከላቸውን በፈቃዱ ይናገራል።

"የፀጥታ አስከባሪ ነን ያሉ ሰዎች እኛ ጋዜጣዊ መግለጫ የምንሰጥበት ሆቴል ከመድረሳችን በፊት ቀድመው ለሆቴሉ ኃላፊዎች ይህ መግለጫ መካሄድ የለበትም ብለው አስቁመውት ነው የጠበቁን።"

ዳይሬክተሩ፤ ጥሪ ደርሷቸው ሽፋን ለመስጠት የተሰበሰቡ ጋዜጠኞችም መግለጫው ወደሚሰጥበት ክፍል እንዳይገቡ ተከልክለው እንደነበርም ይናገራል።

በፈቃዱ እንደሚለው ጋዜጣዊ መግለጫው እንዳይካሄድ ክልከላ ካደረጉ ሰዎች መካከል፣ ሲቪል የለበሱ ሰዎች እንዲሁም መለዮ የለበሱ እንደነበሩ ይገልጣል።

አክሎም ጋዜጠኞች ወደ ሆቴሉ አዳራሽ እንዳይገቡ ክልከላ እንደተደረገባቸው ይናገራል።

ለመሆኑ ክልከላውን ያደረገው ማን ነው? በፈቃዱ "የከለከለን ክፍል ማን እንደሆነ እስካሁን ባናውቅም እያጣራን ነው" ይላል።

"እኔ ነኝ የከለከልኩት፤ ምክንያቴ ደግሞ ይህ ነው ያለን የመንግሥት አካል የለም። ማን ነው የከለከለን? ለምንድነው የተከለከልነው? ብለን የጠይቅናቸው የፀጥታ አካላት ‘እኛ አይካሄድም ነው የተባልነው’ ይላሉ።"

በፈቃዱ ድርጅቶቹ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ እንደሆነ ይጠቅሳል።

"የአደባባይ ስብሰባ ካልሆነ በስተቀር ማሳወቅም ሆነ ፈቃድ መጠየቅ አይጠበቅብንም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ አይደለንም።"

ዳይሬክተሩ "ድርጊቱ መጣራት አለበት። አለበለዚያ ለሲቪል ማኅበረሰቡ ምኅዳሩ እየጠበበ ነው የሚሄደው ማለት ነው" የሚል ስጋት አለው።

ድርጅቶቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች ሰላማዊ ዜጎች ላይ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ቀውስ እየፈጠረ ነው ይላሉ።

በተለይ ደግሞ በትግራይ ክልል በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ ማኅበራዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ እንዲጀምሩ ጠይቀው በጦርነት ወቅት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ያደረሱ አካላት ላይ ምርመራ ተደርጎ የተጠያቂነት እርምጃ ይወሰድ ሲሉ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

"ሐቀኛ፣ ሰላማዊና የግጭቶቹ ተሳታፊ አካላት በሙሉ ያካተተ የእርቅ ንግግር" እንዲጀመር ከሚጠይቁት ድርጅቶች መካከል አንዱ የአማራ ጋዜጠኞች ማኅበር ነው።

ለቢቢሲ ድምፃቸውን የሰጡት የማኅበሩ ዳይሬክተር አየለ አዲስ [ዶ/ር] "አሁን ያቀረብነው ጥሪ የሸምጋይነት ሚናችንን ለመወጣት ጥረት ያደረግንበት ነው" ይላሉ።

"ሁለቱም ኃይሎች የጀመሩት ጦርነት በማቆም መነጋገር አለባቸው። ዜጎች መብታቸው መከበር አለበት። ከዚህ ድል ይኖራል ተብሎ አይጠቀበም፤ ለሰላም ሲሉ እጃቸውን የሚዘረጉ ኃይሎች ናቸው አሸናፊ የሚሆኑት።"

ሲቄ የሴቶች ልማት ማኅበር [ዉሜንስ ዲቨሎፕመንት አሶሲዬሽን] የተሰኘው አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅትም የሰላም ጥሪ ካቀረቡት መካከል ነው።

የማኅበሩ መሥራችና ዳይሬክተር ዘርትሁን ተፈራ በአዲሱ ዓመት [2015] ትልቁ ተስፋችን በአገሪቱ ሰላም ወርዶ ማየት ነው ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

ዳይሬክተሯ፤ "የሴቶችና ሕፃናት መብት ተጠብቆ፤ በሰላም ወጥተን የምንገባት፤ ከቀያቸው ተፈናቅለው ያሉ፤ የተለያዩ ጉዳቶች የደረሰባቸው፤ ሁሉ ነገር ተስተካክሎላቸው፤ ድጋሚ ተቋቁመው መብታቸውና ተጠብቆ ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ ነው ፍላጎታችን" የሚል መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።

ስለ ሰላም የሚያሳይ

የፎቶው ባለመብት, CARD

የሰላም ጥሪው ዘግይቶ ይሆን?

"የአገሪቷ ጉዳይ በፖለቲካ ተፋላሚዎች እጅ ውስጥ ወድቋል። የደረሰው ኪሳራ ደግሞ [የሰላም ጥሪ ለማቅረብ] መዘግየታችን ያረጋግጣል። ነገር ግን ከሚቀር ዘግይተንም ቢሆን ጥሪ ማድረግ አስፈላጊ ነው" ይላሉ የአማራ ጋዜጠኞች ማኅበር ዳይሬክተር አየለ አዲስ።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዓለም፤ በፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው ህወሓት መካከል የጀመረው ሰላም እንዲሰፍን የጀመረው ሂደት ተቋርጦ ዳግም ጦርነት መቀስቀሱን እንዳሳዘናቸው ይገልጣሉ።

"ሁሉም ለሰላም መዘመር አለበት" የሚሉት አየለ፤ ማኅበራቸው ባለፉት አምስት ወራት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያጎለብቱ ሥራዎች ሲያከናውን እንደነበር ይናገራሉ።

የመብቶች እና የዴሞክራሲ እድገት ማዕከል ዳይሬክተር በፍቃዱ ኃይሉ በበኩሉ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥሪ ስናደርግ ነበር ይላል።

"ይህ የመጀመሪያ ጥሪያችን አይደለም። አምናም ልክ እንዲሁ ጳጉሜ ወር 24 የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት ተመሳሳይ የሰላም ጥሪ አቅርበናል። ዘንድሮ 35 ደርሰናል።"

"ዘግይቷል ብለው የሚጠይቁ ሰዎች ከራሳቸው የመከታተል ጉድለት የተከሰተ ሊሆን ይችላል" ባይ ናቸው።

በተለያዩ ጊዜዎች በተናጠልም በጋራም መግለጫዎችን ያወጡ እንደ ነበር ከጋዜጠኞች፣ ከፖለቲካ ተዋናዮችና ከሲቪል ማኅበራት ጋር አቅማቸው በፈቀደ መጠን እየሠሩ እንደሆነም ይገልጣሉ።

"መገናኛ ብዙኃን ግጭቶች ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላት የሚናገሩት ማስተጋባት ይመርጣሉ። በዚህ ምክንያት ጩኸን አልወጣን ይሆናል እንጂ ዝም አላልንም።"

በሴቶች፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች ላይ የሚሠራው ሲቄ የሴቶች ዕድገት ማኅበር ኃላፊ ዘርትሁንም በበኩላቸው "የሰላም ጥሪ ስናቀርብ ይህ የመጀመሪያችን አይደለም። ከዚህ በፊትም ድምፃችንን ስናሰማ ነበር" ይላሉ።

የአማራ ጋዜጠኞች ማኅበር፤ ለብሔራዊ የዕርቅ ኮሚሽን ግብዓት እንዲሆን ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እንደሚያካሂዱ ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።

"ሕዝቡ ሰላምን ማስቀደም እንደሚሻ ግልጽ ነው፤ በአማራ ክልል ያካሄድናቸው ውይይቶች ይሄንን ነው የሚያሳዩት፤ ጦርነት ቆሞ ወደ ሰላም እንግባ የሚል ነው ያለው።"

የሰላም ተስፋ ይኖር ይሆን ተብለው የተጠየቁት የመብቶች እና የዴሞክራሲ እድገት ማዕከል ዳይሬክተሩ በፈቃዱ ኃይሉ "ፈቃደኝነቱ ካለ፤ አዎ!" ይላሉ።

"ይህ ግላዊ አስተያየቴ ነው። ጦርነቱ ከዚህ በበለጠ የጋለበት ጊዜ ነበር። ከዚያ ዓይነት አዘቅት ወጥተን የሰላም ድርድርን እንደ አማራጭ ማየት ከቻልን፤ አሁንም ወደዚያ የማንመለስበት ሁኔታ የለም ብዬ አላምንም። ፈቃደኝነቱና የብዙኀኑ ግፊት እስካለ ድረስ ተፋላሚ ወገኖች ወደ ሰላማዊ አማራጭ ማምራታቸው አይቀርም።"