ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስር ቤት ውስጥ ሞቶ የተገኘው የፑቲን ተቃዋሚ እናት ልጃቸው “በሚስጥር” እንዲቀበር ጫና እየተደረገባቸው እንደሆነ ተናገሩ
በቅርቡ በሩስያ እስር ቤት ውስጥ ሞቶ የተገኘው ፖለተከኛ አሌክሲ ናቫልኒ እናት የልጃቸውን አስከሬን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ሆኖም የቀብር ስነ ስርዓቱ “በሚስጥር” እንዲፈጸም የሩስያ ባለስልጣናት ጫና እያደረጉባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
ሊዩድሚላ ናቫልናያ በቪዲዮ በተላለፈ መልዕክታቸው ወደ አስከሬን ምርመራ ሆስፒታል ተወስደው የሞት ማረጋጫ የምስክር ወረቀት ላይ መፈረማቸውንም ጠቅሰዋል።
ተቃዋሚው በተፈጥሯዊ ምክንያት መሞቱ ለእናቱ እንደተገለጸላቸው የቀድሞ የስራ ባልደረባው ተናግሯል።
የአሌክሲ ናቫልኒ ባለቤት ፖለተከኛው በሩስያ ባለስልጣናት ተገድሏል ስትል ገልጻለች።
እናቱ የልጃቸውን አስከሬን ተላልፎ እንዲሰጣቸው ህጉ ቢያዝም ባለስልጣናቱ ግን ይህንን ለማድረግ አሻፈረኝ እንዳሉ ይገልጻሉ።
ቀጥለውም ባልስልጣናቱ የልጃቸው የቀብር ስነ ስርዓት የሚፈጸምበት ሰዓት፣ ቦታ እና ሁኔታን ጨምሮ ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጠዋል ሲሉ ተናግረዋል።
“ከከተማ ወጣ ወዳለ አዲስ የመቃብር ስፍራ ‘ልጅሽ ይኼውና ሊሉኝ ይፈልጋሉ” ሲሉለም አክለዋል።
እናቱ የልጃቸውን ሞት ተከትሎ ከስድስት ቀናት በፊት ሳልኪያርድ ወደተባለችው የሩስያ ከተማ ተጉዘዋል።
ቀደም ብሎ የልጃቸውን አስከሬን እንዳያዩ የተከለከሉ ሲሆን ፕሬዝዳንት ፑቲንን ልጄን እንድቀብር ይፍቀዱልኝ ሲሉ ተማጽነው ነበር።
ትናንት ሐሙስ ባስተላለፉት መልዕክት ከሩስያ ባለስልጣናት ዛቻ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።
“አይኔን እየተመለከቱ ልጄን በሚስጥር ለመቅበር ከልተስማማው የልጄ አስከሬን ላይ አንዳች ነገር እንደሚፈጠር ነግረውኛል” ብለዋል።
ጨምረውም መርማሪዎች “ጊዜው ካንቺ ጋር አይደለም፣ አስክሬኑ እየተበላሸ ነው” እንዳሏቸው ተናግረዋል።
ቀድሞ ልጃቸው ሲጠቀምበት በነበረው የዩቲብ ቻናል በተለቀቀው በዚህ ቪዲዮ የልጃቸው አስከሬን እንዲመለስ በመጠየቅ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።
በቪዲዮው ላይ የሩስያ ባለስልጣናት ያሉት ነገር የለም።
በተያያዘ ዜና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የፖለተከኛው ባለቤት ዩሊያ እና ልጃቸውን ዳሻ ናቫልናያ ሳንፍራንሲስኮ ውስጥ አግኝተዋቸዋል።
ፕሬዝዳንቱ ፖለቲከኛው በሩስያ ሙስናን ለመታገል እንዲሁም ነጻ እና ዲሞክራሲያዊ ሩስያን ለማየት ላደረገው አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን መግለጸቸውን ኋይት ሀውስ በጽሁፍ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
በዚሁ መግለጫ አሜሪካ ሩስያ ላይ ሌላ ማዕቀብ ለመጣል እየተዘጋጀች እንደሆነም ተመላክቷል።
ሩስያዊው ፖለቲከኛ ባለፈው ሳምንት እስር ቤት ውስጥ መሞቱ ተሰምቷል። የእስር ቤቱ አስተዳደር አሌክሲ ናቫልኒ በመራመድ ላይ ሳለ ህምም አጋጥሞት መውደቁን ተናግረዋል።
ሆኖም ባለቤቱ ኡሊያ አሌክሲ ናቫልኒ የተገደለው በፑቲን ትዕዛዝ ነው ብላለች።
ሆኖም የፑቲን ጸህፈት ቤት ውንጀላውን ያጣጣለ ሲሆን የምዕራባውያን ክስ ያልተገባ ሲል አጣጥሎታል።
በአውሮፓውያኑ 2020 የቀድሞ የሩስያ የተቃዋሚ መሪ በሩስያ ሚስጥራዊ አገልግሎት ተመርዞ መገደሉ መዘገቡ ይታወሳል።