ዩክሬን በሁለቱ ዓመቱ ጦርነት 31 ሺህ ወታደሮቼ ተገድለውብኛል አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሁለት ዓመት ባስቆጠረው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በአጠቃላይ 31 ሺህ ወታደሮች እንደተገደሉባት የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚይር ዘለንስኪ አስታወቁ።
ፕሬዚዳንቱ የሟቾችን አኃዝ ቢያስታውቁም በቀጣዩ ሩሲያ ለምታደርገው ወታደራዊ ዕቅድ ሊጠቅም ይችላል በሚል የቆሰሉትን ወታደሮች ቁጥር ይፋ አላደርግም ብለዋል።
በዩክሬን ባለስልጣናት ዘንድ የሟቾችን ቁጥር ይፋ ማድረግ ያልተለመደ ሲሆን ሌሎች አካላት የሚሰጧቸው ግምቶች ከዚህ በጣም ከፍ ያሉ ናቸው።
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ምዕራባውያን ለአገራቸው የሚሰጡት ዕርዳታ በመዘግየቱ ህይወት እና ግዛት እያስከፈሉ ነው ካሉ በኋላም ነው ዩክሬን የሟቾችን ቁጥር ያስታወቀችው።
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ እሁድ እለት እንደተናገሩት ሩሲያ ለጠቀሰችው የተጋነነ አኃዝ ምላሽ መሆኑንም አስታውቀዋል።
“በዚህ ጦርነት 31 ሺህ የዩክሬን ወታደሮች ሞተዋል። ፑቲን እና ዋሾ ስብስባቸው እንደሚሉት 300 ሺህ ወይም 150 ሺህ አይደለም። ነገር ግን እያንዳንዱ ያጣናቸው ሰዎች ለኛ ትልቅ ኪሳራ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
ፕሬዚዳንቱ በአጠቃላይ በጦርነቱ ውስጥ አገራቸው ስላጣቻቸው ሰዎች በተናገሩበትም ወቅት በሩስያ በተያዙ የዩክሬን ግዛቶች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ዜጎች ሞተዋል ብለዋል። ነገር ግን ትክክለኛ ቁጥራቸው እንደማይታወቅም በዚሁ ወቅት ገልጸዋል።
“ምን ያህሎቹ እንደሞቱ፣ ስንቶቹ እንደተገደሉ፣ ስንቶቹ እንደተሰቃዩም ሆነ እንደተሰደዱ አላውቅም” ብለዋል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት ከጥቂት ወራት በፊት የተገደሉ የዩክሬን ወታደሮች ቁጥር እስከ 70 ሺህ እንደሚደርስ እና የቆሰሉት 120 ሺህ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ሩሲያ 180 ሺህ ወታደሮች እንደተገደሉባት እና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እንደቆሰሉባትም በዚሁ ወቅት አስታውቀዋል።
ቢቢሲ ራሺያ ከሚዲያዞና ድረ ገጽ ጋር በጋራ በሰራው ፕሮጀክት የሞቱ ከ45 ሺህ በላይ የሩስያ ወታደሮችን ስም ያወጣ ሲሆን አጠቃላይ ቁጥሩ ከዚያ እንደሚበልጥ ይገመታል።
በየካቲት ወር የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስቴር 350 ሺህ የሩስያ ወታደሮች እንደተገደሉ ወይም እንደቆሰሉ ግምቱን አስቀምጦ ነበር።
ዩክሬን በአሁኑ ወቅት በሩሲያ በወረራ የተያዙባትን ግዛቶች ለማስመለስ የጀመረችው የጦርነት ዘመቻ የተለያዩ ሳንካዎች እየገጠሙት ነው።
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ሩስታም ኡመሮቭ እንደተናገሩትም አገራቸው እየገጠማት ያለው የአቅርቦት እጥረት ተጨማሪ ጉዳት እያደረሰባት እንደሆነ ጠቅሰው ምዕራባውያኑም እርዳታቸውን እንዲያፋጥኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።












