የሩስያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን የአገሪቱ ጦር ማፈግፈጉን በተመለከተ ያወጡትን ዘገባ አነሱ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሩስያ መገናኛ ብዙኃን ትላንት ሰኞ ወታደሮች ከአንድ በሩስያ ቁጥጥር ስር ካለ የዩክሬን ግዛት መውጣቱን ዘግበው ነበር። ሆኖም ይህንኑ ዘገባ መልሰው አንስተዋል።
መገናኛ ብዙኃኑ ለዘገባቸው የሀገሪቱን የመከላከያ ሚኒስቴር የጠቀሱ ሲሆን ሚኒስቴሩ ወታደሮች “ይበልጥ ምቹ ወደ ሆነ ቦታ” መዘዋወራቸውን ማስታወቁን አስታውቋል። ይህም ስፍራ ሩሲያ የተቆጣጠረቸው ምስራቃዊ ክፍል ነው።
እነዚህ ዘገባዎች ብዙም ሳይቆዩ ተነስተዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ዘገባዎቹ “ሀሰተኛ” ናቸው ያለ ሲሆን ዩክሬንንም ወቅሷል።
ዩክሬን ግን ይህ ትችት የሩስያ መንግሥት የከፍተብኝ የሀሰተኛ መረጃዎች ዘመቻ አካል ነው ብላለች።
እነዚህ ዘገባዎች ወጥተው ማሻሻያ ከተደረገበት ተመሳሳይ ቀን አንድ ዓመት በፊት የሩስያ ወታደሮች ኬርሶን ከተማን ጨምሮ በርካታ አከባቢዎችን ለቀው ወጥተው ነበር። በአካባቢው ያለው ወንዝ የሩስያና የዩክሬን ኃይሎችን ለይቷል።
ትላንት ማሻሻያ የተደረገበት ዘገባን የሩስያ መንግሥት መገናኛ ብዘኃን ሩስያ ወታደሮቿን ዲንፕሮ ወደ ተሰኘው ወንዝ ምስራቃዊ አቅጣጫ ላይ የቦታ ለውጥ አድርጋ ዳግም ማሰማራቷን አመላክተዋል። ይህም የተወሰኑ ወታደሮችን በመቀነስ በሌላ አካባቢ ለምታደርገው ዘመቻ ለመጠቀም ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ሩስያ ከዚህ ቀደም የያዘቻቸውን አከባቢዎች ለቃ ስትወጣ ተመሳሳይ አገላለጽ የያዙ ዘገባዎችን ተጠቅማለች።
የፕሬዝዳንት ፑቲን ጸህፈት ቤት - ክሬምሊን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቦ ጉዳዩ የመከላከያ ሚኒስቴር ነው ብሏል።
ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ የዩክሬን ጦር ጠንካራ ውጊያ የጀመረ ሲሆን ይህም እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ሞስኮ የጠቀለለችን የክሪሚያ ባህረገብ መሬት መልሶ ለማግኘት የሚደረግ ነው።
ባለፈው አርብ ሩስያ ዩክሬን የባህር ዳርቻ ላይ ቦታ በመያዝ ከባድ መሳሪያ ለማጓጓዝና ወሳኝ ቦታዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችላትን ሙከራ ማክሸፏን አስታውቃለች።
በሌላ በኩል በኬርሶን ከተማ ሩስያ በወሰደችው እርምጃ ሶስት ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን የዩክሬን ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ከዚያ ቀደም ብሎ ከትላንት በስትያ ዕሁድ ሩስያ በተቆጣጠረችው ሜሊቶፖል ከተማ ላይ በተከሰተ ፍንዳታ ቢያንስ ሶስት የሩስያ የጦር መኮንኖች መገደላቸውን የዩክሬን ወታደራዊ ስለላ ተቋም ገልጿል። ዩክሬን ግድያው የተፈጸመው በአካባቢው ባሉና የሩስያ አንቅስቃሴ በተቃወሙ ነዋሪዎች የተወሰደ የበቀል እርምጃ ነው ብላለች።
ከዩክሬን ጋር ግንኙነት ያላቸው ተዋጊዎች በርካታ በርካታ የሩስያ የጦር ባለስልጣናትና ተባባሪዎቻቸውን መኪና ላይ በተጠመደ ቦምብና ተቀጣጣይ ፈንጂዎች መግደላቸውን ይገልጻሉ።
ባለፈው ሳምንት ሚካኤል ፊሊፔንኮ የተባለ የቀድሞ የሚሊሻ ኃላፊ ሩስያ በተቆጣጠራቻት ሉሻንካ በተባለ ስፍራ የተገደለ ሲሆን ጥቃቱ በዩክሬን የተፈጸመ ነው ተብሏል።












