አርሰናል የሰሜን ለንደን ደርቢን ያሸንፋል? ወይስ የመርሲሳይድ ደርቢ ዕጣ ይደርሰዋል?

የአርሰናል እና ቶተነሃም አምበል የሆኑት ኦዴጋርድ እና ሶን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአርሰናል እና ቶተነሃም አምበል የሆኑት ኦዴጋርድ እና ሶን
ታትሟል

ሊቨርፑል በመርሲሳይድ ደርቢ በኤቨርተን መሸነፉ በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ያለውን ተስፋ ሲያጨልምበት፤ አርሰናል በሜዳው ቼልሲን፤ ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ ከሜዳው ውጪ ብራይተንን አሳማኝ በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

በዚህ ሳምንት የሚደረጉ ጨዋታዎች የዘንድሮውን ዋንጫ ወደ የትኛው ክለብ ሊያመራ እንደሚችል ሊጠቁመን ይችላል።

ሊቨርፑል በአውሮፓ መድረክ የመጫወት ተስፋ ካለው ዌስት ሃም ጋር ከሜዳው ውጪ ይጋጠማል። አርሰናል በሰሜን ለንደን ደርቢ በቶተነሃም ሜዳ ይፈተናል። ሲቲ ደግሞ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ወደ ሚታገለው ፎረስት ያቀናል።

የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን የፕሪሚየር ሊግ ግምቶቹን እንደሚከተለው ሰጥቷል።

ዌስት ሃም ከ ሊቨርፑል

ዌስት ሃም ከ ሊቨርፑል

ከሁለት ሳምንት በፊት ሊቨርፑል በፓላስ ተሸንፎ ጉድ ሲባል በተመሳሳይ ቀን አርሰናል በደጋፊው ፊት በቪላ መሸነፉ ይታወሳል።

ይባስ ብሎ ሊቨርፑል በኤቨርተን መሸነፉን የዋንጫ ተስፋው አብቅቶለታል አስብሏል።

8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዌሰት ሃም በቀጣይ ዓመት በኮንፍረንስ ሊግ የመሳተፍ ዕድሉን ለማረጋገጥ ሊቨርፑልን ሊፈትነው ይችላል።

በኤቨርተን ያልተጠበቀ ሽንፈት አስተናግዶ የዋንጫ ተስፋው በእጅጉ የተመናመነው ሊቨርፑል ይህን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ ይኖርበታል።

የርገን ክሎፕ በመጨረሻ የውድድር ዘመናቸው የሚገባቸውን ማግኘት አለባቸው ብዬ አስባለሁ።

ግምት፡ ዌስት ሃም 1 - 2 ሊቨርፑል

ፉልሃም ከ ክርስታል ፓላስ

በቅርቡ ክርስታል ፓላስ አስደናቂ አቋም እያሳዩ ይገኛሉ። ጎሎችንም እያስቆጠሩ ነው። ማቴታ ለፓላስ ጎል እያመረተ ነው። ካለፉት 8 ጨዋታዎች 7 ጎሎችን አስቆጥሯል።

በተቃራኒው ፉልሃም ካለፉት 4 ጨዋታዎች በሦስቱ ተሸንፈዋል። በዚህ ጨዋታ ፓላስ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ። ጨዋታው ግን በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል።

ግምት፡ ፉልሃም 2 - 2 ፓላስ

ማንቸሰተር ዩናይትድ ከ በርንሊ

ማንቸሰተር ዩናይትድ ከ በርንሊ

ዩናይትድ ሆነ ብሎ ነገሮችን እራሱን የሚያከብድ ይመስለኛል።

በቀላሉ ያሸንፋሉ ብዬ በገመትኩት ጨዋታ በሊጉ የመጨረሻ ደረጃ ላይ በሚገኝ ቡድን ሁለት ጊዜ ተመርተዋል።

ይህ ተጋጣሚያቸው በወራጅ ቀጠና የሚገኝ ቢሆንም፣ ከሼፊልድ የተሻለ ወጥ የሆነ አቋም እያሳየ የሚገኝ ቡድን ነው።

በተርፍ ሞር በጠባብ ውጤት በዩናይትድ የተሸነፉት በርንሊዎች በዚህ ጨዋታም እንደሚሸነፉ ብገምትም የቪንሰት ኮምፓኒ ቡድን ለቀያይ ሴጣኖቹ ፈተና እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም።

ግምት፡ ዩናይትድ 2 - 1 በርንሊ

ኒውካስል ከ ሼፊልድ ዩናይትድ

ሼፊልድ በዚህ ጨዋታ የሚሸነፍ ከሆነ ከፕሪሚየር ሊጉ እንደሚወርድ ያረጋግጣል።

በሁሉም የአሰላለፍ ክፍል ውስጥ ቁጥጥር አንሷቸው የቆዩት ሼፊልዶች ከሊጉ እንደሚወርዱ ከገባቸው የቆየ ይመስለኛል።

ከዚህ ቀደም በነበረው ጨዋታ ኒውካስል 8 ጎሎች እንዳስቆጠረባቸው ይታወሳል። በዚህ ጨዋታም ኒውካስል እንደሚያሸንፍ ምንም ጥርጥር የለኝም።

ግምት፡ ኒውካስል 3 - 1 ሼፊልድ

ዎልቭስ ከ ሉተን

ዎልቭስ እጅግ አስቀያሚ የሆነ አቋም ላይ ይገኛል። ምናልባት ላለመውረድ ከፍተኛ ትንቅንቅ ውስጥ ላለው ሉተን መልካም አጋጣሚ ሊሆን ይችላል።

ሉተን በሜዳቸው በብሬንትፎርድ 5 ለ 1 ሲሸነፉ በሜዳ ተገኝቼ ጨዋታውን ስመለከት ነበር። በዚያ ጨዋታ አጥቅተው ለመጫወት ሲሞክሩ በቀላሉ ሲጠቁ ነበር።

ከዚህ ቀደም እንዳልኩት ሉተን በፕሪሚየር ሊጉ የሚቆይ ከሆነ አሠልጣኙ ሮብ ኤድዋርድስ የዓመቱ ምርጥ አሠልጣኝ ተብሎ መሸለም አለበት።

ግምት፡ ዎልቭስ 3 - 1 ሉተን

ኤቨርተን ከ ብሬንትፈርድ

ኤቨርተን ከ ብሬንትፈርድ

ኤቨርተን ሊቨርፑልን ባሸነፈበት ጨዋታ ዶሚኒክ ካልቨርት-ሉዊን እጅግ አስደናቂ ነበር። እስካሁን የት ነበር ስል እራሴን ስጠይቅ ነበር።

ኤቨርተን ከዚያ ድል በኋላ የመውረድ ስጋቱ ቀሎለታል።

ይህን ጨዋታ ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል መገመት ቀላል አይሆንም፤ ግን ሁለቱም ጎል እንደሚያስቆጥሩ እገምታለሁ።

ግምት፡ ኤቨርተን 1 - 1 ብሬንትፈርድ

አስተን ቪላ ከ ቼልሲ

ማንቸስተር ሲቲን ከአንዴም ሦስቴ የፈተነው ቼልሲ እንዴት ለአርሰናል በቀላሉ እጅ እንደሰጠ ማሰብ ከብዶኛል።

በቀሪ ጨዋታዎች ምንም ይፈጠር ምን አሰልጣኝ ማሪሲዮ ፖቸቲኖ ከቼልሲ ጋር አብሮ መቆየት አለበት።

በኤፍኤ ዋንጫ ቼልሲ በቪላ ፓርክ አስተን ቪላን ማሸነፍ ችሎ ነበር። አሁን ግን ሁኔታዎች ተመሳሳይ አይደሉም። ቪላ ያሸንፋል ባይ ነኝ።

ግምት፡ አስተን ቪላ 2 - 1 ቼልሲ

ቦርንመዝ ከ ብራይተን

ብራይተን በዚህ የውድድር ዓመት በጣም ደካማ ሆኖ ቆይቷል።

ከሲቲ ጋር በነበራባቸው ጨዋታ ኳስ በጥሩ ሁኔታ ቢቀባበሉም ከ4 ለ 0 ሽንፈት አልታደጋቸውም።

በውድድር ዓመቱ በዚህ ወቅት በደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ቦርንመዝን ከብራይተን በላይ ይሆናል ብሎ አይታሰብም ነበረ።

ይህ ጨዋታ ብዙ ጎሎች የሚቆጠሩበት ይሆናል። ብዙዎች ባይስማሙም ይህን ጨዋታ ቦርንመዝ ያሸንፋል ባይ ነኝ።

ግምት፡ ቦርንመዝ 4 - 3 ብራይተን

ቶተነሃም ከ አርሰናል

ቶተነሃም ከ አርሰናል

የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ይህ ነው። አርሰናል ከቪላው ያልተጠበቀ ሽንፈተ በኋላ ዎልቭስ እና ቼልሲን በተከታታይ አሸንፎ ነው ወደ ስፐርስ ስታዲየም የሚያቀናው።

አርሰናል በዚህ አጨዋወቱ ከቀጠለ ይህን ጨዋታ ያሸንፋል።

ቶተነሃም ደግሞ ባለፉት ጨዋታዎች ብቃታቸው ላይ አይገኙም።

ጥሩ ፉክክር የሚኖረው ጨዋታ ይሆናል። አርሰናል የተሻሉ አጥቂዎች አሉት ብዬ ስለማስብ ይህን ጨዋታ አሸንፈው ማንቸሰተር ሲቲ ላይ ጫናውን ከፍ ያደርጋሉ።

የሚኬል አርቴታ ቡድን ከቶተነሃም በኋላ ያሉትን ሦስቱንም ጨዋታዎች ያሸንፋል ብዬ ግን አልገምትም።

ግምት፡ ቶተነሃም 1 - 2 አርሰናል

ኖቲንግሃም ፎረስ ከ ሲቲ

ለላመውረድ እና ሻምፒዮን ለመሆን በሚደረገው ትንቅንቅ ውስጥ ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች እጅግ ወሳኝ ነው።

ሲቲ ከብራይተን በነበረው ጨዋታ እጅግ ድንቅ ነበረ። የአርሰናል ደጋፊዎች ብራይተን ሲቲን ነጥብ ካስጣለ በሚል ጨዋታውን ለመመልከት ተቀምጠው ነበር። ሲቲ ገና ከጅምሩ ጎል ማዝነብ ሲጀምር የአርሰናል ደጋፊዎች ከእረፍት በፊት ቲቪያቸውን የዘጉ ይመስለኛል።

ይህን መሰል አስደናቂ አቋም የሚያሳየው ሲቲን ከአሁን በኋላ ማን ሊፈትነው ይችላል የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። እኔ ግን ፎረስት ሲቲን እንደሚፈትነው እገምታለሁ።

ፎረስት በሜዳው የሚቀመስ ቡድን አለመሆኑን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ተመልክተናል። ባለፈው የውድድር ዓመት ማብቂያ ላይም ከሲቲ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል።

ፎረስቶች በዚህ ጨዋታ የተቻላቸውን ያደርጋሉ። በመጨረሻም እጅ ይሰጣሉ።

ግምት፡ ፎረስ 1 - 2 ሲቲ