ፖሊስ በናይሮቢ 41 ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ

ታትሟል

በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ፖሊስ 41 ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ።

ግለሰቦቹ ወደ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች አገራት ለመዘዋወር በአንድ ቤት ውስጥ ለአራት ቀናት ያህል ሲጠባበቁ ሰኞ ጥር 29፣ 2015 ዓ.ም መያዛቸው ተገልጿል።

ኢትዮጵያውያኑን በሕገ ወጥ መንገድ ሊያዘዋውሩ ነበሩ የተባሉ ሁለት አዘዋዋሪዎችም በዚሁ አጋጣሚ የተያዙ ሲሆን አንደኛው ኢትዮጵያዊ መሆኑም ተነግሯል።

ፖሊስ ጥቆማ ደርሶት በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው እነዚህ የሕገ ወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ሌሎች በርካታ ዝውውሮች ጀርባ እንዳሉበትም አስታውቋል።

ኢትዮጵያውያኑ በዚህ ሳምንት ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን ወደ ኬንያ እንዴት እንደገቡ ተጨማሪ ምርመራ እስኪደረግ ድረስ ለተጨማሪ ስድስት ቀናት በእስር እንዲቆዩም ታዟል።

የኬንያ ተሻጋሪ የተደራጁ ወንጀሎች ክፍል ኃላፊ ጆርጅ ሙቶኒያ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያዊያኑ ሕጋዊነታቸውን የሚያረጋግጥ ትክክለኛ ሰነድ አልነበራቸውም ብለዋል።

ኬንያ ወደ ታንዛንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ወደ መካከከለኛው ምሥራቅ ለመሄድ ለሚፈልጉ ስደተኞች እንደ መሸጋገሪያ ሆና ታገለግላለች።

የተያዙት ግለሰቦች በተጨናነቁ ሁለት ክፍሎች ውስጥ ፈታኝ በሆነ ቦታ ለአራት ቀናት ያህል ሲጠባበቁ እንደነበር ኃላፊው ገልጸዋል።

ግለሰቦቹ ለአዘዋዋሪዎቹ ገንዘብ ከፍለው ኬንያ እንደገቡ የተናገሩት ጆርጅ፣ ኢትዮጵያውያኖቹ የነበሩበትን ሁኔታ “አሳዛኝ” ሲሉ ተናግረዋል።

41ዱ ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያዎቹ ሳይሆኑ ከዚህ ቀደም ኅዳር ወር ላይ 70 ስደተኞችን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሌላ አገር ለመሸጋገር ኬንያ በሕገ ወጥ መንገድ በመግባታቸው ታስረዋል እንዲሁም ወደ አገራቸውም እንዲመለሱ ተደርገዋል።

ፖሊስ እንዲሁም የአገሪቱ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ወደ ኬንያ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ነው።

በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ኢትዮጵያውያንም ቁጥር መጨመሩ አሳሳቢ እንደሆነም ነው ጆርጅ ሙቶኒያ የተናገሩት።

በኬንያ በየዓመቱ በአማካኝ አስር ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ሲሆን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋሉ ተብሏል። በርካቶች ወደ ሌላ አገር ለመሻገር ወይንም በኬንያ ሥራ ለመፈለግ የሚመጡ ናቸው።

ለፖሊስም ሆነ ለባለስልጣናቱ ጥያቄ የሆነው ስደተኞቹ ከሞያሌ ድንበር እስከ ናይሮቢ ድረስ ያሉ የፖሊስ ኬላዎችን እንዴት አለፉ የሚለው ነው።

በዚህ መንገድ ላይ በርካታ ኬላዎችና የጸጥታ አስከባሪዎች እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን ባለስልጣናቱ ሙስና ለአዘዋዋሪዎቹ መንገድ ከፍቶላቸዋል ይላሉ።

“ይህ ለሕገ ወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች አትራፊ ቢዝነስ ሆኖላቸዋል እናም ሊቆም ይገባዋል። በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ በሰዎች ዝውውር በተቀናጀ ሁኔታ የሚንቀሳቀሰው ቡድን አካል ናቸው” ሲሉም ተናግረዋል።