ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ የዩክሬን ከተሞችን እያጠቃች ባለበት ወቅት ዜሌንስኪ የጦር ግንባር ጎበኙ
የዩክሬኑ ፕሬዝዳናት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ለወራት የዘለቀ ውጊያ ሲደረግበት ወደ ነበረው ባክሃሙት ተጉዘው ጉብኝት አድርገዋል።
በምስራቅ የዩክሬን ክፍል የሩሲያ ጦር መልሶ ለማንሰራራት በሚያደርገው ጥረት የጦርነት ማዕከል የነበረችው ከተማዋ ክፉኛ ተጎድታለች።
ይህ የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት የተደረገው የሩሲያ ጦር በዩክሬን ከተሞች ተከታታይነት ያለው ጥቃት እየፈጸሙ ባሉበት ሰዓት ነው።
በዚህም ሳቢያ ቢያንስ ስምንት ሰዎች ከኪየቭና ዛፖርዚያ አቅራቢያ ሰምንት ሰዎች ተገድለዋል።
ዩክሬን 16 የሩሲያ ድሮኖችን መትታ መጣሏን ገልጻለች።
ከዩክሬን ዋና ከተማ አቅራቢያ በተማሪዎች ማደሪያ ላይ በተደረገ ጥቃት ሰባት ሰዎች ተገድለዋል።
በደቡባዊ ምስራቋ ዛፖርዚያ ከተማ በተፈጸመ ሌላ የሮኬት ጥቃት አንድ ሰው ሞቶ 25 ሰዎች ተጎድተዋል። የአካባቢው መሪዎች የተጎጂዎች ቁጥር ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል ገልጸዋል።
ሩሲያ በሲቪል ሰዎች ላይ የምታደርሰውን ጥቃት ያወገዙት ዜሌንስኪ በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል የሩሲያ ጦር ከ7 ወራት በላይ ለመቆጣጠር ትግል ሲያደርገበት የነበረውን የጦር ግንባሮች ጎብኝተዋል።
በፕሬዝዳንቱ ጸህፈት ቤት በተለቀቀ አንድ ቪዲዲዮ ላይ ዜለንስኪ ለወታደሮች ሜዳሊያ ሲያጠልቁ ይታያል። “በምስራቃዊ የሀገራችን ክፍል በዶምባስ ተገኝቼ ለጀግኖች ሽልማት በመስጠቴ ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል።
የዩኬ የወታደራዊ ስለላ ተቋም ትናንት ረቡዕ ባወጣው መረጃ በምራባዊ ባክሙት ግዛት ዩክሬን እያደረገች ያላቸው መልሶ ማጥቃት ውጤት እያስገኘና ሩሲያ የነበራትን የተገደበ እንቅስቃሴ እንድታጣ እያደረገ ነው ብሏል።
በሌላ በኩል በክሬሚያ የሚገኙ የሩሲያ ባለስልጣናት ፕሬዝዳንት ፑቲን ከተማዋን ከጎበኟት በኃላ የተሰነዘረውን የድሮን ጥቃት ማክሸፋቸውን ገልጸዋል።
በሰሜናዊ ክሪሚያ ሚሳኤሎችን እንዳወደመች የገለጸችው ዩክሬን ግን በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠችም።
ትላንት የዩክሬን ከተሞች ቀደም ብሎ በድሮኖች በኃላም በሚሳኤሎች ሲደበደቡ ቆይተዋል።
በኪዮቭ አቅራቢያ የተማሪዎች ማደሪያ የላይኛው ክፍል ከተደበደበ በኃላ በፍርስራሾች ውስጥ የቀሩ ሰዎች ካሉ የመፈለግ ስራ እየተሰራ ነው።
በጥቃቱ የአምቡላንስ አሽከርካሪን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ሲሞቱ ዘጠኝ ሰዎች ተጎድተዋል። ከተጎጂዎቹ የ11 ዓመት ታዳጊ ልጅ ይገኝበታል።
ይህ ከሆነ ከሰዓታት በኃላ በዛፓዚያ ከተማ በለዘጠኝ ወለል ህንጻዎች ላይ የተተኮሰ ሚሳኤል ሁለት ህንጻዎችን በእሳት አያይዟል። ባለስልጣናቱ በዚህ ጥቃት አንድ ሰው በሆስታል ህይወቱ እንዳለፈና 25 ሰዎች ደግሞ እንቆሰሉ ገልጸዋል።
ይህ የሩሲያ ጥቃት የተሰነዘረው የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ባለ 12 ነጥብ የሰላም ዕቅዳቸው ላይ ለመምከር ያደረጉትን የሞስኮ የሁለት ቀናት ጉብኝት ካጠናቀቁ በኃላ ነው።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ሁልጊዜ “በሞስኮ የሆነ ሰው ‘ሰላም’ የሚለውን ቃል ለማስማት ሲሞክር” ጥቃት እንዲሰነዘር ትዕዛዝ ይተላለፋል ብለዋል።