በአማራ ክልል ‘የሕግ ማስከበር ዘመቻ’ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ12 ሺህ በላይ መድረሱ ተገለጸ

የአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባህር ዳር
የምስሉ መግለጫ, የአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባህር ዳር
ታትሟል

የአማራ ክልል ባለፈው አንድ ወር አካሄድኩት ባለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከ12 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ።

የክልሉ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገበው ፖሊስ በሕገ ወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል ሲል የጠረጠራቸውን 12 ሺህ 400 ሰዎች ባለፈው አንድ ወር ብቻ ይዟል።

እነዚህ ተጠርጣሪዎች በፋኖ ስም የሚነግዱ እና በተለያዩ ኢ-መደበኛ ቡድኖች ተደራጅተው በግድያ፣ በዘረፋ እና በአስገድዶ መድፈር እና አሸባሪ ከተባሉ ቡድኖች ተልዕኮ ወስደው ክልሉን በማናጋት ወንጀሎች የተጠረጠሩ መሆናቸውን መገናኛ ብዙኃኑ የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽነርን ጠቅሶ ዘግቧል።

ከእነዚህ መካከል 3 ሺህ 746 የመከላከያ፣ የልዩ ኃይል እና የፖሊስ አባላት ሲሆኑ፣ ከ8 ሺህ 700 በላይ የሚሆኑት በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ግለሰቦች ናቸው ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት  ሰኔ 07/2014 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፣ በክልሉ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል 3 ሺህ 500 የሚሆኑት የከዱ የመከላከያ ሠራዊት እና ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት መሆናቸውን ጠቅሰው ነበር።

ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ባወጣው መግለጫ መንግሥት እየወሰድኩት ነው ባለው ሕግ የማስከበር እርምጃ ጋዜጠኞችና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን ገልጾ፣ ድርጊቱ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መፈፀሙን ኮንኗል።  

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾችም የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ እንዲሁም በጋዜጠኞችና በሚዲያ ባለሙያዎች ላይ የሚደርሰው ትንኮሳ እንዲቆም የጠየቁ ሲሆን  ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችም እስሩ በሕግ አግባብ እንዲከናወን ማሳሰባቸው አይዘነጋም።

ባለፈው ወር ላይ በሁለት ሳምንት ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው የታሰሩ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ቁጥር ከአስራ ስድስት በላይ ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ የተወሰኑት ካለፈው ሳምንት ወዲህ በዋስ ከእስር ተለቀዋል። ሆኖም አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ አሉ።

በአሜሪካ የአማራ ማኅበርም ዘመቻው “የዐቢይን አስተዳደር የሚቃወምን ኃይል የማጥፋት እንቅስቃሴ ነው” ሲል ተቃውሞት ነበር።

የክልሉ መገናኛ ብዙኃን - አሚኮ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጠቅሶ እንደዘገበው ተጠርጥረው በፖሊስ ከተያዙት ውስጥ ከ3 ሺህ 750 በላይ የሚሆኑት በዋስትናና በማጣራት ከእስር ተለቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ለህወሓት ሊተላለፍ ነበር ያለው ከ37 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ኬላ ላይ በተደረገ ፍተሻ መያዙን ኮሚሽኑ አክሏል። በተወሰደው እርምጃም በክልሉ ሕገ ወጥ ተኩስን ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎች መቀነሳቸውን አመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ፣ በተለያዩ የአገሪቷ ክልሎች የሕግ ማስከበር አርምጃ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአማራ ክልል በተወሰደው እርምጃ የክልሉ ሕዝብ ደስተኛ መሆኑንም ተናግረው ነበር።

ከሕግ ማስከበር ዘመቻው በፊት በክልሉ ያሉ ሁኔታዎችን በሰላም ለመፍታት ጥረት መደረጉንና አለመቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ በክልሉ የተካሄደው ሕግ የማስከበር ዘመቻም ሙሉ በሙሉ በክልሉ ልዩ ኃይል መከናወኑንም አመልክተዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት "የሕግ ማስከበር ዘመቻ" መጀመሩን ያስታወቀው ክልሉ በግለሰቦች እጅ የሚገኝ የጦር መሣሪያ ምዝገባ ሊያካሄድ መሆኑን የክልሉ የሰላምና የፀጥታ ቢሮ ማስታወቁን ተከትሎ ነበር።

በተለይም በበርካታ አካባቢዎች በስፋት በተደራጀው "ፋኖ በተባለው መደበኛ ያልሆነ ታጣቂ ቡድን ስም ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ግለሰቦችና ቡድኖች" ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቆ ነበር።

ባለፈው አንድ ወር የክልሉ መንግሥት የሚያካሂደውን ዘመቻ በመቃወም በተለያዩ የክልሉ ከተሞች በተቀሰቀሰ የተቃውሞ ላይ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል።