በሁለት ሕጻናት ልጆችዋ ግድያ የተጠረጠረችው እናት በቁጥጥር ሥር ዋለች

ታትሟል

በደቡብ ኮርያ የምትገኝ ሴት ሁለት ሕጻናት ልጆቿን በመግደል እንደተከሰሰች የኒው ዚላንድ ፖሊስ አስታወቀ።

ከአንድ ወር በፊት የሕጻናቱ አስክሬን ኒው ዚላንድ ውስጥ ሻንጣ ውስጥ ሆኖ መገኘቱ በስፋት ተዘግቦ ነበር።

በዚህ ወንጀል የተጠረጠረችው እናት አሁን በደቡብ ኮርያ በቁጥጥር ሥር የዋለች ሲሆን፣ ኒው ዚላንድ ተላልፋ እንድትሰጣት ጠይቃለች።

አስክሬኖቹን ያገኙት ኦክላንድ ከሚገኝ መደብር ሻንጣውን ጨምሮ በርካታ እቃዎችን በጨረታ የገዙ ሰዎች ናቸው።

የሕጻናቱ ዕድሜ ከአምስት ዓመት እስከ 10 የሚገመት ሲሆን፣ አስክሬናቸው ለጥቂት ዓመታት ለዓመታት ሻንጣ ውስጥ ቆይቷል።

ትውልደ ኮሪያዊ እና የኒው ዚላንድ ዜግነት ያላት ግለሰቧ ወንጀሉን ከፈጸመች በኋላ ወደ ደቡብ ኮሪያ ያቀናች ሲሆን፤ ተጠርጣሪዋን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የኒው ዚላንድ ፖሊስ ከደቡብ ኮርያ ፖሊስ ጋር ላለፉት ሦስት ሳምንታት በቅርበት እንደሠራ ተገልጿል።

ግለሰቧን ፖሊስ መያዝ የቻለው የሕጻናቱን ማንነት ማወቅ ከተቻለ በኋላ ነበር።

የኒው ዚላንድ ፖሊስ መርማሪ የሆኑት ቶፊሉ ፋማኑያ ቫሉአ “የደቡብ ኮርያ ፖሊሶች ከኒው ዚላንድ ኢንተርፖል ባልደረቦች ጋር በመተባበራቸው ግለሰቧ በቁጥጥር ሥር ውላለች” ብለዋል።

ሕዝቡም ፖሊስን እንደተባበረ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

የሟቾቹ ሕጻናት አያቶች ኦክላንድ ውስጥ ሲሆን የሚኖሩት፣ ወላጅ አባታቸው ደግሞ ሕጻናቱ ከመሞታቸው በፊት በካንሳር ሕመም ሕይወቱ አልፏል ተብሏል።

ያለፈው ነሐሴ ላይ አንድ ቤተሰብ በኦክላንድ መደብር ሻንጣን ጨምሮ የተለያዩ መገልገያዎች ከገዛ በኋላ ነበር የሕጻናቱ አስክሬን ሻንጣ ውስጥ የተገኘው።