መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለው ታጣቂ ቡድን በአርጆ ደዴሳ ስኳር ፋብሪካ ላይ ጥቃት አደረሰ

አርጆ ስኳር ፋብሪካ

የፎቶው ባለመብት, @OdaaTarbiiWBO

ታትሟል

የፌደራሉ መንግሥት ‘ሸኔ’ ብሎ የሚጠራው እና በሽብርተኝነት የፈረጀው ቡድን በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኘው አርጆ ደዴሳ ስኳር ፋብሪካ ላይ ጥቃት ማድረሱ ተገለጸ።

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን በምሥራቅ ወለጋ ዞን የሚገኘውን ፋብሪካ ለሰዓታት ተቆጣጥሮ ከቆየ በኋላ ንብረት ማውደሙን እና ዘረፋ መፈጸሙን የስኳር ኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት እና ተሳትፎ ዋና ክፍል ኃላፊ ረታ ደመቀ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህ ጥቃት ስምንት መኪኖች በእሳት የጋዩ ሲሆን፣ ስድስቱ የአርጆ ደዴሳ ተሸከርካሪዎች ሲሆኑ፤ አንዱ ደግሞ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ሌላኛው ተሸከርካሪ ደግሞ በፋብሪካው የነበረ የኮንስትራክሽን ድርጅት መሆኑን አቶ ረታ ጨምረው ተናግረዋል።

ታጣቂ ቡድኑ ካደረሰው ጉዳት በተጨማሪ ዘረፋ መፈጸሙን አቶ ረታ ጨምረው ተናግረዋል።

“የሠራተኞችን ሞባይል፣ ጫማ ይዘው ሄደዋል። ቁጥሩ ገና እየተጣራ ያለ ላፕቶፕ እና ዴስክቶፕ ኮምፒዩተሮች ወስደዋል። ከወሰዷቸው ዕቃዎች መካከል ሃርድ ዲስክ እና ፕሪንተር እንዳለበት ከፋብሪካው ሪፖርት ደርሶናል” ብለዋል።

ታጣቂ ቡድኑ በበኩሉ 'መንግሥት የጦር ካምፕ ያደረገው' ያለውን ደዴሳ ስኳር ፋብሪካን ጥሰው መግባታቸውን ገልጿል።

የቡድኑ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት በስኳር ፋብሪካው እርምጃ መውሰዳቸውን ተከትሎ በቅጥር ግቢ ውስጥ የነበሩ የመንግሥት ኃይሎች አካባቢውን ጥለው ሸሽተዋል ብለዋል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ X ይዘት መጨረሻ

የስኳር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነቱ አርጆ ደዴሳ፣ ተቋሙ የፌደራል ተቋም መሆኑን በመግለጽ በፌደራል ፀጥታ ኃይሎች አባላት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድኑ ተቋሙን ሲጠብቁ በነበሩ የመንግሥት ፀጥታ ኃይል አባላት ላይ ጥቃት ከከፈተ በኋላ ፋብሪካውን መቆጣጠሩን ተናግረዋል።

ፋብሪካውን የሚጠብቁት “በቁጥር ውስን ናቸው። እነሱ ላይ ጥቃት ከከፈቱ በኋላ ነው ወደውስጥ የገቡት” ብለዋል።   

አቶ ረታ ከአንድ ሳምንት በፊት ማክሰኞ ነሐሴ 24/2014 ዓ.ም. በተፈጸመው በዚህ ጥቃት በሰው ላይ ስለደረሰው ጉዳት ከመናገር ተቆጥበዋል።  

ይህ ቡድን በስኳር ፋብሪካ ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከዚህ ቀደም ብሉምበርግ የተሰኘው የዜና ምንጭ ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር እያለ የሚጠራው ቡድን በፋብሪካው ላይ ባደረሰው ጥቃት የምርት ሥራውን ለማቆም ተገዷል ሲል ዘግቦ ነበር።

በወቅቱ ስኳር ኮርፖሬሽን በአካባቢው ባለው የደኅንነት እጦት ምክንያት ለፋብሪካው ግብዓት የሚሆን ነዳጅ ማቅረብ ባለመቻሉ ፋብሪካው የካቲት 2014 ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ ምርት ለማቆም ተገድዶ እንደነበር ለቢቢሲ አረጋግጧል።

ታጣቂዎቹ በአርጆ ደዴሳ ስኳር ፋብሪካ ላይ ጥቃቱን ከፈጸሙ በኋላ ከፋብሪካው አካባቢ መሄዳቸውን አቶ ረታ ጨምረው ተናግረዋል። “አሁን ፋብሪካው ሰላም ነው። ሥራቸውን እየሰሩ ነው” ብለዋል።

ከአሁን በኋላ በአርጆ ደዴሳ ፋብሪካ የሚኖረው የደኅንነት ሁኔታን ምን ያክል አሳሳቢ ነው ተብለው የተጠየቁት አቶ ረታ፤ “እኛ እንደ ተቋም ይህን መናገር አንችልም። ይሄ የፀጥታ ተቋሙን የሚመለከት ነው” ብለዋል።

አርጆ ደዴሳ ፋብሪካ በቅርቡ የፌደራሉ መንግሥት ሊሸጣቸው ለጨረታ ካወጣቸው የስኳር ፋብሪካዎች መካከል አንዱ ነው።

የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው ጨረታ አርጆ ደዴሳን ጨምሮ 8 ፋብሪካዎችን ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች መሸጥ ያስፈለገው በዘርፉ ተወዳዳሪነትን ለመጨመር እና የአገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን ለማሟላት መሆኑን ገልጾ ነበር።