የዛሬ 50 ዓመት በሞባይል የመጀመሪያውን የስልክ ጥሪ ያደረጉት ኩፐር

ማርቲን ኩፐር የመጀመሪያ ጥሪ ያደረጉበትን የሞባይል ስልክ ይዘው
የምስሉ መግለጫ, ማርቲን ኩፐር የመጀመሪያ ጥሪ ያደረጉበትን የሞባይል ስልክ ይዘው
ታትሟል

ጊዜው ከአምስት አስርት ዓመታት በፊት እንደ አውሮፓውያኑ ሚያዝያ 03/1973 ነበር።

አሜሪካዊው መሃንዲስ ማርቲን ኩፐር፣ በኒው ዮርክ ከተማ ጎዳና አንድ ጥግ ላይ ቆመው ከኪሳቸው የስልክ ቁጥር የያዘ መዝገብ አወጡ።

ከዚያም በያዙት በመጠን ትልቅ ወደ ሆነው እና ክሬም ቀለም ባለው መሣሪያ ላይ ቁጥር አስገብተው ወደ ጆሯቸው አስጠጉ።

በአጠገባቸው የሚያልፉ መንገደኞች በአግራሞት አፍጥጠው ይመለከቷቸው ነበር።

በሞባይል (ተንቀሳቃሽ ስልክ) አምራቹ ሞቶሮላ ኩባንያ መሃንድስ የሆኑት ኩፐር፣ ስልክ የመቱት ተቀናቃኛቸው ቤል ላብራቶሪስ ውስጥ ወደሚሰሩት አቻቸው ነበር።

በድል አድራጊነት ስሜትም በግል፣ በእጅ በሚያዝ እና ተንቀሳቃሽ በሆነ ስልክ እንደሚደውሉላቸው ነገሯቸው።

ይሁን እንጂ ከጥሪው ተቀባይ በኩል ምንም ምላሽ እንዳላገኙ እና ጸጥታ እንደነበር ኩፐር ያስታውሳሉ።

የ94 ዓመቱ ኩፐር በሳቅ ታጅበው “በወቅቱ በንዴት ጥርሱን እያፋጨ ነበር ብዬ አስባለሁ” ይላሉ።

ተቀናቃኛቸው ቤል ላብራቶሪስ በመኪና ላይ የሚገጠሙ ስልኮች ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ ነበር የቆየው ይላሉ ኩፐር።

“እስኪ አስቡት . . . በቤታችን እና በቢሯችን በመዳብ ገመድ ታስረን ከ100 ዓመታት በላይ አሳልፈናል። ከዚያ ደግሞ በመኪናችን ውስጥ ሊያስሩን ነበር እኮ!” ይላሉ።

ኩፐር የተጠቀመበት የሞባይል ስልክ
የምስሉ መግለጫ, የሞባይል ስልክ ሙዚየም ለገበያ የተሰራውንና ለመጀመሪያ ጊዜ ኩፐር የተጠቀሙበትን የሞቶሮላ ስልክ የራሱ አድርጎታል።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኩፐር እና ኩባንያቸው ሞቶሮላ ግን ይህ ቀጣዩ የቴክኖሎጂ መዳረሻ ነው ብለው እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም።

በውስን አካባቢያዊ የኔትወርክ ትስስር የሚሰራ ተንቀሳቃሽ ስልክ መፍጠር ችለዋል።

አሁንም ግን የመጀመሪያው የስልክ ጥሪያቸው የሰራበት መሠረታዊ ነገር ብዙም አልተቀየረም። ስልኩ የራዲዮ ሞገድ የሚፈጥረውን ድምጽን ወደ ኤሌክትሪክ ሲግናል ነው የሚቀይረው።

የራዲዮው ሞገድ ወደ ማሰራጫ ከሄደ በኋላ ማሰራጫው ድምጽን ወደሚደወልለለት ሰው ያደርሳል። ሂደቱን በመገልበጥም የተደወለለት ሰው የምትናገሩትን ይሰማል። ሳይንሱ የነበረ አሁንም ያለ ነው።

ነገር ግን አሁን ላይ ያሉት የሞባይል ስልኮች ከቀደመው የሞቶሮላ ስሪት ጋር የሚነጻጸሩ አይደሉም።

የኩፐር ምርት የሆነው ሞቶሮላ ዲይናታክ 8000X ገበያ ላይ የወጣው ኩፐር የመጀመሪያውን የስልክ ጥሪ ካደረጉ ከ11 ዓመታት በኋላ በ1984 (እአአ) ነበር።

በዛሬ ገበያ 11 ሺህ 700 ዶላር እንደሚያወጣ የሞባይል ስልክ ሙዚየምን የሚያስተዳድሩት ቤን ውድ ይናገራሉ።

ስለአገልግሎቱ ሲናገሩም “ቁጥሮቹን በመንካት መደወል ብቻ ነው። የጽሑፍ መልዕክት መላኪያ የለውም። ካሜራ የለውም። ማናገር የሚችለውም ለ30 ደቂቃ ነው። ባትሪውን ቻርጅ ለማድረግ 10 ሰዓታት ይወስዳል። ከላዩ ላይ 5 ሴንቲ ሜትር የሚረዝም አንቴና አለው።

“ክብደቱ 790 ግራም ይመዝናል። ይህም 172 ግራም የሚመዝነውን የአይፎን 14 ስልክ ከአራት እጥፍ በላይ ይሆናል” ይላሉ።

ኩፐር ምንም እንኳን የሞባይል ስልኮች አንድ ቀን ተንቀሳቃሽ፣ የተራቀቁ፣ የካሜራ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ያላቸው እንደሚሆኑ ተንብየው ባያውቁም፣ በ2023 የሞባይል ቀፎዎች ስሪት ብዙም አይደነቁም።

“አሁን ላይ ያሉ ስልኮች ብዙ የሚያስደንቁ አይደሉም። ከሚጠበቅባቸው ያነሱ ናቸው። በብዙ መልኩም ጥሩ ስልኮች አይደሉም” ይላሉ።

“አስቡት እስኪ . . . የምትፈልጉትን አገልግሎት ለማግኘት ጠፍጣፋ የሆነ የፕላስቲክ እና የመስታዋት ቁራጭ ጆሯችሁ ላይ ታስቀምጣላችሁ። በማይመች መልኩ በእጃችሁ ይዛችሁ ትቆያላችሁ። ለመጠቀምም መጀመሪያ ላይ መተግበሪያ ያስፈልጋል” ሲሉ ምክንያታቸውን ያብራራሉ።

በእርግጥ ኩፐር ወደፊት አርተፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) የስልኩ ባለቤት በሚፈልገው መልኩ መተግበሪያ ሊፈጥሩለት አሊያም ሊመርጡለት ይችላሉ ብለው ያምናሉ።

አንድ ቀን ስልኮቻችን ጤንነታችንን ሊቆጣጠሩ፣ ምርታማነታችንን ሊጨምሩ እና ሕይወታችንን ሊያሻሽሉ እንደሚችሉም ይተነብያሉ።

ከዚህም ባሻገር ጦርነትን ሊያስቀሩ ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው። “ስልኩ በራሱ ይህንን ማድረግ ባይችልም መሠረት ሊሆን ይችላል” ይላሉ።

ኩፐር ምንም እንኳን ዘመናዊ በሆኑት አቻ ስልኮች ላይ ቅሬታ ቢኖራቸውም፣ ከ50 ዓመታት በፊት በኒው ዮርክ ጎዳና አንድ ጥግ ላይ ሆነው ወደ ጆሯቸው ባስጠጉት ስልክ አሁንም ደስተኛ ይመስላሉ።

አሁንም ግን “በሞባይል ስልክ አብዮት መጀመሪያ ላይ ነው ያለነው። ገና ብዙ ይቀረናል” ብለዋል ኩፐር።