ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ኪሳራ ያጋጠመውን ባንክ የደንበኞች ተቀማጭ ገንዘብ ተቆጣጠረች
የአሜሪካ ተቆጣጣሪዎች ከፍተኛ ኪሳራ የገጠመውን ሲልከን ቫሊ ባንክን ዘግተው የደንበኞቹን ተቀማጭ ገንዘብ ተቆጣጠሩ።
ባንኩ በሁለት አስርት ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ውድቀትም ውስጥ በመግባቱ ነው ይህ ውሳኔ የተላለፈው።
ባንኩ የአሜሪካ መንግሥትን ቦንድን የሸጠው በከፍተኛ የወለድ ተመን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የገጠመውን ኪሳራ ለመሸፈን ገንዘብ ለማሰባሰብ እየሞከረ እንደነበረ ተገልጿል።
ባንኩ 2.25 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ እየሞከረም ነበር።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የባንኩ ደንበኞች ገንዘባቸውን ማውጣት እንደጀመሩና የባንክ ሴክተሩን ሁኔታም ስጋት ላይ መጣሉም ተነግሯል።
ባለስልጣናቱ ይህንን እርምጃ የወሰዱት “ተቀማጭ ገንዘብ ያላቸውን” ደንበኞች ለመጠበቅ ነው ብለዋል።
በካሊፎርኒያ የሚገኙ ተቆጣጣሪዎች የሲሊከን ቫሊ ባንክ ‘ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እና ኪሳራ አጋጥሞታል’ ሲሉም ተናግረዋል።
እስከ 250 ሺህ ዶላር የሚደርስ ተቀማጭ ገንዘብን የሚጠብቀው የፌደራል ዲፖዚት ኢንሹራንስ ኮርፖሬሽን (ኤፍዲአይሲ) በባንኩ ውስጥ 175 ቢሊዮን ዶላር ተቀማጭ ገንዘብ መቆጣጠሩን ገልጿል። መጠኑም በአሜሪካ 16ኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጠዋል።
የባንኩ ቢሮዎች እንደሚከፈትና ገንዘባቸውን በኢንሹራንስ ሽፋን ያስቀመጡ ደንበኞች እስከ መጪው ሰኞ ባለው ጊዜ ገንዘባቸውን እንደሚያገኙና የባንኩን ንብረት በመሸጥ የሚሰበሰበው ኢንሹራንስ ለሌላቸው ደንበኞች እንደሚደርስ ተነግሯል።
ይህ ዜናም ባለሃብቶች እና ደንበኞች ከባንኩ እንዲሸሹ አድርጓቸዋል።
በዚህ ሳምንት ሀሙስ የባንኩ የአክሲዮኖች ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ፣ 60 በመቶ አሽቆልቁሏል።
ይህንንም ተከትሎ ሌሎች ባንኮች ተመሳሳይ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል በሚል ስጋት በያዝነው ሳምንት ሐሙስ እና አርብ የባንክ አክሲዮኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ በመጠነ ሰፊ ሁኔታ ለሽያጭ ቀርበዋል።
አርብ ዕለት በዋሽንግተን ንግግር ያደረጉት የአሜሪካ የግምጃ ቤት ጸሐፊ ጃኔት የለን በሲልከን ቫሊ ባንክ እና በሌሎች ባንኮች በቅርብ ጊዜ ያጋጠሙ ክስተቶችን እየተከታተልን ነው ብለዋል።
የግምጃ ቤቱ ጸሃፊ ከባንክ ከፍተኛ ተቆጣጣሪዎች ጋር የተገናኙ ሲሆን “ የባንክ ተቆጣጣሪዎች ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስዱ ሙሉ እምነት እንዳላቸውና የባንክ ስርዓቱ ጠንካራ መሆኑን ገልጸዋል።