በስምንተኛው የአፍሪማ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ ድምጻውያን አሸነፉ

ኢትዮጵያውያን ድምጻውያን በዘንድሮው የመላው አፍሪካ የሙዚቃ ሽልማት (አፍሪማ) በተለያዩ የሙዚቃ ዘርፎች ማሸነፋቸው ተሰማ።
በስምንተኛው የአፍሪማ ሽልማት በተለያዩ ዘርፎች ታጭቶ የነበረው ካሥማሰ 'ሰዋሰው' በተሰኘ ሥራው በምርጥ የምሥራቅ አፍሪካ አርቲስት ዘርፍ ማሸነፍ ችሏል።
ካሥማሰ ታጭቶባቸው የነበሩት ዘርፎች ምርጥ የምሥራቅ አፍሪካ አርቲስት እና ምርጥ የአፍሪካ አነቃቂ ሙዚቃ ሲሆን በምርጥ የአፍሪካ የሙዚቃ ቪዲዮ ዘርፍ 'ሰዋሰው' በተሰኘው ሙዚቃው ማራናታ ተገኘ ታጭቶ ነበር።
ሌላው አሸናፊ ጉቱ አበራ ሲሆን ‘ዴሚ’ በተሰኘው ዘፈኑ በምርጥ የአፍሪካ ጃዝ አርቲስት/ጥምረት ዘርፍ አሸንፏል።
ጉቱ በትዊተር ሰሌዳው ላይ እንዳሰፈረው 'ዴሚ' በተሰኘው ሙዚቃው ምርጥ የአፍሪካ ጃዝ አርቲስት/ጥምረት በማሸነፉ ደስታ እንደሚሰማው ገልጿል። "በአፍሪካ የተከበረ ውድድር ማሸነፍ ክብር ነው" ሲልም ጽፏል።
በዚህ ዘርፍ አዲስ ለገሰ ‘እንጃ’ በተሰኘው ዘፈኑ ሲካተት ጃኖ ባንድ በ ‘ዘብናናው’ ሙዚቃም ታጭተዋል።
በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው ስምንተኛው ‘ኦል አፍሪካ ሚውዚክ አዋርድ’ ወይም አፍሪማ ውድድር ላይ ቴዲ አፍሮ ፣ ቤቲ ጂ፣ ሔዋን ገብረወልድ፣ አዲስ ለገሰ እና ሌንጮ ገመቹ በተለያዩ ዘርፎች የታጩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ።
በዘንድሮው የአፍሪማ ውድድር ቤቲ ጂ በምሥራቅ አፍሪካ ምርጥ ድምጻዊት ዘርፍ ‘ሰማይ’ በተሰኘው ዘፈኗ ፣ አዲስ ለገሰ ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ ድምጻዊ ዘርፍ ‘እንጃ’ በተሰኘው ዘፈኑ ታጭተዋል።
በምሥራቅ አፍሪካ ምርጥ ድምጻዊት ዘርፍ ሔዋን ገብረወልድ ‘ሼሙና’ በተባለው ሙዚቃዋ ትገኛለች።
በምርጥ የአፍሪካ ባንድ ሥር ጃኖ በ ‘ዘብናናው’፣ በምርጥ የአፍሪካ ሬጌ፣ ራጋ እና ዳንሶል አርቲስት/ጥምረት ዘርፍ ቴዲ አፍሮ በ ‘ናዕት’ ታጭተዋል።
በምርጥ የአፍሪካ ባህላዊ ሙዚቃ አርቲስት/ጥምረት ዘርፍ ቤቲ ጂ በ‘ሰማይ’ ዘፈኗ፣ ሌንጮ ገመቹ በ ‘ሰግሊ’ እና በዓመቱ አዲስ ታዋቂ ዘርፍ ደግሞ ሔዋን ገብረወልድ ‘ሼሙና’ በተባለው ሙዚቃ ታጭተዋል
በዘንድሮው አፍሪማ ናይጄርያውያኑ አሳኪ፣ በርና ቦይ እና ዴቪዶ በርካታ ሽልማቶች ሰብስበዋል።
አሳኪ የዓመቱ አዲስ ታዋቂ ዘርፍ አሸናፊ ሲሆን፣ በርና ቦይ የዓመቱ ምርጥ አርቲስት፣ ዴቪዶ የዓመቱ ምርጥ አነቃቂ የአፍሪካ አርቲስት፣ ዊዝኪድ ደግሞ የዓመቱ ምርጥ የምዕራብ አፍሪካ አርቲስት ተብለዋል።
‘ታላ’ የተሰኘው የአይቮሪ ኮስታዊው ዲቢ ቢ ሙዚቃ የዓመቱ ምርጥ ዘፈን ተብሏል።
ሴኔጋል አፍሪማን በማዘጋጀት የመጀመሪያዋ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ አፍሪካዊ አገር ሆናለች።
ጥቂት ስለ አሸናፊዎቹ ካሥማሰ እና ጉቱ አበራ
ጉቱ የተወለደው በኦሮሚያ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ መንዲ ከተማ ውስጥ ነው። የ16 አመት ታዳጊ ሆኖ ነበር ቤተሰቦቹ በስደት ወደሚኖሩባት ኖርዌይ ከ12 ዓመት በፊት የሄደው።
ከልጅነቱ ጀምሮ ከፍተኛ የሙዚቃ ፍላጎት እንደነበረው የሚናገረው ጉቱ፣ ኖርዌይ ከሄደ በኋላ ወደ ጥሩ ሙዚቀኞች እየሄደ ሙዚቃን በመማር አዲስ ነገር ለመፍጠር እና በተለይም የፊውዥን ሙዚቃዎች ላይ አተኩሮ መሥራት ጀመረ።
በሶሻል ወርክ እና አንትሮፖሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪውን የያዘው ጉቱ፣ በሞያው ሶሻል ወርከር ነው። የትምህርት ዝግጅቱም ለሙዚቃ ሥራው እገዛ እንዳደረገለት ይናገራል፡፡
ሌላው አሸናፊ ካሥማሰ የመድረክ ስሙ ነው። እናት አባቱ ያወጡለት፣ መዝገብ የያዘው ስሙ ደግሙ ፍቅሩ ሰማ ይሰኛል። ሰባት ሥራዎችን የያዘ 'ግማሽ አልበም' ለሙዚቃ አድማጮች አቅርቧል።
ካሥማሰ ሥራውን ያቀረበው በሂፕ ሆፕ የሙዚቃ ስልት ሲሆን በርከት ያሉት ሥራዎቹን ከቀደሙ ስመ ጥር ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ስራ ጋር አዋህዶ ሰርቷቸዋል።
አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው ካሥማሰ ትምህርቱን በቅዱስ ዮሴፍ፣ ከዚያም ንግድ ሥራ ኮሌጅ፣ ኮሜርስ በመግባት ተከታትሏል።
በንግድ ሥራ ኮሌጅ ማርኬቲንግ የተማረው ካሥማሰ ትምህርቱ ከጨረሰ በኋላ ጊዜውን የሰጠው ለሙዚቃ ነው።
ካሥማሰ በአፍሪማ የሙዚቃ አዋርድ ካሸነፈበት ‘ሰዋሰው’ ሥራው ሌላ ከጃማይካዊው ፕሮቶጄ ጋር የተጣመረበት ‘መላ መላ’ የተሰኘ ነጠላ ዜማውም ተወዳጅ ሆኗል።












