አንጀሊና ጆሊ በቀድሞ የትዳር አጋሯ ብራድ ፒት ላይ ክስ መሰረተች

አንጀሊና ጆሊ እና የቀድሞ የትዳር አጋሯ ብራድ ፒት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ዕውቋ ተዋናይት አንጀሊና ጆሊ የቀድሞ ባለቤቷ ብራድ ፒት በረራ ላይ ሳለን ሰክሮ በእኔ እና በልጆቻችን ላይ ጥቃት ሰንዝሮብን ነበር ስልት ክስ መሠረተች።

እንደ አንጀሊና ጆሊ ከሆነ ብራድ ፒት በገዛ ቤተሰቡ ላይ ይህን ጥቃት የሰነዘረው እአአ በ2016 የቤተሰቡ አባላት ከፈረንሳይ ወደ ሎስ አንጀለስ በግል አውሮፕላን ሲበሩ ነው።

ጆሊ እንደምትለው ብራድ ፒት በዚህ በረራ ላይ ጭንቅላቷን ይዞ እንደጎተታት፤ ትከሻዋን አጥብቆ ይዞ እየነቀነቀ እንደጮኸባት፣ ሁለት ልጆቻቸው ላይ ጥቃት መሰንዘሩን እንዲሁም የአልኮል መጠጥ እንደደፋባቸውም በክስ ወረቀቱ ላይ አስመዝግባለች።

ብራድ ፒት ግን ይህን ፈጽሞ አልፈጸምኩም ሲል ይከራከራል። ለብራድ ፒት ቅርበት ያላቸው ምንጮችም በአንጀሊና ጆሊ የቀረበው ክስ ሐሰተኛ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እነዚህ ምንጮች የአንጀሊና ጆሊን የክስ ታሪኮች ሐሰተኛ ክስተቶች እየተጨመሩባቸው በየጊዜው የሚቀያየሩ ናቸው ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ጆሊ እአአ 2016 በእኔ እና በልጆቼ ላይ ተፈጽሟል ያለችው ክስተት ከዚህ ቀደም በነበረ የክስ መዝገብ ላይ የተጠቀሰ ቢሆንም ዝርዝር ክስተቶችን ግን አልያዘም ነበር።

የሆሊውድ ፈርጥ የሆኑት የቀድሞ ጥንዶች በደቡብ ፈረንሳይ ባላቸው መኖሪያ ቤት እና የወይን እርሻ የድርሻ ባለቤትነት ዙሪያ ያላቸው ክርክርም በሎስ አንጀለስ ፍርድ ቤት እየተደመጠ ነው።

ጆሊ እና ፒት እአአ በ2008  ዘ ሚራቫል የሚባለውን ቅንጡ መኖሪያ ቤት እና የወይን እርሻ በ25 ሚሊዮን ዶላር ገዝተውት ነበር።

በፈረንሳይ የሚገኘው መኖሪያ  ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በፈረንሳይ የሚገኘው የጋራ መኖሪያ ቤታቸው

የአንጀሊና ጆሊ ጠበቆች ለፍርድ ቤት ባስገቡት አተታ ብራድ ፒት በወቅቱ ከ8-15 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆቻቸው እና ባለቤቱ ላይ አካላዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጥቃቶችን ሰንዝሯል ይላል።

እአአ 2016 ላይ በነበረው በረራ ላይ ተከስቷል የተባለውን ጥቃት በወቅቱ ኤፍቢአይ ምርመራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ክስ ሳይመሰረት ቀርቷል።

ባለፈው ዓመት የፍርድ ቤት ዳኛ ሁለቱ ወላጆች በጋራ ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉ ፈቅደዋል።