በኢትዮጵያ ያለ ሕግ አግባብ የታሰሩ ኤርትራውያን እንደሌሉ መንግሥት አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, ACT OF SAMARITAN
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ሕግ አግባብ የታሰሩ ኤርትራውያን እንደሌሉ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ።
መሥሪያ ቤቱ በርካታ ኤርትራውያን በሕገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ በመቆየት፣ ለውጭ አገር ዜጎች ባልተፈቀዱ የሥራ መስኮች ላይ ተሰማርተው መገኛታቸውን አመልክቷል።
በተጨማሪም በኮንትሮባንድ፣ በሕገወጥ ሰው ዝውውር እና በሌሎች ሕገወጥ ተግባሮች ላይ የሚገኙ እንዳሉ ጠቅሶ እነዚህ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ገልጿል።
በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ በኤርትራውያን ላይ የጅምላ እስራት እየተካሄደ እንደሆነ ቢቢሲ ትግርኛ ያነጋገራቸው በርካታ በከተማዋ የሚኖሩ ኤርትራውያን ከዚህ ቀደም መግለጻቸው ይታወሳል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ላይ ግን ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ያነጣጠረ ከአገር ማባረርም ሆነ እስር እንዳልተፈጸመ ገልጾ ነገር ግን "የአገርን ብሔራዊ ደኅንነት እና ጥቅምን በሚጎዳ መልኩ ሕገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የውጭ አገር ዜጎች" ላይ ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ ገልጿል።
በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር የገቡ ኤርትራውያንን መሥሪያ ቤቱ ወደ ሕጋዊ መንገድ ለማስገባት መሥሪያ ቤቱ በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያደርግም የተመዘገቡት ውስን ናቸው ብሏል።
ሆኖም ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ እና የሥራ ፈቃድ ሳይኖራቸው፣ በሐሰተኛ ማንነት ለውጭ አገር ዜጎች ባልተፈቀዱ የሥራ መስኮች ከትንሽ ሱቅ ችርቻሮ እስከ ትላልቅ ሥራዎች ላይ በሕገወጥ መንገድ ተሰማርተው እንደሚገኙ አጽንኦት ሰጥቷል።
በርካታ የኤርትራ ስደተኞች ዘመድ ለመጠየቅ በማስመሰል ከዱባይ፣ ከኤርትራ፣ ከኡጋንዳ በመመላለስ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች በሻንጣ በማስገባት እና በማስወጣት በኮንትሮባንድ እና በሌሎች ሕገወጥ ተግባራት ተሰማርተው ተገኝተዋል ተብሏል።
በተጨማሪም በተለያዩ አገራት ከሚገኙ ሌሎች ሕገወጥ ደላሎች ጋር በመተባበር በርካታ ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሲያከናውኑ መገኘታቸውን ጠቅሷል።
ሐሰተኛ እና የተጭበረበሩ የጉዞ እና የይለፍ ሰነዶች፣ ማህተሞች፣ የባንክ ቡኮች በማዘጋጀት እና በመጠቀም ሕገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ የተገኙ አሉ ብሏል።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አክሎም ሐሰተኛ ሰነድ እና ማንነትን በመጠቀም ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ሲያከናውኑ እና ከሕግ ውጪ ሰነዶችን ይዘው የተገኙ እንዳሉም በመግለጫው አካቷል።
ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ የአገሪቱን ሕግ ተላልፎ ከተገኘ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን ገልጾ በአንድ አገር ዜጋ ብቻ ተለይቶ እየተፈጸመ ያለ አሰራር ተደርጎ ሪፖርት መደረጉ ስህተት ነው ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የኤርትራውያን ስደተኞች እስርን በተመለከተ መረጃ እንዳለው እና የኢትዮጵያ ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ በኩል እንዲፈቱ መጠየቁን ለቢቢሲ ትግርኛ መናገሩ ይታወሳል።
በተለያዩ ምክንያቶች ከኤርትራ እንደተፈናቀሉ የሚገልጹት ስደተኞቹ ሕይወታቸውን የሚፈታተን ስጋት እያጋጠማቸው በመሆኑ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ለጉዳያቸው ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች በኤርትራውያን ላይ እስር እና እንግልት በመድረሱ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የኤርትራውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች እስር እንዲቆም መጠየቁ አይዘነጋም።
ከተፈቀደላቸው የጊዜ ገደብ በላይ የቆዩ ስደተኞች የሚጣልባቸው ክፍያ በእጅጉ የቀነሰ ሆኖ እያለ ለኤርትራውያን የተለየ የተጋነነ ክፍያ እየተጠየቁ ነው የሚለው ከእውነት የራቀ መሆኑንም የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ገልጿል።












