ማንቸስተር ዩናይትድ ከቶተንሀም - ቁጥሮች ምን ይላሉ? የሰቱን ግምትስ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የስድስተኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተጠባቂ ጨዋታ ማንቸስተር ዩናይትድ ከቶተንሀም የሚያደርጉት ነው።
የዩናይትዱ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ተጫዋቾቻቸው ዝግጁ እንደሆኑ ጠቅሰው የጉዳት ስጋት እንደሌለባቸው ተናግረዋል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ባለፈው ረቡዕ በአውሮፓ ሊግ በሜዳው ኤፍሲ ትዌንቴን አስተናግዶ 1 አቻ መውጣቱ ይታወሳል። ጉዳት ላይ የነበረው ሜሰን ማውንት በዚህ ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት ወደ ሜዳ መመለሱን አሳይቷል።
ሉክ ሾው እና ታይለር ማላሲያ እንዲሁም ሊንዴሎፍ እና አዲስ ፈራሚው ሌኒ ዮሮ አሁንም ሙሉ በሙሉ አላገገሙም።
በቶተንሀም በኩል አምበሉ ሶን ሂዩንግ-ሚን ይሰለፋል ወይ የሚለው ጥያቄ ገና ምላሽ አላገኘም። አሰልጣኝ አንግ ፖስቴኮግሉ ውሳኔውን ጨዋታው ሲቃረብ እናሳውቃለን ብለዋል።
የእርስ በርስ ግንኙነት
በአውሮፓውያኑ 2021 እና 2022 ማንቸስተር ዩናይትድ ከቶተንሀም ጋር ያደረጋቸውን አራቱንም ጨዋታዎች አሸንፏል። ቀጥሎ ባሉት ሶስት ጨዋታዎች ግን አንድ አሸንፎ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይቷል።
ስፐርስ ወደ ኦልድ ትራፈርድ መጥቶ 24 ጊዜ ተሸንፏል። አራት ጊዜ ድል ሲቀናው አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል። ከአንድ ተቀናቃኝ ተደጋጋሚ ሸንፈት በማስተናገድ ከስፐርስ የሚቀድመው ኤቨርተን ብቻ ነው።
ስፐርስ ወደ ኦልድ ትራፈርድ መጥቶ ብዙ ድል የቀናው ባለፉት 12 ጨዋታዎች ነው። ባለፉት 12 የኦልድ ትራፈርድ ጨዋታዎች 4 ጊዜ ሲያሸንፍ፣ 1 አንድ አቻ፣ 7 ጊዜ ደግሞ ሽንፈት አጣጥሟል።

ዩናይትድ በእሑዱ ጨዋታ ከተሸነፈ በታሪኩ ለአራተኛ ጊዜ ከመጀመሪያዎቹ ስድስት ጨዋታዎች በሶስቱ ተሸነፈ የሚል ታሪክ ይፃፍበታል።
ቀያይ ሰይጣኖቹ ከነሐሤ 2022 እስከ ነሐሤ 2023 በሜዳቸው ባደረጓቸው 20 ጨዋታዎች አንድ ጨዋታ አልተሸነፉም ነበር። ነገር ግን ከዚያ በኋላ ካደረጓቸው 19 ግጥሚያዎች በሰባቱ ተረትተዋል።
ምንም እንኳ ብሩኖ ፈርናንዴዝ በያዝነው የፕሪሚዬር ሊጉ ዘመን 17 ዒላማቸውን የጠበቁ ኳሶች በመሞከር ከሊጉ አንደኛ ቢሆንም ጎል ማስቆጠር ተስኖታል።
ማርከስ ራሽፈርድ ቶተንሀም ላይ ስድስት ጎሎች አስቆጥሯል። በእግር ኳስ ዘመኑ በርካታ ጎሎች ያስቆጠረው ሌስተር ላይ ሲሆን የጎሎቹ ብዛት 8 ነው።
ቶተንሀም ከኅዳር 2023 በኋላ ከሜዳቸው ውጭ ሶስት ጊዜ ብቻ ነው ድል የቀናቸው። ይህ አሀዝ ቡድኑን ትችት ላይ የጣለ ነው።
ስፐርስ በዛሬው ጨዋታ ድል ከቀናው ካለፈው መጋቢት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከታታይ 3 ነጥብ ሊሰበሰብ ይችላል።
የሱተን ግምት
ማንቸስተር ዩናይትድ ከኤፍሲ ትዌንቴ ጋር አቻ በመለያየቱ ትችቶች እየተሰነዘሩበት ነው የሚለው የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱተን ነው።
ስፐርስም በተቃራኒ ቡድን ጎል ፊት ያለውን ድክመት ማረም ይኖርበታል ሲል አስተያቱን ይሰጣል።
የኤሪክ ቴን ሀግ ቡድን እንደስፐርስ ያለ አጨዋወት ለሚከተለው የመልሶ ማጥቃት ስለሚመቸው ይህንን ጨዋታ ያሸንፋል ይላል ሱተን።
ቢሆንም ስፐርስን ስለማሸነፋቸው ግን እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
እንደ ሱተን ትንታኔ የማንቸስተር የአማካይ ክፍል አሳሳቢ ነው። ክርሲቲያን ኤሪክሰን ድንቅ ተጫዋች ቢሆንም እንደቀድሞው ተሯሩጦ ለመጫወት አለመቻሉ ተደጋግሞ ታይቷል።
የሱተን ግምት፡ 2 – 1
በሌሎች የፕሪሚዬር ሊጉ ጨዋታዎች ቅዳሜ ከሰዓት የተገናኙት ኒውካስል ዩናይትድ እና ማንቸስተር ሲቲ 1 አቻ ተለያይተዋል።
አርሰናል በሜዳው ሌስተር ሲቲን አስናግዶ 4-2 ሲረታ፤ ሊቨርፑል ደግሞ ወደ ዎልቭስ ተጉዞ 2-1 በመርታት የሊጉ መሪ ሆኖ ተመልሷል።












