ሲንጋፖር የዩኒቨርስቲ ተማሪዋን ደፍሮ የቀረጸው ጃፓናዊን በመግረፍ እና በእስራት ልትቀጣ ነው

እስር ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የሲንጋፖር ፍርድ ቤት ከጥቂት ዓመታት በፊት የአንድ ዩኒቨርስቲ ተማሪን ደፍሮ የቀረጸው ጃፓናዊ እንዲገረፍ እና በ17 ዓመት እስራት እንዲቀጣ ፈረደበት።

በአውሮፓውያኑ 2019 የመድፈር ወንጀል የፈጸመው ጃፓናዊ ጸጉር አስተካካይ “ጭካኔ የተሞላበት” ወንጀል ፈጽሟል በሚል ነው ይህ የተበየነበት።

የ38 ዓመቱ ጸጉር አስተካካይ ኢኮ ኪታ በከተማዋ በዱላ የሚገረፍ የመጀመሪያው ጃፓናዊ ዜጋ መሆኑንም በሲንጋፖር የሚገኘው የጃፓን ኤምባሲ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ግለሰቡ 20 ጊዜ በዱላ ከተገረፈ በኋላም ለ17 ዓመት ከመንፈቅ ይታሰራል።

የግርፋት ቅጣት በሲንጋፖር ውስጥ አወዛጋቢ ቢሆን በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል የአካል ቅጣት ነው። የህዝብ መሰረተ ልማቶችን ማውደም፣ ዘረፋ እና በአደንዛዥ ዕዝ ዝውውር የተወነጀሉ ሰዎችም ይህ ቅጣት ተፈጻሚ ይሆንባቸዋል።

በፍርድ ቤት ሰነዶች መሰረት ግለሰቡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዋን ያገኘው ክላርክ ኳይ በተሰኘ ታዋቂ የምሽት ክበብ ነበር።

በወቅቱ 20 ዓመቷ የነበረችው ይህች ሴት ግለሰቡን አታውቀውም ነበር። ግለሰቡ በወቅቱ የአልኮል መጠጥ ጠጥታ የነበረችውን ተማሪ መኖሪያ ቤቱ ወስዶ ከደፈራት በኋላም በተጨማሪም ድርጊቱን በሞባይል ስልኩ ቀርጾ ለጓደኛው ልኳል።

የተደፈረችው ተማሪ ከግለሰቡ አፓርታማ ከወጣች በኋላ በዚያችው ዕለት ለፖሊስ ሪፖርት አድርጋለች። በዚያኑ ዕለት በቁጥጥር ስር የዋለው ይህ ግለሰብ በስልኩ ላይም ተማሪዋን ሲደፍር የሚያሳይ ሁለት ቪዲዮዎች ተገኝተውበታል።

ውሳኔውን ያሳለፉት ዳኛ አዲት አብዱላህ ግለሰቧ ተጋላጭ በነበረችበት እና በግልጽ መስከሯ በሚታይበት ሁኔታ እንደነበር ገልጸው ጥቃቱንም “ጭካኔ የተሞላበት” ሲሉ ገልጸውታል።

ግለሰቧ ለወሲብ መስማማቷን ምልክት ሰጥታለች በሚል በተከሳሹ በኩል የቀረበው የመከላከያ ክርክር በዳኛው ውድቅ ተደርጓል።

ብያኔው በጃፓን በስፋት የተዘገበ ሲሆን በማህበራዊ ሚዲያም በሰፊው ተጋርቷል።

አንዳንዶች በዘመናዊቷ ሲንጋፖር የግርፋት ቅጣት ተፈጻሚ መሆኑ ቢያስደነግጣቸውም አንዳንዶች መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በሲንጋፖር የዱላ ግርፋት የሚፈጸመው በጭን ጀርባ ላይ ሲሆን ይህም የማይድን ጠባሳ እስኪፈጥር ድረስ ነው።

የዱላው እርዝመት 1.5 ሜትር እና ስፋቱን ከ1̀.27 ሴንቲሜትር እንደማይበልጥ ትራንስፎርማቲቭ ጀስቲስ ኮሌክቲቭ የተሰኘ የሰብዓዊ መብቶች ቡድን ገልጿል።