እስራኤል የፍልስጤም የእርዳታና ሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን አሸገች

ታትሟል

የእስራኤል ወታደሮች የፍልስጤም የእርዳታ እና የሰብዓዊ መብት ተቋማትን አሸጉ።

እስራኤል ከአንድ ዓመት በፊት ተቋማቱን በሽብርተኝነት ልትፈርጅ እንደምትችል አስጠንቅቃ ነበር።

ወታደሮቹ በእስራኤል ቁጥጥር ስር በሚገኘው ዌስት ባንክ የሚገኙትን እነዚህን ቢሮዎች በማለዳ በከፍተኛ ቁጥር የከበቡ ሲሆን መታሸጋቸውን የሚያሳዩ ማሳሰቢያዎችን ለጥፈዋል።

የእስራኤል ባለሥልጣናት ተቋማቱ የአንድ ታጣቂ ቡድን ግንባር ናቸው ሲሉ ከሰዋል።

ክሱ በቡድኖቹ ውድቅ የተደረገ ሲሆን ለተቋማቱ ድጋፍ የሚሰጡ የአውሮፓ ለጋሽ አገራትም በተመሳሳይ ክሱን አስተባብለውታል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም የሆነው አል-ሀቅ የእስራኤል ወታደሮች ቢሮውን ለመውረር  ለሊት 9 ሰዓት ገደማ ወደ ራማላ ከተማ እንደገቡ ገልጿል።

እንዲሁም ከአዳሜር፣ ቢሳን የምርምር እና ልማት ማዕከል፣ ዲፌንስ ፎር ቺልድረን፣ የግብርና ሠራተኞች ኮሚቴ ኅብረት እንዲሁም የፍልስጤም የሴቶች ኮሚቴ ኅብረት ተመሳሳይ ብርበራ ተደርጎባቸዋል።

ወታደሮቹ የተለያዩ ዕቃዎችን ከወሰዱ በኋላ ወደ አል ሃቅ ቢሮ ማንም እንዳይገባ በሮቹን በይደዋል።

እንዲሁም ድርጅቱ በአስቸኳይ መዘጋቱን የሚያሳይ እና አስተዳዳሪዎቹን የሚያስጠነቀቅ የትዕዛዝ ወረት በሩ ላይ ለጥፈውም ሄደዋል።

ባለፈው ጥቅምት ወር እስራኤል ስድስት የፍልስጤም መብት ተሟጋች ድርጅቶችን ለፍልስጤም ሕዝባዊ ነጻ አውጪ ግንባር ገንዘብ ይረዳሉ በሚል በአሸባሪነት መፈረጇ ይታወሳል።

"ድርጅቶቹ የአሸባሪ ድርጅቱን አላማ ለማራመድ፣ ለማጠናከር እና ተዋጊዎችን ለመመልመል በሰብአዊ ተግባራትን ጥላ ስር በመሸሸግ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ" ሲሉ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ ሐሙስ ቀን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

እስራኤል እያቀረበች ያለውን ክስ የሚደግፍ የሰነድ ማስረጃ ለማቅረብ እንደማትችል ለቢቢሲ የተናገረች ሲሆን፣ ለዚህም ሰነዶቹ ምስጢራዊነት ያላቸው ናቸው የሚል ምክንያት ሰጥታለች።

የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶቹ ተቋማቱ እስራኤል በጦር ወንጀል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠያቂ እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት የሚደግፉ በመሆናቸው ዝም ለማሰኘት የተወሰደ እርምጃ ነው ሲሉ ያምናሉ።

"እኛን ዝም ለማሰኘት የጦርነት ግፍ ፈፅመውብናል" ሲሉ የአል-ሀቅ ዋና ዳይሬክተር ሻዋን ጃባሪን ትዊተር ላይ ባሰፈሩት ቪዲዮ ላይ ተናግረዋል።

"ሥራችንን እንቀጥላለን፣ አናቆምም፣ የሰብአዊ መብት መሟገት ተግባር ሥራ ብቻ አይደለም" ሲሉም አክለዋል።

እስራኤል ክሷን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ባለማቅረቧ ፈረንሳይ እና ጀርመንን ጨምሮ ዘጠኝ የአውሮፓ አገራት ለድርጅቶቹ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም በበኩሏ በደርጅቶቹ ላይ የተለጠፈው የሽብርተኝነት ፍረጃ እንደሚያሳስባት ገልጻለች።