ድምጽ አንሰጥም ያሉ ዴሞክራት እንደራሴዎች እንዲያዙ ሪፐብሊካኖች ወሰኑ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የምርጫ ክልልን በድጋሚ የሚያዋቅር ረቂቅ ላይ ድምጽ ላለመስጠት ከቴክሳስ ግዛት የወጡ የዴሞክራት ሕግ አውጭዎች እንዲታሰሩ የቴክሳስ ሪፐብሊካኖች ውሳኔ አሳለፉ።

የምርጫ ክልል በድጋሚ እንዲዋቀር የቀረበው ዕቅድ ለሪፐብሊካኖች የሚያዳላ ሲሆን፣ ዴሞክራቶች በረቂቁ ላይ ድምጽ ላለመስጠት የቴክሳስ ግዛትን ለቀው ወጥተዋል።

በአሥራዎቹ የሚቆጠሩት እነዚህ ዴሞክራቶች ተይዘው እንዲታሰሩ ሲሉ የሪፐብሊካን የግዛቲቱ የምክር ቤት አባላት ድምጽ ሰጥተዋል።

ከውሳኔው በኋላ ሪፐብሊካኑ የቴክሳስ አገረ ገዥ ግሬግ አቦት "የቴክሳስ ሕዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት ጥለው የሄዱ የምክር ቤት አባላት ተፈልገው እንዲያዙ እና ወደ ምክር ቤት እንዲመለሱ" ሱሉ ለፀጥታ ኃይሎች ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ዴሞክራቶች ከምክር ቤቱ የቀሩበትን ቀን እና ወጪውን በማስላት በጉቦ እንደሚከሰሱም አገረ ገዢው አክለዋል።

የምርጫ ክልልን በድጋሚ የሚያዋቅረው ረቂቅ በዋሽንግተን ዲሲ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስት ተጨማሪ መቀመጫዎችን ለሪፐብሊካን ደጋፊዎች እንዲሰጡ ያመቻቻል።

በአሁኑ ወቀት የአሜሪካ ምክር ቤት ሪፐብሊካኖች በጥቂት የወንበር ብልጫ ይመራሉ።

ረቂቁን ለማሳለፍ ከቴክሳስ ግዛት 150 የሕግ አውጪ አባላት ቢያንስ ሁለት ሦስተኛው መገኘት አለባቸው።

50 ዴሞክራት እንደራሴዎች ከቴክሳስ ከወጡ በኋላ ምልዐተ ጉባዔ ሳይሟላ ቀርቷል። አብዛኞቹ ዴሞክራቶች ወደ ኤልኖይስ ነው የሸሹት።

የኤልኖይስ አገረ ገዢ ጄቢ ፕሪትከር "ለእያንዳንዳቸው ከለላ ለመስጠት ሁሉንም ነገር አደርጋለሁ" ብለዋል።

ዴሞክራቶቹ ለሁለት ሳምንታት ያህል ወደ ቴክሳስ መመለስ አይፈልጉም። በእነዚህ ሁለት ሳምንታት ልዩ የምክር ቤት ጉባዔ ማካሄጃ ጊዜ ይጠናቀቃል።

ዴሞክራቶቹ እንዲያዙ መወሰኑን ተከትሎ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ማንኛውም ዓይነት ክስ አይመሠረትባቸውም።

የቴክሳስ ዴሞክራት ሕግ አውጪ ሮን ሮይኖልድስ ለቢቢሲ እንደገለጹት የእስር ማዘዣው "ከማስፈራራት የዘለለ" አይደለም።

የሕዝብ እንደራሴዎቹ በምክር ቤት በማይገኙበት እያንዳንዱ ቀን 500 ዶላር ቅጣት ይጣልባቸዋል።

"ገንዘቡን ወስደው ምክር ቤት የማይመጡ ከሆነ ጉቦ መቀበል ነው" ሲሉ የቴክሳስ አገረ ገዥ አስጠንቅቀዋል።

እንደራሴዎቹ እንዲታሰሩ ያስተላለፉት ውሳኔ ሁሉም እንደራሴዎች እስከሚመለሱ ድረስ ጸንቶ እንደሚቆይም አክለዋል።

የቴክሳስ ሪፐብሊካን ሕግ አውጪ ብራያን ሀሪሰን ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ የምርጫ ክልልን በድጋሚ የሚያዋቅረው ረቂቅ በዘር መስመር የተከፋፈለ ነው የሚለው የዴሞክራቶች መከራከሪያ ውሃ አይቋጥርም።

"ረብ የለሽ፣ ጨለምተኛ፣ ተዓማኒነት የጎደለው እና ትርጉም አልባ ነው። እነዚህ ዴሞክራቶች ታስረው እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል" ብለዋል።

ሪፐብሊካኑ የቴክሳስ ዐቃቤ ሕግ ኬን ፓክስተንም በምክር ቤት ያልተገኙ ዴሞክራት እንደራሴዎች እንደሚታሰሩ ዝተዋል።

የቴክሳስ ሪፐብሊካኖች ከምክር ቤቴ 38 መቀመጫዎች መካከል 25ቱን ይዘዋል።

የምርጫ ክልልን በድጋሚ የሚያዋቅረው ረቂቅ 30 መቀመጫዎች እንዲያገኙ እንደሚረዳቸው ተስፋ ያደርጋሉ።

ሪፐብሊካኖች እንዳደረጉት ሁሉ ዴሞክራቶችም በኤልኖይስ፣ ኒው ሜክሲኮ እና ኔቫዳ የምርጫ ክልሎች በድጋሚ ተዋቅረው ለዴሞክራቶች ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ ችለዋል።

እንደ ኒው ዮርክ፣ ካሊፎርያ፣ ኮሎራዶ እና ዋሽንግተን ያሉ ግዛቶች ግን ለገለልተኛ ወገን ውክልና ሰጥተዋል።

በቴክሳስ ምክር ቤት የሚያጡትን መቀመጫ ለማካካስ በሌሎች ግዛቶች የምርጫ ክልል ዳግመኛ እንደሚያዋቅሩ የሌሎች ግዛቶች ዴሞክራቶች አስታውቀዋል።

በተመለደው አሠራር መሠረት የአሜሪካ ግዛቶች በየ10 ዓመቱ የምርጫ ክልልን መልሰው ያዋቅራሉ።

ከአምስት ዓመት በፊት በ2020 መልሶ ማዋቀር የተደረገ ሲሆን፣ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ዳግመኛ ለመለወጥ መሞከር የተለመደ አካሄድ አይደለም።