በአሜሪካ የአዞ መንጋጋ ውስጥ የአንዲት ሴት አስክሬን ተገኘ

በፖሊስ የተገደለው ግዙፉ አዞ

የፎቶው ባለመብት, CBS

የምስሉ መግለጫ, በፖሊስ የተገደለው ግዙፉ አዞ
ታትሟል

በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት ውስጥ 4 ሜትር ርዝመት ባለው አዞ መንጋጋ ውስጥ የአንዲት ሴት የሰውነት ቅሪት መገኘቱን ተከትሎ አዞው መገደሉን ፖሊስ ገልጿል።

በአካባቢው በሚገኝ የውሃ መፋሰሻ ውስጥ አዞው የጉዳቱ ሰለባ የሆነችውን ሴት የታችኛውን የሰውነት ክፍል ይዞ መመልከቱን አንድ የአይን ዕማኝ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግሯል።

በፍሎሪዳ ፒኒሌስ ካውንቲ የጸጥታ መስሪያ ቤት ባልደረባ አዞው እንደተገደለና የ41 ዓመቷ ሳብሪና ፒክሃም ቀሪ አስክሬን በውሃ ላይ መገኘቱን ተናግረዋል።

የሳብሪና ፒክሃም አሟሟትን በተመለከተ ምርመራ እየተደረገ ይገኛል።

ባለፈው አርብ በአዞ መንጋጋ ላይ የሰው ቅሪት መታየቱን ተከትሎ ወደ ፖሊስ ሪፖርት ተደርገል።

ክስተቱን ለፖሊስ ሪፖርት ያደረገው ጃማርከስ ቡላርድ ለስራ ቃለ መጠይቅ እየተጓዘ ሳለ አዞው አፉ ውስጥ መጀመሪያ ላይ የልብስ መሸጫ ቤቶች አሸንጉሊት የሚመስል ነገር መመልከቱን ተናግሯል።

“የሰው ታችኛው የሰውነት ክፍል አስክሬን በአፉ ውስጥ እንደሚገኝ አስተዋልኩ። ያንን እንደተመለከተኩ ወደ እሳት አደጋ መቆጣጠሪያ መስሪያ ቤት ገሰገስኩ” ሲል ለአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።

“አዞን ፊት ለፊት ሳይ ይህ የመጀመሪያ ነው። ስለዚህ ሳየው እንደጥሩ ነገር ነው የተመለከትኩት። ነገር ግን ያየሁት ነገር ሳይ ‘ይሄ የልብስ መሸጫ አሻንጉሊት ነው?’ አልኩ” ይላል።

ቀጥሎም “በአፉ የያዘው የገረጣና ነጭ ነው” ብሏል።

በሌላ ቃለ መጠይቁ ደግሞ “ከአፉ ጋር ተጣብቋል። ከዚያም ዞሮ ሄደ። እውነት ነው ብዬ ለማመን ተቸገርኩ” ሲል ገልጿል።

የሟቿ ቤተሰቦች የገቢ ማሰባሰቢያ አዘጋጅተዋል። ፒክሃም በሞተችበት አቅራቢያ በሚገኝ የቤት አልባ ሰዎች መጠለያ ውስጥ ትኖር እንደነበር ቤተሰቦቿ ተናግረዋል።

የጉዳቱ ሰለባ የሆነችው ሴት ልጅ እንደሆነች የተናገረች ብሪውና ዶሪስ “ወደ መጠለያው እየሄደች ወይም ከመጠለያው ወጥታ እየተጓዘች ሳለ ከውሃ የወጣው አዞ ጥቃት አድርሶበት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል” ስትል በፌስ ቡክ ገጿ ጽፋለች።

አዞው የተያዘበት የውሃ መፋሰሻ ቦይ

የፎቶው ባለመብት, GOOGLE

የምስሉ መግለጫ, አዞው የተያዘበት የውሃ መፋሰሻ ቦይ

“ማንም ሰው በዚህ አኳሃን ሊሞት አይገባውም” ስትልም አክላለች።

የአካባቢው ባለስልጣናት አዞው ውሃ ውስጥ እንዳለ እንዲገደል ከተደረገ በኃላ የፖሊስ የአደጋ ጊዜ ቡድን ውሃ ውስጥ በመግባት ባከናወነው ስራ የሟቿን ቀሪ የአስክሬን አካል እንዳገኘ ገልጸዋል።

የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ግዙፍ የሆነ አዞ በፖሊስና በአደጋ ጊዜ መኪናዎች ተከቦ አሳይቷል።

ሆኖም የጤና ባለሙያዎች እስካሁን የሞቷን መንስኤ እያጣሩ ይገኛሉ።

የአካባቢው ነዋሪዎች በስፍራው አነስተኛ አዞዎች እንደሚገኙ ገልጸው ይህንን የሚያክል አዞ አይተው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

ጄኔፈር ዲን የተባችው ነዋሪ “በጣም ይገርማል። ልጆቼ በዚህ ቦታ ሁልጊዜ ይሄዳሉ። በጣም ያስፈራል። አነስ ያሉ አዞዎችን አይቼ አውቃለሁ። ይህንን የሚያክል ግዙፍ አዞ ግን ገጥሞኝ አያወቅም” ብላለች።