“የክሪፕቶ ንግሥቷን” ለጠቆመ የሚሰጠው የሽልማት መጠን ወደ 5 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ተደረገ

ታትሟል

“የክሪፕቶ ንግሥት” ተብላ የምትጠራውን ሩጃ ኢግናቶቫን መያዝ የሚያስችል መረጃ ለጠቆመ የሚሰጠው ሽልማት ወደ 5 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ተደረገ።

ትውልደ ቡልጋሪያዊት እና የጀርመን ዜግነት ያላት እና ‘ዋንኮይን’ በተሰኘ ክሪፕቶከረንሲ የማጭበርበር ወንጀል 4.5 ቢሊዮን ዶላር ይዛ እንደተሰወረች ይታመናል።

የአሜሪካ ስለላ ተቋም (ኤፍቢአይ) የ44 ዓመቷን ሴት ለመያዝ ፍለጋ ሲያደርግ ቆይቷል።

ግለሰቧ ከእአአ 2017 ጀምሮ የገባችበት አይታቅም።

ዶ/ር ሩጃ ኢግናቶቫ 'ዋንኮይን' በተባለ ክሪፕቶከረንሲዋ ዓለም አቀፍ ዝናን አትርፋ ነበር። ቢልየነሮች በክሪፕቶከረንሲዋ ላይ ሃብታቸውን እንዲያፈሱ አሳምናም ነበር። በመጨረሻ አድራሻዋን ስታጠፈ ዶ/ር ሩጃ አጭበርባሪ እንደሆነች ተደረሰባት።

በማጭበርበር እና ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ በማስመሰል ወንጀሎች አሁንም ትፈለጋለች።

ከሦስት ሳምንታት በፊት ዶ/ር ኢግናቶቫ ከቡልጋሪያ የማፊያ ቡድን መሪ ጋር ስላላት ግንኙነት እንዲሁም የክሪፕቶ ንግሥቷ በማፊያ ቡድኑ ተገድላ ሊሆን እንደሚችል ቢቢሲ በሠራው ዘገባ አመልክቶ ነበር።

ይሁን እንጂ ፖሊስ ኢግናቶቫን አድኖ ለመያዝ የሚያደርገውን ጥረት አላቋረጠም።

እአአ 2022 ላይ ኤፍቢአይ በጥብቅ ከሚፈልጋቸው 10 ሰዎች መካከልም ኢግናቶቫን አካትቶ ነበር።

ቀደም ሲል ግለሰቧን ለመያዝ መረጃ ለጠቆመ 100 ሺህ ዶላር ሽልማት ይበረከታል ተብሎ ነበር። ትንሽ ቆይቶ የሽልማት መጠኑ ወደ 250 ሺህ ዶላር ከፍ ያለ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ኤፍቢአይ የ5 ሚሊዮን ወሮታ እከፍላለሁ ብሏል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ “የክሪፕቶ ንግሥት ተብላ የምትታወቀውን ጀርመናዊት ሩጃ ኢግናቶቫ በዓለም አቀፍ ደረጃ በታሪክ ትልቁ የማጭበርበር ስራዋ በቁጥጥር ስር ለማዋል ወይም በፍርድ ቤት ጥፋተኛ እንድትባል የሚያስችል መረጃ ለሚጠቁም 5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እንሰጣለን” ብሏል

በአሁኑ ወቀት ኢግናቶቫ በአሜሪካ ድንበር ተሻጋሪ የተደራጀ ቡድን ቢሮ የምትፈለግ ብቸኛዋ ሴት ነች።

ከኢግናቶቫ ውጪ አሜሪካ የተደራጀ የወንጀለኛ ቡድን መሪ ነው የተባለውን አየርላንዳዊ ዳንኤል ኪናሃን ለጠቆመ የ5 ሚሊዮን ዶለር እሰጣለሁ ብላለች።

ኢግናቶቫ በሌለችበት በጀርመን ክስ ተመስርቶባታል። በቡልጋሪ ያሉ ባለስልጣናትም የክሪፕቶ ንግሥቷ በሌለችበት ክስ ይመሰረትባታል ብለዋል።

ከሳምንታት በፊት በሩጃ ኢግናቶቫ ላይ ለቢቢሲ ዘገባ የሰራው ጄሚ ባርትሌት የአሜሪካ መንግሥት የሽልማት መጠኑን ከፍ ያደገው፤ ኢግናቶቫን ለመከላከል መረጃ ከመስጠት የሚቆጠቡ ሰዎችን ለመፈታተን ነው ይላል።

“ኤፍቢአይ አሁን ትኩረቱ ለዶ/ር ሩጃ ቅርበት ያላቸውን ሰዎች መረጃ እንዲሰጡ ማድረግ ነው” ብሏል።

“100 ሺህ ዶላር የወንጀለኛ ቡድን አባልን ብዙም አያጓጓውም። ከጥቅሙ ይልቅ አደጋው ያመዝናል። 5 ሚሊዮን ዶላር ግን መረጃ እንዲሰጡ ይገፋፋል” በማለት ምናልባት የኤፍቢአይ ዘዴ የሚሳካ ከሆነ ውጤቱ በጥቂት ሳምንታት ልንመለከት እንችላለን ብሏል።