ሴሊን ዲዮን ካጋጠማት እምብዛም ከማይታወቀው ህመሟ አገግማ ወደ ሙዚቃ ልትመለስ ነው

ሴሊን ዲዮን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    • ፀሐፊ, ኤማ ቫርዲ
    • የሥራ ድርሻ, ሪፖርተር
  • ታትሟል

ከላስ ቬጋስ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኙት ቅንጡ መኖሪያ ቤቶች ከአንዱ ለጆሮ አዲስ ያልሆነች ድምጻዊት ዘፈን ይሰማል።

“ሴሊን ዲዮን ነች?” ስል ጠየቀኩ።

ከጠባቂዎቹ አንዱ ጭንቅላቱን በመነቅነቅ “አዎ” የሚል ምላሽ ሰጠኝ።

ከመንደሩ የተገኘሁት በሙዚቃ ዓለም ትልቅ ዝናን ካተረፈችው ሴሊን ዲዮን ጋር ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ነው።

ሴሊን ከጥቂት ወራት በፊት በጤና እክል ምክንያት ከሙዚቃው እራሷን እንደምታርቅ ገልጻ ነበር።

ሴሊን ዲዮን በኢንስታግራም ገጿ ያጋራችው “መርዶ” በበርካታ አድናቂዎቿ ዘንድ ያን ስርቅርቅ ድምጿን መልሰው ላይሰሙት እንደሚችሉ ስጋት አሳድሮባቸው ነበር።

“በብዙ ሰዎች ላይ የማይከሰት የነርቭ ህመም ገጥሞኛል” ስትል ተናግራ ነበር።

ድምጻዊቷ ያጋጠማትን የጤና ዕክል ተከትሎ በዕቅድ ተይዘው የነበሩ በርካታ ኮንሰርቶቿን ለመሰረዝ ተገዳ ነበር።

ሴሊን ዲዮን ከልጆቿ በመድረክ ላይ እንዲሁም ከሟቹ ባሏ ጋር የተነሳችው ፎቶ ከጀርባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሴሊን ዲዮን ከልጆቿ በመድረክ ላይ እንዲሁም ከሟቹ ባሏ ጋር የተነሳችው ፎቶ ከጀርባ

ከሴሊን ጋር ለማወራት እንደተቀመጠን ከምትወደው መድረክ አርቋት የቆየው ህመም ሳይታወቅ ለበርካታ ጊዜያት አብሯት መኖሩን ነግራኛለች።

የ56 ዓመቷ ድምጻዊት በጊዜ ሂደት በድምጿ ላይ ያለውን ለውጥ ካስተዋለች በኋላ ነበር ያለባት ህመም በምርመራ የተለየው።

“ድምጽ ለማውጣት ይቸግረኝ ነበር። ኃይል ለማውጣት እታገል ነበር” ብላለች ሴሊን።

ሴሊን እንደ ቀደመው ጊዜ ድምጽ ለማውጣት የተቸገረችው ከሥራ ብዛት ሰውነቷ ዝሎ እንደሆነ ነበር የምታስበው።

ድምጻዊቷ ምንም እንኳ በመድረክ ሥራዎቿ አድናቂዎቿ በድምጿ ላይ ያለውን ለውጥ ባያስተውሉትም በዕቅድ ይዛ የነበረውን የሙዚቃ ድግስ ጉዞ ለማጠናቀቅ ብዙ ጥራለች።

ሁኔታው መቋቋም ከምትችለው በላይ ሲሆንባት ለምርመራ በሄደችበት ጊዜ የተረዳችው የገጠማት ችግር ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላቂ ነገር መሆኑን ነበር።

ሴሊን ዲዮን በመድረክ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሴሊን የገጠማት ስቲፍ ፐርሰን ሲንደሮም (ኤስፒሴስ) የተባለው ህመም ብዙ ጊዜ መገለጫው በሰውነት ውስጥ ያለ ጡንቻ በራሱ ጊዜ በመኮማተር እና ታማሚውን አቅም ማሳጣት ነው።

በሽታው መድኃኒት የለውም። ይሁን እንጂ በሽታው መለየት መቻል ህመሙን ለመቆጣጠር ይረዳል።

“ዓላማዬ መድኃኒት ለማግኘት እና በሽታውን ለማሳወቅ የሚደረገውን ጥረትን ማገዝ ነው። ይህን ማድረግ መቻል በጣም አስደሳች ነው” ትላለች።

ሴሊን ከሙዚቃ ሥራዎቿ ጎን ለጎን መድኃኒቱን በአግባቡ በመውሰድ እንዲሁም ፊዚዮ ቴራፒ በመሥራት ታሳልፋለች።

የድምጻዊቷ ሐኪም የሆኑት አማንዳ ፒኬት (ዶ/ር) “አሁን ላይ ስለበሽታው ሰዎች መረጃው እየደረሳቸው ነው” ይላሉ።

ሴሊን በዚህ በሽታ ስለመያዟ በይፋ መናገሯ ሰዎች ስለበሽታው ብዙ መረጃ እንዲያገኙ እንደረዳ ዶ/ር አማንዳ ይናገራሉ።

ሐኪሟ እንደሚሉት ምንም እንኳ ሴሊን ዲዮን ቀሪ ዕድሜዋን ከህመሙ ጋር የምታሳለፍ ቢሆንም፣ እያገኘች ያለው ሕክምና ወደ ሙዚቃ ሥራዋ እንድትመለስ ያደርጋታል ብለዋል።

ሴሊን ዲዮን በ1988 በዩሮቪዥን የሙዚቃ ውድድር ላይ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሴሊን ዲዮን በ1988 በዩሮቪዥን የሙዚቃ ውድድር ላይ

የላስ ቬጋስ ኮንሰርት

“የድምጼን ጉልበት መልሼ አገኛለሁ” የምትለው ሴሊን ሲዮን፣ በላስ ቬጋስ ከተማ ለሚኖራት የሙዚቃ ድግስ ልምምድ መጀመሯን ጨምራ ገልጻለች።

ሴሊን በፈገግታ ተሞልታ “ለዚህ የሙዚቃ ድግስ በጣም ጠንክረን እየሠራን ነው። ምክንያቱም ተመልሻለሁ” ብላለች።

“በትክክል መቼ መሆኑን ባላውቅም ወደ መድረክ እመለሳለሁ። እመኑኝ ድምጼን ከፍ አድርጌ እጫወታለሁ። ያን ቀን በጉጉት እጠብቃለሁ።”

ካናዳዊቷ ድምጻዊ በአውሮፓውያኑ በ90ዎቹ ያወጣቻቸው 'ዘ ፓዎር ኦፍ ላቭ' እንዲሁም 'ኢትስ ኦል ካሚንግ ባክ ቱ ሚ ናው' የተሰኙት ሙዚቃዎቿ ዝናን እና ትልቅ አድናቆትን ካተረፉላት የሙዚቃ ሥራዎቿ መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ሴሊን ዲዮን በብዙዎች ዘንድ ተዋቂነትን ያተረፈችው እአአ 1988 ላይ በስዊትዘርላንድ የተካሄደውን የዩሮቪዥን የሙዚቃ ውድድርን ካሸነፈች በኋላ ነበር።