ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ ከጠቀለለቻቸው የዩክሬን ግዛቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ማስወጣት ጀመረች
ሩሲያ ህዝበ ውሳኔ በማካሄድ ወደ ግዛቷ ከጠቀለቻቸው ግዛቶች ነዋሪዎችን ማስወጣት ጀመረች።
በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች እና በሩሲያ የተሾሙ ባለስልጣናት በደቡባዊ ዩክሬን ኬርሶን ግዛት ለቀው እንዲወጡ መደረጉን በሩሲያ የተሾሙ የአካባቢው ባለስልጣን ተናግረዋል።
ይህም ዩክሬን ጥቃት ከመክፈቷ በፊት እየተከናወነ እንደሆነ የገለጹት ቭላድሚር ሳልዶ ከ50 ሺህ እስከ 60 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎችን በዲኒፐር ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ ላይ ከሚገኙ አራት ከተሞች በተደራጀና በሂደትም ለቀው እንደሚወጡ አስታውቀዋል።
ከነዋሪዎቹ በተጨማሪም በኬርሰን ከተማ ውስጥ በሩሲያ የተሾሙ ሁሉም የመምሪያ ኃላፊዎች ወንዙን ያቋርጣሉ።
የሩሲያ ቴሌቪዥን በዲኒፐር አቅራቢያ በርካታ ሰዎች ተሰባስበው አሳይቷል።
እነዚህ ነዋሪዎች ወደ ጀልባዎች ለመግባት ተሰልፈው የታዩ ሲሆን ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ በትክክል አልታወቀም።
በጦርነት በኃይል ከተቆጣጠሯቸው ግዛቶች ዜጎችን ማፈናቀልም ሆነ ወደ ሌሎች ስፍራዎች መውሰድ እንደ የጦር ወንጀል ይቆጠራል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት አማካሪ ሚካሂሎ ፖዶሊያክ ሩሲያ ኬርሶን ለመጠቅለል ህዝበ ውሳኔ ካካሄደች አንድ ወር እንኳን ሳይሞላት ይህ እየተከናወነ እንደሆነ ጠቁመዋል።
“በምናባዊ ዓለም ውስጥ የምትኖር ከሆነ እውነታው ሊጎዳ ይችላል። ብለዋል።
ሰኞ መገባደጃ ላይ በዩክሬን አዲሱ የሩሲያ ጦር አዛዥ ጄኔራል ሰርጌይ ሱሮቪኪን በክልሉ ዋና ከተማ ኬርሶን ያለውን ሁኔታ አስቸጋሪ እንደሆነ ገልፀዋል ።
በሩሲያ የተሾሙት ባለስልጣን ኪሪል ስትሪሞሶቭ የዩክሬን ሃይሎች በከተማዋ ላይ “በቅርብ ጊዜ ውስጥ” ጥቃት እንደሚሰነዝሩ የኬርሶን ነዋሪዎችን አስጠንቅቀዋል።
"ማንም ወደ ኋላ አያፈገፍግም። ነገር ግን ህይወታችሁንም ማትረፍ እንፈልጋለን ስለዚህ በተቻለ መጠን ከወንዙ ዳርቻ በግራ በኩል አቋርጡ” ሲሉም አክለዋል።
በሞስኮ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙት ሳልዶ ለሩሲያ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ማንም ሰው እጅ የመስጠት ፍላጎት እንደሌለው ገልጸው ነገር ግን ነዋሪዎች በጦርነት ቀጣና ውስጥ መቆየት አላስፈላጊ ነው ነው ብለዋል።
"ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ ከ5 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከኬርሶን ወጥተዋል” ማለታቸውም ተዘግቧል።
በግዞት ላይ ያሉት የኬርሶን ምክትል ከንቲባ እንዳሉት ከጦርነቱ በፊት የከተማዋ ነዋሪ 320 ሺህ ህዝብ የነበረ ሲሆን የሩሲያን ወረራ ሸሽተው 100 ሺህ ነዋሪዎች ብቻ እንደቀሩም አስረድተዋል።
በሩስያ ቁጥጥር ስር ያለችው የሜሊቶፖል ከንቲባ ኢቫን ፌዶሮቭ ሩሲያ ከተማዋን በ"ወታደሮች እና በባንዳዎች" ለመሙላት የኬርሰን ነዋሪዎች በግዳጅ እየተባረሩ እንደሆነና ቤታቸውንም እየተነጠቁ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።