ናሳ ከምድር 20 ቢሊዮን ኪሎ ሜትር ርቆ ጠፍቶበት የነበረውን መንኮረኩር መልሶ አገኘ

ቮይጀር 2 ወደ ጠፈር የተላከው እአአ 1977 ላይ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, NASA

የምስሉ መግለጫ, ቮይጀር 2 ወደ ጠፈር የተላከው እአአ 1977 ላይ ነበር።
ታትሟል

ናሳ ከምድራችን 20 ቢሊዮን ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ጠፍቶብኝ ነበር ያለውን መንኮረኩር መልሶ ማግኘቱን አስታወቀ።

የአሜሪካው ግዙፉ የጠፈር ምርምር ማዕከል ከእአአ 1977 ጀምሮ ጠፈርን ሲያስስ ከነበረው መንኮራኩር ጋር የነበረው ግንኙነት መቋረጡን አስታውቆ ነበር።

ባለፈው ወር ቮይጀር-2 ወደተባለው መንኮራኩር በስህተት የተላከ ትዕዛዝ መንኮራኩሩ ከምድራችን በሁለት ዲግሪ አንቴናውን እንዲያዞር በማድረጉ ግንኙነት ተቋርጦ ናሳ መልዕክት መቀበልም ሆነ መላክ ተስኖት ቆይቷል።

ይሁን እንጂ ናሳ ትናንት ማክሰኞ በአጽናፈ ሰማይ (ዩኒቨርስ) ላይ የተለመደ ዳሰሳ እያደረገ ሳለ ከመንኮረኩሩ መልዕክት እንደደረሰው አስታውቋል።

ቮይጀር-2 አሁን ያለው የት ነው?

ቮይጀር-2 አሁን ላይ ከምድራችን 19.9 ቢሊዮን ኪሎ ሜትሮች ርቆ በከዋክብት መገኛ አካባቢ በሰዓት 55 ሺህ ኪሎ ሜትር እየበረረ ይገኛል።

ከሐምሌ 14/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ከናሳ ጋር የነበረው ግንኙነት ተቋርጦ የነበረው ቮይጀር-2 በአሁን ወቅት በናሳ ኔትወርክ ውስጥ መልሶ መግባቱ ዳግም ከመንኮራኮሩ ጋር ግንኙነት መፍጠር ይቻላል የሚል ተስፋን ፈጥሯል።

መንኮራኮሩ ከምድራችን 20 ቢሊዮን ኪሎ ሜትሮችን ርቆ መገኘቱ ከመንኮራኮሩ የወጣው መልዕክት ወደ ምድር እስኪደርስ 18 ሰዓታት ሳይወስድ አይቅርም ተብሏል።

ናሳ መልዕክቱን መቀበሉ መንኮራኮሩ አሁንም መረጃ እያሰራጨ እና “በጥሩ ሁኔታ” ላይ እንደሚገኝ የሚያሳይ ነው ብሏል።

ናሳ እስካሁን ድረስ ከመንኮራኮሩ ጋር ሙሉ ግንኙነት መፍጠር ባይችልም ቮይገር-2 በቀጣይ አንቴነው ወደ ምድር አቅጣጫ ሲሆን ዳግም ሙሉ ግንኙነት መመሥረት እችላለሁ የሚል ተሰፋን ሰንቋል።

እንደ ናሳ ገለጻ ቮይገር-2 በየዓመቱ ለበርካታ ጊዜያት ሥርዓቱን እንደ አዲስ እንዲያስጀምር ቀድሞ ተሞልቷል። ይህ ማለት መንኮራኮሩ የመቆጣጠሪያ ሥርዓቱን እንደ አዲስ ሲያስጀምር አንቴናውን ወደ መሬት አቅጣጫ ያዞራል።

መንኮራኮሩ በቀጣይ ሥርዓቱን እንደ አዲስ የሚያስጀምረው ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም. ነው።

ቮይጀር-2 የፀሐይን የውጪያዊ ሥርዓትን እንዲያጠና ነበር እአአ 1977 የተላከው። ይህ መንኮራኩር ከኔፕቱን እና ዩራኑስ ጎን የበረረ ብቸኛው መንኩራኩር ነው።