በጦርነት መካከል ለሽርሽር ወደ ማልዲቭስ የሄዱት የዩክሬን ፓርላማ አባል የወንጀል ምርመራ ተከፈተባቸው

ታትሟል

የዩክሬን ባለሥልጣናት አንድ የፓርላማ አባል ቤተሰባቸውን ይዘው ለሽርሽር ወደ ማልዲቭስ በመሄዳቸው ምርመራ እንዲካሄድ አዘዙ።

በዩክሬን ባለሥልጣናት ወደ ውጭ ሃገር ለሽርሽር መሄድ አይችሉም። ለወታደራዊ ግዳጅ የበቁ ወንዶች ደግሞ ለመውጣት ልዩ ፈቃድ ያሻቸዋል።

ዩሪይ አሪስቶቭ የተባሉት የፓርላማ አባል ሐሰተኛ መረጃ ሰጥተው ይሆን ወይ የሚለው እየተጣራ ነው።

መርማሪዎች እንደሚሉት እንደራሴው ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የሶስት ዓመት እሥር ይጠብቃቸዋል።

ኤስቢአይ የተሰኘው የምርመራ ቢሮና የዩክሬን ሴኪዩሪቲ ሰርቪስ ናቸው ግለሰቡ ከሃገር ለመውጣት ሲሉ ሐሰተኛ መረጃ ሰጥተው እንደሆን እያጣሩ ያሉት።

የኤስቢአይ ምርመራ እንደሚያሳየው ሰውየው ማልዲቭስ ወደ ሚገኘው ኢራፉሺ የተባለ የግል ደሴት ከሚስታቸውና ከልጆቻቸው ጋር ሐምሌ አጋማሽ ሄደዋል።

በወቅቱ ሕመም ላይ መሆናቸው ተነገሮ የሕክምና እረፍት ላይ ነበሩ።

ለ17 ቀናት ያክል ከሃገር ወጥተው የከረሙት አሪስቶቭ መጀመሪያ የሶስት ቀናት ኦፊሴላዊ የሥራ ጉዞ ለማድረግ ወደ ፓላንድ ነበር የበረሩት።

ማልዲቭስ ውስጥ ሲዝናኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የታዩት በዩክሬን መገናኛ ብዙሃን አማካይነት ነው።

የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ባለፈው ማክሰኞ ባሰሙት ንግግር የመንግሥት ሠራተኞች የሃገራቸውን ጥቅም የማያስቀድሙ ከሆነ “ቁጣ” ይደርስባቸዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

“በተዋጊዎቻችን፣ በሕዝባችን አማካይነት የመጣውን የዩክሬን ሞራል ጥንካሬ ስትመለከቱ ምን ያክል የሚቻለውንም የማይቻለውንም አድርገን ድል ለማምጣት፤ ነፃነት ለመቀዳጀት እንዳለምን ያሳያል። ከዩክሬን ጥቅም በፊት የትኛውም ውሳጣዊ ክህደት፤ የትኛውም ‘ሽርሽር’፤ ማንኛውም ግላዊ እርካታ መጨረሻው ቁጣ ነው” ብለዋል።

የፓርላማ አባሉ አሪስቶቭ የሥር መልቀቂያ ደብዳቤ ያስገቡ ሲሆን ምክር ቤቱ ቀጣይ ሲሰበሰብ እንደሚመክርበት አፈ-ጉባዔው ረስላን ስቴፋንቹክ በፌስቡክ ገፃቸው ገልጸዋል።

በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መጀረመሪያ ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ በመንግሥታቸው ያሉ ባለሥልጣናትን ሥፍራ ከቀያየሩ በኋላ በርካቶች መንበራቸውን ለቀዋል።