የአሜሪካው ጡረተኛ ወታደር በአንድ ጊዜ ስድስት የሎተሪ ትኬት አሸናፊ ሆኑ

የፎቶው ባለመብት, MASSACHUSETTS STATE LOTTERY
በቬትናም ጦርነት ጊዜ የተሳተፉት የአሜሪካ ሠራዊት ጡረተኛ ማሳቹሴትስ ግዛት ውስጥ ወደ ሚገኝ አንድ የመጠጥ ግሮሰሪ የገቡት በስሜታቸው ተመርተው ነበር።
ከ20 ዓመታት በላይ እንዳደረጉት በዚህ ዕለትም ሎተሪ ገዝተው ዕድላቸውን ሞክረዋል።
ቀልባቸው ግን በአንድ ትኬት ብቻ ዕድላቸውን መሞከር እንደሌለባቸው ይገፋፋቸው ነበር፣ ከሁለትም በላይ ስድስት ሎተሪ የመግዛት ፍላጎት አደረባቸው።
ለዚህ ደግሞ በሎተሪ ትኬቶቹ ላይ ያሉት ቁጥሮች የተለያዩ እንዳይሆኑ ስሜታቸው ይገፋቸው ነበር። በዚህም ምክንያት በእያንዳንዱ ትኬት ላይ ተመሳሳይ ቁጥሮችን ተጠቀሙ።
ዕድል ሆነና የቬትናም ጦርነት ጡረተኛ ሬይመንድ ሮበርትስ በስድስቱም ትኬቶች አሸንፉ። በዚህም ወደ 2 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እና 20 ዓመታዊ የ25,000 ዶላር ክፍያ አሸነፉ።
ሮበርትስ የመረጧቸው አሸናፊዎቹ ቁጥሮች በጥንቃቄ የተመረጡ የልደት እና የክብረ በዓል ቀኖችን ያጣመሩ ናቸው።
ነገር ግን ከዚህ በፊት ይህን ዘዴ በሌሎች የሎተሪ ቲኬቶች ላይ ቢጠቀሙባቸውም ተሳክቶላቸው አያውቅም ነበር።
ከቦስተን በስተደቡብ 80 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ፎል ሪቨር የሚኖሩት ጡረተኛ ወታደር አሸናፊ የሆኑት ታኅሥሣ 15 ነው።
ታዲያ ባላሰቡት ሃብታቸው ምን ለማድረግ አስበዋል?
የሎተሪው ድርጅት እንዳለው የመጀመሪያው ዕቅዳቸው ሞተር ሳይክል መግዛት ነው።
ላኪ ፎር ላይፍ (የሕይወት ዕድለኛ) የሚባለውን የሎተሪ ጨዋታ ነው ሮበርትስ የተጫወቱት።
በጨዋታው ሕግ መሠረት የሕይወት ሽልማት የሆነውን 25,000 ዶላር በዓመት የማሸነፍ ዕድሉ ከ1,813,028 አንድ ነው።
የማሳቹሴትስ ግዛት ነዋሪዎች ከአሜሪካ ግዛቶች በበለጠ በነፍስ ወከፍ ሎተሪ እና የሚፋቁ ትኬቶችን በመግዛት ይታወቃሉ።












