ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቼልሲው ባለቤት ኪሊያን ምባፔን ለማስፈረም ገንዘብና ተጫዋች ሊያቀርቡ ተዘጋጅተዋል
ባየርን ሙኒክ የቶተንሃሙን ሃሪ ኬን ለማስፈረም የክለቡ ክብረ ወሰን የሆነ 80 ሚሊዮን ዩሮ ሊያወጣ እንዳቀደ ስካይ ስፖርትስ ዘግቧል።
የ30 ዓመቱ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አምበል ወደ ባየርን ሊያቀና እንደሚችል ሲዘገብ ቆይቷል።
ሰኞ ዕለት የቶተንሃምና ባየርን ባለሥልጣናት ተገናኝተው ቢያወሩም ከስምምነት እንዳልደረሱ የዘገበው ደግሞ አትሌቲክ ነው።
ቶተንሃም ከሃሪ ኬን ሽያጭ የሚያገኘውን ገንዘብ ተጠቅሞ አይቮሪ ኮስታዊው ፍራንክ ኬሲዬ እና ፈረንሳዊው ክሌሜንት ሌንግሌን ከባርሴሎና ሊያስፈር እንዳቀደ ሙንዶ ዲፖርቲቮ ፅፏል።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት በርካታ ተጫዋቾችን ለማምጣት ያቀደው ቶተንሃም 50 ሚሊዮን ፓውንድ የተገመተውን የኖቲንግሃም ፎረስቱን የ22 ዓመት የፊት መስመር ተጫዋች ብሬናን ጆንሰን ሊያስፈርም ይችላል የሜል ዘገባ።
ከቼልሲ ባለቤቶች አንዱ የሆኑት ቶድ ቦህሊ የፈረንሳዩን አምበል ኪሊያን ምባፔ ከፓሪ ሳን ዠርማ ለማስፈረም ማቀዳቸውን የኢንዲፔንደንት ዕትም ይጠቁማል።
ሰውየው ምባፔን ለማምጣት ከገዘንብ በተጫማሪ ተጫዋች ለማቅረብ ቢያቅዱም ከባርሴሎና ፉክክር ይጠብቃቸዋል።
በተያያዘ ቼልሲ ቤልጂየማዊው አጥቂ ሮሜሉ ሉካኩን ለጁቬንቱስ ሰጥቶ ሰርቢያዊውን አጥቂ ዱሳን ቭላሆቪች ሊያስፈረም እንደሻተ ፋብሪዚዮ ሮማኖ በማሕበራዊ ሚድያ ገፁ ለጥፏል።
በርካታ ተጫዋቾችን እየሸጠ እየለወጠ የሚገኘው ቼልሲ የእንግሊዛዊው ተከላካይ ሌቪ ኮልዌልን ውል ለስድስት ዓመት አራዝሟል።
ፒኤስጂ፤ የኢንትራኽት ፍራንክፈርቱን 24 ዓመት ፈረንሳዊ አጥቂ ሮንዳል ኮሎ ሙዋኒ ለማስፈረም እንዳሰበ የፈረንሳዩ ሌኢኪፕ ጋዜጣ አስነብቧል።
እንደ ሜል ዘገባ ከሆነ 50 ሚሊዮን የተገመተውን የሳውዝሃምፕተኑን ቤልጂየማዊ አማካይ ሮሜዮ ላቪያ ለማስፈረም ሊቨርፑል አዲስ ጨረታ ለማስገባት ሲያቅድ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቼልሲን ፍላጎታቸውን አሳይተዋል።
ዌስት ሃም የሳውዝሃምፕተኑን አማካይ ጄምስ ዋርድ ፕራውስ ለማስፈረም ያቀረበው ጥያቄ ለሁለተኛ ጊዜ ውድቅ መሆኑን ተከትሎ ሃሰሳውን ሊያቋርጥ እንደሚችል የዘገበው ደግሞ ጋርዲያን ነው።
የጣሊያኑ ኢንተር ሚላን የ24 ዓመቱን አጥቂ ጂያንሉካ ስካማካ በ17 ሚሊዮን ፓውንድ ለማስፈረም ያቀረበው ጥያቄ በዌስት ሃም ውድቅ ሆኖበታል ይላል የቶክስፖርት ዘገባ።
በርንሊ የ23 ዓመቱን ቤልጂማዊ አማካይ ሳምቢ ሎኮንጋ በውሰት ለአንድ የውድድር ዘመን ለማምጣት ከአርሰናል ጋር ድርድር ጀምሯል።
ፓሪ ሳን ዠርማ ጣሊያናዊው የ30 ዓመት አማካይ ማርኮ ቬራቲን በ25 ሚሊዮን ፓውንድ እንግዛው ጥያቄ ከሳዑዲው አል-ሂላል ቢቀርብላቸውም አለመቀበላቸውን ፋብሪዚዮ ሮማኖ ገልጧል።
የሳዑዲ አረቢያው አል-ሂላል የናፖሊውን ናይጄሪያዊ አጥቂ ቪክተር ኦሲምሄን በ140 ሚሊዮን ዩሮ ለመግዛት ጥያቄ ማቅረባቸውን የስካይ ስፖርት ዘገባ ጠቁሟል።
ቼልሲ የብራይተኑን የ25 ዓመት ስፔናዊ ግብ ሳንቼዝ ጠባቂ ለማስፈረም ጥያቄ ቢያቀርቡም ብራይተን እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
ባለፈው የውድድር ዘመን ከእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የወረደው ሳውዝሃምፕተን አጥቂ የሆነው ቼ አዳምስን ለማስፈረም ኤቨርተን፣ ዎልቭስና ቦርንመዝ ተሰልፈዋል።
የ26 ዓመቱ ፈረንሳዊ የክንፍ መስመር ተጫዋች ወደ ፓሪ ሳን ዠርማ ከሄደ፤ ባርሴሎና ፖርቹጋላዊው አጥቂ ጃዎ ፌሊክስን ከአትሌቲኮ ማድሪድ ሊያስፈርም እንደሚችል የስፔኑ ስፖርት ፅፏል።