በተባበሩት መንግሥታት የሚመራ ቡድን በሸራሮ አካባቢ ጉብኝት ማድረግ ሳይችል መቅረቱ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, RW
ባለፈው ሳምንት ወደ ትግራይ ለጉብኝት የሄደው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚመራ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ልዑካን ቡድን ሸራሮ አካባቢ በሚገኝ ስፍራ በኤርትራ ወታደሮች ክልከላ ገጥሞት እንደነበር ተነገረ።
ቡድኑ ወደ ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ለጉብኝት ተንቀሳቅሶ እንደነበረ እና የእርዳታ ተደራሽነት ለመታዘብ እንደሞከረ ቢቢሲ ከአካባቢው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከልዑካን ቡድኑ ጋር አብረው የተጓዙት የዞኑ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ አቶ ተክላይ “አድመይቲ በሚባል አካባቢ ልዩው ቦታ ዓዲ-አሰር ለማለፍ ሲሞክሩ የኤርትራ ሠራዊት ባቆመው ኬላ ላይ አስቁመው ‘ከዚህ ማለፍ አትችሉም’ ሲሉ ከለከሏቸው” ሲሉ ያስረዳሉ።
አክለውም ቡድኑ እንዲመለስ መደረጉን ሲናገሩ “እንድናልፍም ሊፈቅዱልን አልቻሉም። መሳሪያ እስከማወዛወዝም ደርሰው ነበር” ብለዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ ባልደረሰባቸው መንደሮች ሊደረግ የታቀደው ጉብኝት በዚህ ምክንያት ቢሰረዝም፣ ቡድኑ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ተጉዞ በክልሉ ውስጥ ያለውን የእርዳታ ተደራሽነት እና የአቅርቦት ሁኔታ ለመመልከት መቻሉ ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ- ኢትዮጵያ) ኃላፊ ሚሼል ሳድ የልዑካን ቡድኑ አዳዲስ ተደራሽ ያልሆኑ ቦታዎችን ማየቱን እና “በጣም የተሳካ ጉብኝት” እንደተደረገ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ስላጋጠመ ክስተት ሲያስረዱም “የልዑካን ቡድኑ ከዚህ ቀደም ተደራሽ ያልሆኑትን አብዛኞቹን አካባቢዎች መጎብኘት ችሏል። ከተጠቀሰው አካባቢ [ገመሃሎ] ካጋጠመን በስተቀር የተሳካ ጉብኝት ነበር። ምናልባት የመረጃ ክፍተት የነበረ ይመስለኛል። በተጠቀሰው አካባቢ እንደታሰበው የልዑካን ቡድኑ ሊቀጥል አልቻለም” ብለዋል። ለት ያስረዳሉ።
“አንዳንድ ቀበሌዎች ከተደራሽነት ውጪ ሆነው ነው የቆዩት” ያሉት ኃላፊው ጽሕፈት ቤታቸው እነዚህን ቦታዎች በቀይ ምልክት እንዳስቀመጣቸው እና ወደ መሰል አካባቢዎች የሚደረገው ጉዞ ልዩ ትኩረት የሚሻ እንደሆነ ገልፀዋል።
“ይህ ዞን ከጦርነት በኋላ በሚፈጠር ቀውስ ውስጥ ነው ያለው። በእንደዚህ አይነት አካባቢ መሥራት ጦርነት በሌለበት አካባቢ ውስጥ ከመስራት ጋር የሚመሳሰል አይደለም። ብዙ መሰናክሎች ያጋጥማሉ፤ ሠራተኞቻችን በየቀኑ የሚያጋጥማቸው ይሄው ነው። እና ይህን ክስተት እንደ ትልቅ ችግር አላየውም” ብለዋል።
አቶ ተክላይ ገብረመድኅን በበኩላቸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ-ኢትዮጵያ) ምክትል ኃላፊ የተመራው የልዑካን ቡድን በሸራሮ ከተማ ከአካባቢው አስተዳደር እንዲሁም በቦታው ከሚገኘው የኢትዮጵያ ሠራዊት ወታደራዊ አዛዦች ጋር መወያየቱን ገልጸዋል።
የጎዞው ዓላማም ለእርዳታ አቅርቦት ተደራሽ ባልሆኑ አካባቢዎች የሚገኝ ሕዝብ እና የአርሶ አደሮችን ሁኔታ ለመታዘብ እንደነበረ አስተዳዳሪው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ተክላይ አክለውም “የዓለም ጤና ድርጅት ተወካዮችም አብረው ስለነበሩ፣ ነዋሪው የሕክምና አገልግሎት እያገኘ እንዳልሆነ ለማሳየት ያለመ ነበር። የኤርትራ ኃይሎች በአካባቢው ስላሉ እርዳታ ልናቀርብላቸው አልቻልም የሚል ጉዳይ የውይይቱ አካል ነበር” ብለዋል።
የኦቻ-ኢትዮጵያ ኃላፊ ሚሼል ሰዓድ በበኩላቸው የልዑካን ቡድኑ ባልደረቦቻቸውን እና በርካታ የሰብአዊ ተልእኮ ከሚያከናውኑ ድርጅቶች የተውጣጡ አካላትን ያቀፈ እንደነበረ በማስታወስ ግንቦት 25 እና 26 በተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች እንደተንቀሳቀሰ ጠቅሰዋል።
ቡድኑ ከነዋሪዎች፣ ከአስተዳደሩ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የተወያየ ሲሆን፣ ጉብኝቱ ለቀጣይ ሥራቸው ጠቃሚ እንደነበርም ተናግረዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክላይ ለቢቢሲ ትግርኛ እንደተናገሩት የኤርትራ ሠራዊት በታሕታይ አዲያቦ ወረዳ የሚገኙ በርካታ መንደሮችን የተቆጣጠረ ሲሆን መፈናቀል፣ የእንስሳት ስርቆት እና የመሠረተ ልማት ውድመት እንደሚፈጸም ከሰዋል።
ቡድኑ ጉብኝት በሚያካሂድበት ጊዜ ስለመከልከሉ እንዲሁም የኤርትራ ሠራዊት አካባቢውን ተቆጣጥሮት ይገኛል በሚባለው ላይ ከኤርትራ መንግሥትን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ከሰላም ስምምነት በኋላ
የኦቻ-ኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚሼል ከጥቅምት 2015 ዓ.ም. የፕሮቶሪያው ስምምነት በኋላ በአጠቃላይ በትግራይ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መሻሻል አሳይቷል ይላሉ።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ዩኤስኤአይዲ ከአራት ወራት በፊት በትግራይ እርዳታ ተዘርፎ በገበያ እንደሚሸጥ የሚገልጽ ሪፖርት ስለደረሳቸው ወደ ክልሉ የሚያቀርቡት እርዳታ ማቆማቸው ይታወሳል።
በዚህም ምክንያት ሞት እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን በመዘገብ ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከሁለት ዓመታት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ በፕሪቶሪያ የተኩስ አቁም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
በስምምነቱ ላይም የውጭ ኃይሎች እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ያልሁኑ ታጣቂዎች ከትግራይ ክልል ጠቅልለው እንዲወጡ የሚጠይቅ ውሳኔ ተካቷል።
የኤርትራ ወታደሮች በትግራዩ ጦርነት ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው በክልሉ ውስጥ ተሰማርተው የነበረ ሲሆን፣ ስምምነቱን ተከትሉ ከአብዛኛው የትግራይ ክፍል ለቀው እንደወጡ ይነገራል።
ነገር ግን በምሥራቅ እና ሰሜናዊ ምዕራብ ትግራይ አንዳንድ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ እና የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ የትግራይ አመራሮች ደጋግመው እየገለጹ ነው።
ከሳምንት በፊት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ “የኤርትራ ኃይሎች የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ቁጥጥር እና ክትትል ሥራውን እንዳያከናውን ከለከሉ” ማለታቸውን ትግራይ ቲቪ ዘግቧል።
የኤርትራ መንግሥትም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን በዚህ ጉዳይ ላይ አስካሁን የሰጡት አስተያየት የለም።












