የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት የአገሪቱ ባለስልጣናት የውጭ ጉዞዎችን እንዳያደርጉ አገዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ቦላ ቱኒቡ ሚኒስትሮች እና ሌሎች የመንግሥት ባለስልጣናት በአገሪቱ ገንዘብ የውጭ አገራት ጉዞዎችን እንዳያደርጉ የሶስት ወራት እገዳ ጣሉ።
ይህ እርምጃ ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ ላይ የተደረሰውም የመንግሥት ባለስልጣናቱ በውጭ የሚያደርጓቸው ጉዞዎች ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ስጋት መሆኑን ተከትሎ እንደሆነ የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ገልጸዋል።
እግዱም ከአስር ቀናት በኋላ ተግባራዊ ይሆናል።
ፕሬዚዳንት ቱኒቡ እና ባለስልጣኖቻቸው በተደጋጋሚ ወደ ውጭ አገራት በሚያደርጓቸው ተደጋጋሚ ጉዞዎች ትችቶች ሲቀርብባቸው ይሰማል።
ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ዓመት ግንቦት ስልጣን ላይ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ከ15 በላይ የውጭ ጉዞዎችን አድርገዋል።
ፕሬዚዳንቱ በመጀመሪያዎቹ የስድስት ወራት ውስጥ ቢያንስ 3.4 ቢሊዮን ናይራ (2.2 ሚሊዮን) ለሃገር ውስጥ እና ለውጭ ጉዞዎች ማውጣታቸው ተዘግቧል።
ይህም ለ2023 ከተያዘው በጀት 36 በመቶ ብልጫ እንዳለውም የመንግሥት ወጪዎችን የሚከታታለውን GovSpend የተባለውንም ተቋም ዋቢ በማድረግ የናይጄሪያው ጋዜጣ ፓንች ዘግቧል።
ናይጀሪያ አሁን ባለችበት የምጣኔ ኃብት ቀውስ መካከል የጉዞ እገዳው ወጪን በመቀነስ የአገሪቱ ገንዘብ ኃላፊነት ባለው መልኩ እንዲወጣ እንደሚያደርግም የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፌሚ ባጃቢያሚላ ተናግረዋል።
የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር በአስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት እየፈተኗት ይገኛል። ይህም ሁኔታ በርካቶችን ለከፋ ችግር ያጋለጠ ሲሆንም ብሔራዊ ቁጣም አስከትሏል።
ፕሬዚዳንቱ በመንግሥት ባለስልጣናት ላይ የሶስት ወር እገዳ የጣሉትም እየቀረበባቸው ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞም ለመቀልበስ እያደረጉት ያለው ሙከራም ነው ተብሏል።
በያዝነው ዓመት ጥር ወር ላይም የራሳቸውን የፕሬዚዳንቱን አጃቢዎች ጨምሮ የመንግሥት ባለስልጣናት የጉዞ ልዑካንን 60 በመቶ ገደማ እንደሚቀንሱ አስታውቀው ነበር።
የአሁኑ እገዳ ተግባራዊ ሲሆን የመንግሥት ባለስልጣናት ወደ ውጭ አገራት ጉዞ ማድረግ የሚችሉት “በጣም አስፈላጊ ናቸው” ወደተባሉ ስፍራዎች ብቻ ይሆናል። በተጨማሪም ከመጓዛቸው ቢያንስ ከሁለት ሳምንት በፊትም የፕሬዚዳንቱን ይሁንታ ማግኘት አለባቸው።
ባጃቢያሚላ አክለውም የጉዞው እግድ የመንግሥት ባለስልጣናት የስራ ድርሻቸውንም ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመወጣት እና አገልግሎትም ለመስጠት እንዲያተኩሩ ያደርጋቸዋል ብለዋል።
በመንግሥት ባለስልጣኖቻቸው ላይ የጉዞ እግድ የጣሉት ፕሬዚዳንቱ ይህ ራሳቸው በሚያደርጓቸው ጉዞዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ ያሉት ነገር የለም።
ፕሬዚዳንቱ እና ባለስልጣኖቻቸው ህዝቡ ችላ ብለዋቸዋል በማለት የሚተቿቸውን የምጣኔ ኃብቶች ለመቅረፍ የሚያደርጓቸው የውጭ አገር ጉዞዎች ወሳኝ ናቸው በማለት ሲሟገቱ ይሰማ ነበር።












