የአውሮፓ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ግምት

ታትሟል

በአውሮፓ ዋንጫ ላይ ሲሳተፉ ከነበሩ 24 ቡድኖች መካከል 8ቱ በጊዜ ተሸኝተዋል።

የትኞቹ ቡድኖች በርሊን ላይ ለሚደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ይደርሳሉ?

ቀሪዎቹ 16 ቡድኖች ከነገ ጀምሮ በጥሎ ማለፉ ይገናኛሉ።

የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን የ16ቱን ቡድኖች ጨዋታ ውጤት እንደሚከተለው ገምቷል።

ቅዳሜ

ስዊትዘርላንድ ከ ጣሊያን

በዚህ ጨዋታ ጣሊያን እንደምታሸንፍ እገምታለሁ።

ያለፈው የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊ ከመሆናቸውም በላይ በክሮሽያ ላለመሸነፍ ያደረጉት ጥረት ፍሬ አፍርቶ ለጥሎ ማለፉ በቅተዋል።

ጨዋታው ተመጣጣኝ እንደሚሆን ብገምትም ጣሊያን ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ይሳናታል ብዬ አላስብም።

ግምት፡ 0 - 1

ጀርመን ከ ዴንማርክ

ጀርመን በስኮትላንድ እና ሃነጋሪ ላይ ጥንካሬዋን ብታሳይም ከስዊትዘርላንድ ጋር የነበራት ጨዋታው ከብዷት ታይቷል።

ጆናታን ታህ በቅጣት ስለማይሰለፍ በሦስቱም ጨዋታዎች ተመሳሳይ ቡድን ይዘው የገቡት ጀርመኖች አሰላለፋቸውን ለመቀየር ይገደዳሉ።

ዴንማርኮች በደንብ የተደራጁ መሆናቸውን ከእንግሊዝ ጋር ሲጫወቱ ተመልክተናል።

ጀርመኖች በርካታ የማጥቃት አማራጮች ስላላቸው ይህንን ጨዋታ እንደሚያሸንፉ እገምታለሁ።

ግምት፡ 2 - 0

እሑድ

እንግሊዝ ከ ስሎቫኪያ

እንግሊዝ ጥሩ ባትጫወትም ከምድቧ ቀዳሚ ሆኗ ማጠናቀቅ ዕቅዷ ነበር።

እንግሊዝ እየተጠነከረች መሄድ እንዳለባት እና ይህንን ጨዋታም ማሸነፍ እንደሚኖርባት እናውቃለን።

ስሎቫኪያ የተደራጀ ቡድን ቢሆንም እንግሊዝ ቀድማ ግብ ካስቆጠረች ጨዋታው ይቀላታል።

ሳውዝ ጌት በአማካይ ስፍራ ላይ በኮኖር ካላገር ምትክ ኮቢ ማይኑን እንደሚያሰልፍ እጠብቃለሁ። ከዚህ በተጨማሪ ኮል ፓልመር በቋሚነት እንዲሰለፍ እመርጣለሁ።

ግምት፡ 2 - 0

ስፔን ከ ጆርጂያ

ጆርጂያ እስካሁን ባደረገችው ጉዞ ወድጄዋለሁ።

ጆርጂያ እንደ ቡድን በመጫወት፣ ለኳስ ቁጥጥር ትኩረት ባለመስጠት በፈጣን ሽግግር መጫወትን መርጠዋል።

ይሁን እንጂ እስካሁን በምድብ ጨዋታዎች ካየናቸው ኮከብ የሆነውን ቡድን ነው የሚገጥሙት።

ስፔን ከኋላ መስመር እስከ አጥቂ ድረስ በደንብ የተደራጀ ቡድን ነው።

ግምት፡ 3 - 1

ሰኞ

ፈረንሳይ ከ ቤልጂዬም

ቤልጂዬም እያሳየችው ባለችው አቋም ምክንያት አሰልጠኟ ዶመኒኮ ቴዴስኮ ትችት እያስተናገዱ ነው።

ፈረንሳይም እንደተጠበቀችው ሳትሆን አሰልቺ ጨዋታ ከመጫወት ባለፈ ምድቧን በሁለተኛነት ለማጠናቀቅ ተገዳለች።

ፈረንሳይ ውድድሮችን ቀዝቀዝ ብለው የመጀመር ልምድ ያላቸው ሲሆን ዋንጫውን እንደሚያነሱ ያለኝን ግምት አለወጥኩም።

ግምት፡ 1 - 0

ፖርቹጋል ከ ስሎቬንያ

ፖርቹጋል የቀድሞው ክርስቲያኖ ሮናልዶን ባለመሆኑ ቡድኑ በእሱ አጨዋወት እንዲንቀሳቀስ ሆኗል።

ስሎቫንያዎች ከእንግሊዝ ጋር እንዳደረጉት በ4-4-2 የሚጫወቱ ከሆነ ለሮናልዶ የሚመቸው ይሆናል።

ስሎቫንያ የተደራጀ ቡድን ቢኖራትም ፖርቹጋል በግል እንዲሁም በቡድን ውጤት የሚቀይሩ ተጫዋቾችን ይዛለች። ስለዚህም ፖርቹጋል ይህን ጨዋታ ታሸንፋለች።

ግምት፡ 3 - 0

ሮማንያ ከ ኔዘርላንድስ

ሜምፊስ ዴፓይ ቡድኑን ወደ ሩብ ፍጻሜ እንደሚመራው ከውድድሩ በፊት ብገምትም ኔዘርላንድስ እስካሁን አሳማኝ አልሆነችም።

ኔዘርላንድስ የማትገመት ከመሆኗም በላይ ምድቧን በሦስተኛነት ነው ያጠናቀቀችው።

ሮማንያ ደግሞ ሳትገመት ምድቧን በመምራት ለዚህ ብትበቃም ይህ የመጨረሻ ጨዋታዋ ይሆናል።

ግምት፡ 1 - 3

ኦስትሪያ ከ ቱርክ

ከጠንካራው ምድብ ፈረንሳይን እና ኔዘርላንድስን ቀድመው አንደኛ በመሆን ያጠናቀቁት ኦስትሪያዎች የትኛውንም ፈተና ማለፍ እንደሚችሉ ይገምታሉ።

ቱርክ አስደናቂ ቡድን ከመሆኗ ባለፈ በርካታ ደጋፊዎች አሏት።

ጥሩ ተጫዋቾች እና ድንቅ ጎሎችን ቢያስቆጥሩ የኦስትሪያን ፍጥነት እና አደረጃጀት የሚቋቋሙ አይመስለኝም።

ግምት፡ 3 - 1