ሩሲያ በመላው ዩክሬን የሚሳኤል ጥቃቶችን ፈጸመች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሩሲያ የዩክሬን መዲና ኪዬቭን ጨምሮ በመላ አገሪቱ በሚገኙ ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደረጉ የሚሳኤል ጥቃቶችን ፈጸመች።
የዩክሬን ባለሥልጣናት ሞስኮ ከ50 በላይ ሚሳኤሎችን መተኮሷን ተከትሎ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የውሃ አቅርቦቶች መቋረጣቸውን አስታውቀዋል።
በመዲናዋ ኪዬቭ ሁለት ፍንዳታዎች ሪፖርት የተደረጉ ሲሆን፣ አንድ ነዋሪ በአካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን ለቢቢሲ ተናግሯል።
በሰሜን ምሥራቅ ዩክሬን በምትገኘው ኻርኪቭ ከተማ የሚገኙ የኃይል ማመንጫ ተቋማት ተመትተዋል።
ይህ የሞስኮ መጠነ ሰፊ የሚሳኤል ጥቃት የተፈጸመው ሩሲያ በጥቁር ባሕር ላይ ዩክሬን በሰው አልባ አውሮፕላን መርከቤ ላይ ጥቃት ሰንዝራለች የሚል ክስ ካሰማች በኋላ ነው።
ዛሬ ጥቅምት 21/2015 ዓ.ም. በበርካታ የዩክሬን ከተሞች የሚሳኤል ጥቃቶች ሪፖርት ተደርገዋል።
በመካከለኛ ቪንሲያ፣ በደቡብ ምሥራቅ ዩክሬን በሚገኙ ደኒፕሮፔትሮቨስክ እና ዛፖሪዢያ እንዲሁም በምዕራብ ዩክሬን በምትገኘው ሌቪቭ የሞስኮ የሚሳኤል ጥቃት ከተፈጸመባቸው ከተሞች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በዛፖሪዢያ የሚገኘ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ መመታቱም ተዘግቧል።
በመዲናዋ ኪዬቭ ደግሞ ለ350 ሺህ መኖሪያ ቤቶች የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያቀርብ ተቋም የተመታ ሲሆን፤ የተቋረጠውን አገልግሎት በፍጥነት መልሶ ለማስጀመር መሃንዲሶች መሰማራታቸው ተጠቁሟል።
በእነዚህ መጠነ ሰፊ የሚሳኤል ጥቃቶች የተጎዱ ሰዎች ስለመኖራቸው እስካሁን አልታወቅም። ሞስኮ ተጨማሪ ጥቃቶችን ልትሰነዝር ትችላለች በሚል ስጋት ነዋሪዎች እራሳቸውን ሸሽገው እንዲቆዩ ማሳሰቢያ ተላልፎላቸዋል።
የዩክሬን አየር ኃይል ቃል አቀባይ ዩሪይ ኢንሃናት ለአንድ የዩክሬን ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ፤ ሞስኮ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቿን በመጠቀም “መጠነ ሰፊ” ጥቃቶችን ፈጽማለች ብለዋል።
የዩክሬን ጦር ደግሞ ሞስኮ ሰኞ ንጋት ላይ ከተኮሰቻቸው 50 ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች መካከል 44ቱን መትቶ መጣሉን ገልጿል።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲምትሮ ኩሌባለ “በጦር አውድማዎች ላይ ከመዋጋት ይልቅ ሩሲያ ሰላማዊ ሰዎችን ትወጋለች” ብለዋል።
ሩሲያ ቀዝቃዛ የክረምት ወራት ከመግባታቸው በፊት ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶችን ስታደርስ ቆይታለች።
ሞስኮ በእነዚህ የሰው አልባ አውሮፕላን እና የሚሳኤል ጥቃቶች የዩክሬንን ሲሶ ያክል የኤሌክትሪክ ጣቢያ እና ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን አውድማለች።
ዩክሬን እና ምዕራባውያን መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ማድረግ ከጦር ወንጀል ጋር ይስተካከላል ሲሉ ቆይተዋል።
ሩሲያ አካሂዳዋለች ስለተባለው መጠነ ሰፊ ጥቃት እስካሁን በይፋ ያለችው ነገር የለም።
ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ በወደብ ከተማዋ ሴቫስቶፖል የነበረችው የሩሲያ የጦር መርከብ በሰው አልባ አውሮፕላን ጉዳት እንደደረሰባት ሞስኮ አስታውቃ ነበር።
ሩሲያ በኃይል በያዘቻት ክሬሚያ በመርከቧ ላይ ለደረሰው ጉዳት ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩክሬንን ተጠያቂ አድርጋለች።
ሞስኮ ምንም አይነት ማስረጃ ባታቀርብም መርከቧ በሰው አልባ አውሮፕላን የተመታችው በዩናይትድ ኪንግደም ጦር አባላት ሥልጠና በወሰዱ የዩክሬን ወታደሮች አማካይነት ነው ብላለች።
በመርከቧ ላይ ደረሰ ስለተባለው የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ዩክሬን ያለችው ነገር ባይኖርም፤ የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ግን በሩሲያ የቀረበው ክስ ከእውነት የራቀ ነው ብሏል።












