የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ሩሲያ የዩክሬንን ግዛቶች በኃይል መጠቅለሏን አወገዘ

ታትሟል

የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ሩሲያ የዩክሬን ግዛቶችን በኃይል መያዟን በከፍተኛ ድምጽ አውግዟል።

ውሳኔው በ143 አገራት ድጋፍ ሲያገኝ ቻይና እና ሕንድ ግን ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል።

ሩሲያን ጨምሮ አራት አገራት ደግሞ ውሳኔውን ባለመቀበል የተቃውሞ ድምጽ ሰጥተዋል።

ሩሲያ ጋር አብረው የቆሙት ቤላሩስ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ሶሪያና ኒካራጉዋ ናቸው።

ሩሲያ የዩክሬንን ከወረረች ወዲህ በዚህን ያህል ድምጽ ተቃውሞ ሲገጥማት የመጀመርያው ነው።

ባለፈው ሳምንት እጅግ በደመቀ ሥነ ሥርዓት ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን ሉሃንስክ፣ ዶኔስክ፣ ዛፖሪዥያ እና ኬርሶን የሩሲያ አንድ አካል እንዲሆኑ ፊርማቸውን ማኖራቸው ይታወሳል።

ሉሃንስክ፣ ዶኔስክ፣ ዛፖሪዥያንና ኬርሶን የምሥራቅ ዩክሬን ግዛቶች ነበሩ።

ፑቲን ይህን ፊርማቸውን ያኖሩት ሩሲያ ሾማቸው ከነበሩ የግዛቶቹ አስተዳዳሪዎች ጋር ከተጨባበጡ በኋላ ነው።

አራቱ ግዛቶች የምዕራቡ ዓለም ‘የይስሙላ’ ያለው ሕዝበ ውሳኔ ማድረጋቸውን ተከትሎም ነበር ፑቲን ግዛቶቹ ከእንግዲህ የሩሲያ ናቸው ብለው የፈረሙት።

ከዚህ ወዲያ በነዚህ ግዛቶች ላይ ጥቃት ቢፈጸም በሩሲያ ግዛት ላይ ጥቃት እንደተፈጸመ ተደርጎ ስለሚቆጠር ፖለቲካዊና ወታደራዊ ትርጉም ሰፊ ነው ይላሉ ተንታኞች።

ይህ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የቀረበው ውሳኔ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግዛቶቹ የሩሲያ እንደሆኑ አድርጎ ዕውቅና እንዳይሰጥ የሚያደርግ ነው።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የጉባኤውን ውሳኔ አሞካሽተው ድምጽ ለሰጡ አገራት ምስጋና አቅርበዋል።

አክለውም፣ ‘ዩክሬን እያንዳንዷን ኢንች መሬት ታስመልሳለች’ ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ዝተዋል።

የአሜሪካው ጆ ባይደን በበኩላቸው ጉባኤው ያሳለፈው ውሳኔ ለሞስኮ ግልጽ መልዕክት ይሰጣል ብለዋል።

‘ሩሲያ እንዲሁ በዘፈቀደ ሉአላዊ ግዛቶችን ከዓለም ካርታ መፋቅ እንደማትችል ያሳየ ውሳኔ ነው’ ብለዋል ባይደን።

በተባበሩት መንግሥታ የዩኬ አምባሳደር ባርባራ ዉድዋርድ በበኩላቸው ‘ሩሲያ በጦር ሜዳም በተባበሩት መንግሥታት ጉባኤም ተሸንፋለች’ ብለዋል።

‘ሩሲያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከዓለም ማኅብረሰብ እየተነጠለች ነው። ነገር ግን ሩሲያ ጦርነቱን ማቆም ከፈለገች ጊዜው አሁን ነው ብለዋል ባርባራ።

የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ሩሲያ ግዛቶቹን መጠቅለሏን ተከትሎ በጸጥታው ምክር ቤት ሊያሳልፈው የነበረውን ውሳኔ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውድቅ ካደረገችው በኋላ የተጠራ ነው።

ሩሲያ በጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ ያላትን ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት እንድትቀማ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው።

ከሩሲያ በተጨማሪ ፈረንሳይ፣ ቻይና፣ አሜሪካና ዩኬ የዚህ ልዩ መብት ባለቤቶች ናቸው።