የቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር ፎቶ ላይ የተኮሰው የቀድሞ ወታደር ታሰረ

ታትሟል

የቀድሞ የቤልጂየም ወታደር የሽብር ጥቃት በማቀነባበር ተጠርጥሮ ኖርዌይ ውስጥ ታሰረ።

የቀድሞው ወታደር የቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ዴ ክሮ ፎቶ ላይ ጥይት ሲተኩስ የሚያሳይ ቪድዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ተለቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ክስተት ምክንያት ያቀዱትን ሕዝባዊ መሰናዶ ባይሰርዙም ፖሊስ የተጠርጣሪውን ቤት ፈትሿል።

ቪድዮው ጥቁር የለበሰ ግለሰብ ጫካ ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶ ላይ ሲተኩስ አሳይቷል።

ይህ ግለሰብ ሳም ኤች የተባለ የቀድሞ ወታደር መሆኑ ተደርሶበታል።

ከቪድዮው ጋር የተያያዘው ጽሑፍ የቤልጂየም መንግሥት ሥልጣን መልቀቅ እንዳለበትና ካለቀቀ “ደም እንደሚፈስ” እንደሚገልጽ ተዘግቧል።

የቤልጂየም መከላከያ ሚኒስትር ሉድቪኒ ዴድንደር እንዳሉት የ29 ዓመቱ የቀድሞ ወታደር ከወታደራዊ አገልግሎት የተባረረው ከወንጀል ቡድን ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ ስለታመነ ሲሆን ክትትልም እየተደረገበት ቆይቷል።

አምና ግንቦት ላይ ወታደራዊ የይለፍ መታወቂያው ተሰርዟል።

ይህ ፀረ መንግሥት ቪድዮ ሲቀረጽ ግለሰቡ ኖርዌይ እንዳለና “ለመኖር ቁርጠኛ” እንደሆነ ሲናገር ይሰማል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምሥራቅ ቤልጂየም ፔፒንስተር አካባቢ ጉብኝት ሲያካሂዱ ይህ ዛቻ ተላልፏል።

“እኔ የምሰማው የደኅንነት ሠራተኞቻችንን ነው። ያደረጉት ምርመራ ምንም አስጊ ነገር እንደሌለና መጨነቅ ወይም መደበቅ እንደሌለብኝ ተናግረዋል” ሲሉም መሪው ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደምም በ2021 አክራሪ ቀኝ ዘመም ወታደሩ ጁርገን ኮኒንግ ከፍተኛ መሣሪያ ታጥቆ ስጋት ነው ተብሎ እንደነበር የቤልጄም መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በሊሙበርግ ደን ውስጥ ተጠርጣሪውን ለመያዝ ከፍተኛ ዘመቻ ተካሂዶ ከወር ፍለጋ በኋላ የግለሰቡ አስክሬን ተገኝቷል። ግለሰቡ ራሱን አጥፍቶ ነበር የተገኘው።