ቲክቶክ ስደተኞች ለምነው ከሚያገኙት ገንዘብ ከፍተኛ ኮሚሽን እየሰበሰበ መሆኑ ተጋለጠ

ህጻናት ለሰዓት በቀጥታ ቪዲዮ ከማሰራጨት ባለፈ አንዳንዴም ይለምናሉ
ታትሟል

በሶሪያ መጠለያዎች ውስጥ ያሉ ስደተኞች በቲክቶክ ላይ ድጋፍ እየለመኑ ከሚያገኙት ገቢ ኩባንያው እስከ 70 በመቶውን እንደሚወስድ የቢቢሲ ምርመራ አረጋገጠ።

ልጆች ወደ ገንዘብ የሚቀየሩ ዲጂታል ስጦታዎችን ለማግኘት በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ለሰዓታት በቀጥታ ስርጭት ሲማጸኑ ይቆያሉ።

ስደተኞቹ ከቀጥታ ስርጭቶቹ በሰዓት እስከ 1,000 ዶላር እንደሚያገኙ ቢቢሲ ተመልክቷል። ስደተኞቹ ኪስ የሚገባው ግን በጣም ጥቂት ነው።

ቲክቶክ "በልመና" ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግሯል።

ኩባንያው በልመና ገንዘብ መሰብሰብን እንደማይፈቅድ ገልጾ ከዲጂታል ስጦታዎች የሚቀበሉ ደርሻ ከ70 በመቶ ያነሰ ነው ቢልም ትክክለኛውን መጠን ከመግለጽ ግን ተቆጥቧል።

በፈረንጆቹ 2022 መጀመሪያ ላይ የቲክቶክ ተጠቃሚ ገጾች ከሶሪያ ካምፖች በሚገኙ የስደተኖች የቀጥታ ስርጭቶች ተሞልተው ነበር።

በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ በሚገኙ መጠለያዎች ውስጥ ይህን ሁኔታ የሚያመቻቹ ‘የቲክቶክ ደላሎች’ መኖራቸውን ቢቢሲ አረጋግጧል። ለስደተኞቹ የቀጥታ ስርጭት የሚያገለግሉ ተንቀሳቃሽ ስልክ እና ቁሳቁስ እነዚህ ደላሎች ያቀርባሉ።

ደላላዎቹ በበኩላቸው በቻይና እና በመካከለኛው ምስራቅ ከሚገኙና ከቲክቶክ ጋር ግንኙነት ካላቸው ድርጅቶች ጋር በመሥራት ስደተኞቹ የቲክቶክ አካውንት እንዲያገኙ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። እነዚህ ድርጅቶች የቀጥታ ስርጭቶችን ለማስፋት እና ተጠቃሚዎች በመተግበሪያው ላይ ተጨማሪ ጊዜ እንዲያሳልፉ ለማበረታታት ቲክቶክ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጀመረው ስትራቴጂ አካል ናቸው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቲክቶክ የሚሰራበት ሁኔታ (አልጎሪዝም) ይዘትን ይበልጥ የሚያስተዋውቀው የተጠቃሚውን የስልክ ቁጥር ጂኦግራፊያዊ አቀመጣጥ መሠረት በማድረግ ነው። በዚህም ደላላዎቹ የእንግሊዝ ሲም ካርዶችን መጠቀም እንደሚመርጡ ተናግረዋል። የዩናይትድ ኪንግደም ሰዎች በጣም ለጋሾች ናቸው ይላሉ።

ሞና አሊ አል-ካሪም እና ስድስት ሴት ልጆቿ በየቀኑ በቲክቶክ የቀጥታ ስርጭት የሚያስተላልፉ ቤተሰቦች ናቸው። በድንኳናቸው ለሰዓታት ተቀምጠው የሚያውቁትን ጥቂት የእንግሊዘኛ ሐረጎች ይደጋግማሉ። "እባክዎ የመውደድ ምልክቱን ይጫኑ፣ ያጋሩ፣ እባክዎን ስጦታ ይስጡን" የሚሉ ቃላት ይደጋገማሉ።

ሞና ባለቤቷ በአየር ድብደባ ወቅት ነው የተገደለው። የቀጥታ ስርጭቱን ተጠቅማ ማየት ለተሳናት ልጇ ሸሪፋ ቀዶ ህክምና የሚሆን ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ ትገኛለች።

የሚጠይቋቸው ስጦታዎች ምናባዊ ናቸው። ተመልካቾችን ግን እውነተኛ ገንዘብ ያስከፍላሉ። ከመተግበሪያውም በጥሬ ገንዘብ ማውጣት ይችላሉ። የቀጥታ ስርጭቱ ተመልካቾች ስጦታዎቹን ይልካሉ። ጥቂት ሳንቲሞችን ከሚያስወጡ ዲጂታል ጽጌረዳዎች እስከ 500 ዶላር ገደማ የሚያወጡ ምናባዊ አንበሶችን በስጦታ መልክ ይሰጣሉ።

ለአምስት ወራት ያህል ቢቢሲ ከሶሪያ የስደተኞች ካምፖች በቀጥታ የሚተላለፉ 30 የቲክቶክ አካውንቶችን ተከታትሏል። ለዚሁ የሚሆን የኮምፒዩተር ስለተ ቀመር አዘጋጅቶ ባገኘው መረጃ እያንዳንዱ አካውንት በሰዓት እስከ 1,000 ዶላር የሚያወጡ ዲጂታል ስጦታዎችን እንዳገኘ ያሳያል።

በካምፑ ውስጥ ያሉ ቤተሰቦች ግን በጣም ትንሽ ብቻ እያገኙ እንደሆነ ተናግረዋል ።

ቲክቶክ ከስጦታዎች ምን ያህል እንደሚያገኝ አልገለጸም። ቢቢሲ ገንዘቡ የት እንደሚገባ ለማወቅ ሙከራ አድርጓል።

በሶሪያ የሚገኝ አንድ ጋዜጠኛ በመጠለያ ጣብያ ውስጥ የሚኖር ስደተኛ መስሎ ከቲክቶክ ጋር ግንኙነት ወዳለው አንድ ኤጀንሲ ይቀርባል። አካውንት ይሰጠውና ቀጥታ ስርጭት ይጀምራል። በለንደን የሚገኙ የቢቢሲ ሠራተኞች በሌላ አካውንት 106 ዶላር የሚያወጣ የቲክ ቶክ ስጦታዎችን ላኩለት።

የቀጥታ ስርጭቱ መጨረሻ ላይ በሶሪያው አካውንት ላይ ያለው ቀሪ ሒሳብ 33 ዶላር ነበር። ቲክቶክ ከስጦታዎቹ ዋጋ 69 በመቶውን ወስዷል።

የቲክቶክ ተፅዕኖ ፈጣሪው እና የቀድሞው የራግቢ ተጫዋች ኪት ሜሰን በአንድ ቤተሰብ የቀጥታ ስርጭት ወቅት 330 ዶላር ለገሰ። አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮቹም በተመሳሳይ አንዲለግሱ አበረታቷቸዋል።

አብዛኛው ገንዘብ በማህበራዊ ድር አምባው ኩባንያ እንደሚወሰድ ከቢቢሲ ሲነገረው በሶሪያ ውስጥ ላሉ ቤተሰቦች ላይ የሚደረግ "አስገራሚ" እና "ፍትሃዊ ያልሆነ" ነገር ነው ብሏል።

"ግልጽነት ሊኖር ይገባል። ለእኔ ይህ በጣም ስግብግብነት ነው። ስግብግብነት” ብሏል።

ከቢቢሲ 106 ዶላር ስጦታ የቀረው 33 ዶላሩ ነው ብለናል። ይህን ገንዘብ ሲቀበሉ የሃገር ውስጥ የገንዘብ አስተላላፊዎች ደግሞ 10 በመቶ ይቀንሳሉ። የቲክ ቶክ ደላላዎቹ ደግሞ 35 በመቶውን ይወስዳሉ። ከዚህ ሁሉ በኋላ የስደተኛ ቤተሰቦቹ 19 ዶላር ብቻ ያገኛሉ።

በካምፑ ውስጥ ከሚገኙ የቲክ ቶክ ደላላዎች አንዱ የሆነው ሃሚድ ከብቶቹን ሸጧል። በገንዘቡ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ሲም ካርድ እና ዋይ ፋይ ገዝቷል። ይህንንም የቀጥታ ስርጭት ከሚያሰራጩ ቤተሰቦች ጋር ይሠራበታል።  

አሁን በቀን ለበርካታ ሰዓታት ከ12 የተለያዩ ቤተሰቦች ጋር ይሠራል።

ሃሚድ እነዚህ ቤተሰቦች ለመተዳደሪያ የሚሆን ገቢ እንዲያገኙ ለመርዳት ቲክቶክን እንደሚጠቀም ይሞግታል። የራሱን ኮሚሽን ቀንሶ አብዛኛውን ገቢ እንደሚከፍላቸውም ገልጿል።

ቻይና ውስጥ በቀጥታ ከቲክቶክ ጋር የሚሠሩ “ኤጀንሲዎች” ይደግፉናል ሲል ሃሚድም ሌሎችን ደላላዎች ሃሳብ ይጋራል።

"በመተግበሪያው ላይ ችግር ካጋጠመን ይረዱናል። የታገዱ አካውንቶችን ያስከፍታሉ። የአካውንቱን ስም እና ምስል ስንሰጣቸው አካውንቱን ይከፍታሉ" ሲል ሃሚድ ያስረዳል።

“የቀጥታ ስርጭት አጋዥ ” በመባል የሚታወቁት እነዚህ ኤጀንሲዎች በመላው ዓለም ይገኛሉ። ተጠቃሚዎች ይበልጥ ማራኪ የቀጥታ ስርጭቶችን እንዲያዘጋጁ ለመርዳት ከቲክቶክ ጋር የተስማሙ ናቸው።

ቲክ ቶክ በቀጥታ ስርጭት የቆይታ ጊዜ እና በተቀበሉት ስጦታዎች ዋጋ መሠረት ኮሚሽን ይከፍላቸዋል ሲሉ ኤጀንሲዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የቆይታ ጊዜውን ለማሳደግ በሶሪያ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ ህጻናትን ጨምሮ ሌሎችም ቲክቶክ ላይ ለሰዓታት ይጣዳሉ።

የዲጂታል መብቶች ድርጅት አክሰስ ናው ባለደረባ የሆኑት ማርዋ ፋፍታታ እነዚህ የቀጥታ ስርጭቶች  ከቲኪ ቶክ ፖሊሲዎች ጋር የሚቃረኑ ናቸው ብለዋል። በተለይም ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህጻናትን “ከጉዳት፣ አደጋ ወይም ብዝበዛ መከላከል” ከሚለው ፖሊሲ ጋር ይቃረናል ይላሉ።

የቀጥታ ስርጭቱን 50 ሺህ ሰዎች ተከታትለዋል

"ቲክቶክ ተጠቃሚዎቹ በግልጽ ስጦታዎችን እንዲጠይቁ እንደማይፈቀድላቸው ይናገራል። ስለዚህ ይህ የራሱን የአገልግሎት ውሎች እና የሰዎችን መብት መጣስ ነው" ይላሉ።

ሰዎች "ድጋፍ እና ርህራሄን ለማግኘት" ታሪኮቻቸውን የማካፈል መብት እንዳላቸው ይገልጻሉ። እነዚህ የቀጥታ ስርጭቶች ግን "ክብር የሌላቸው እና የሚያዋርዱ ናቸው" ይላሉ።

የቲክቶክ የቀጥታ ስርጭት ከመጀመር በፊት 1,000 ተከታዮች ሊኖሩዎት ይገባል ይላል። ስጦታዎችን በቀጥታ መጠየቅም አይፈቀድም። ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን “ከጉዳት፣ አደጋ ወይም ብዝበዛ መከላከል” አለብዎትም ይላል።

ቢቢሲ መተግበሪያውን ተጠቅሞ ህፃናት የሚለምኑባቸውን 30 አካውንቶች ሪፖርት ቢያደርግም ቲክቶክ ፖሊሲው እንዳልተጣሰ ተናግሯል።

ቢቢሲ አስተያየት ለማግኘት በቀጥታ ቲክቶክን ካነጋገረ በኋላ ኩባንያው ሁሉንም አካውንቶች አግዷል።

በመግለጫውም “ቢቢሲ ያቀረበልን መረጃ እና ውንጀላ በጣም አሳስቦናል። ፈጣን እና ጥብቅ እርምጃም ወስደናል” ብሏል።

"ይህ ዓይነት ይዘት በእኛ መድረክ ላይ ፈጽሞ አይፈቀድም። በበዝባዥ ልመና ዙሪያ ዓለም አቀፋዊ ፖሊሲያችንን የበለጠ እያጠናከርን ነው።"

ቲክቶክ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበ የሚገኝ ማህበራዊ ድር አምባ ነው። ሴንሰር ታወር እንደተባለ አጥኚ ኩባንያ ከሆነ እአአ በ2017 ከተመሠረተ በኋላ 6.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል።

በቲክቶክ ቀጥታ ስርጭት ገንዘብ ማግኘትን እንደ አማራጭ ከመውሰድ  በሶሪያ ውስጥ የሚሠሩ በጎ አድራጊ ድርጅቶች በመጠለያዎች ውስጥ ያሉ ቤተሰቦችን እንዲደግፉ ቢቢሲ ጠይቋቸዋል።

ታካፉል አልሻም የተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት ልጆቹ ትምህርት እንዲያገኙ የትምህርት ወጪያቸውን በመሸፈን ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት መሠረታዊ ቁሳቁሶችን እንደሚያቀርብ ተናግሯል።

በካምፑ ውስጥ ላሉ ብዙ ቤተሰቦች ግን በቀጥታ ስርጭት ከመለመን ውጪ ገንዘብ የማግኛ ጥቂት አማራጮች ነው ያላቸው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች በየቀኑ በቀጥታ ስርጭት መቅርባቸውን ቀጥለዋል። ከተለገሰው ገንዘብ አብዛኛውም ቲክቶክ መግባቱን ቀጥሏል።