ታዋቂው አሜሪካዊ ዘፋኝ ሾን ኪንግስተን “ቴሌቪዥን ገዝቶ ባለመክፈሉ” ታሰረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፖሊስ ፍሎሪዳ የሚገኘው የታዋቂው ጃማይካዊ-አሜሪካዊ ዘፋኝ ሾን ኪንግስተንን መኖሪያ ቤት ከበረበረ በኋላ ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ተሰምቷል።
ፖሊስ በወቅቱ ካሊፎርኒያ የነበውን ሾን ኪንግስተን እና እናት በቁጥጥር ሥር አውሎ ወደ ጣቢያ ወስዷቸዋል።
ባፈለው የካቲት አንድ ኩባንያ ታዋቂው ዘፋኝ ግዙፍ ቴሌቪዥን እና 'ስፒከር' ገዝቶ ሙሉ ሒሳቡን አልከፈለም ሲል ወቀሳ ማሰማቱ ይታወሳል።
ኪንግስተን ደቡብ ካሊፎርኒያ ወደ ሚገኘው ፎርት ኧርዊን ፖሊስ ጣቢያ የተወሰደ ሲሆን፣ በማጭበርበር እና ስርቆት እንደተጠረጠረ ፖሊስ ይፋ አድርጓል።
ዘፋኙ ከመታሰሩ በፊት በማኅበራዊ ሚድያ ገፁ “ጠበቃዎቼ ጉዳዩን ይዘውታል” ሲል መልዕክት ለጥፎ ነበር።
የፍሎሪዳ ፖሊስ በመዝገብ ስሙ ኪሲያን አንደርሰን የተሰኘውን ዘፋኝ መኖሪያ ቤት የፈተሸው ባለፈው የካቲት በተከፈተ ክስ መሠረት ነው።
በአሜሪካ የቢቢሲው አጋር ሲቢኤስ ቴሌቪዥንን ጨምሮ ሌሎች መገናኛ ብዙኃን መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ሳለች በቁጥጥር ሥር የዋለችው የዘፋኙ እናት መሆኗን አረጋግጠዋል።
መኖሪያ ቤቱ መፈተሹን ለቢቢሲ ያረጋገጡት የፖሊስ መኮንኖች የፍተሻ እና የእስር ደብዳቤ ይዘው እንደሄዱ ተናግረዋል።
ጃኒስ ተርነር የተባለች ሴትም በማጭበርበር እና በስርቆት ወንጀል ተጠርጥራ በቁጥጥር ሥር ውላለች ይላል የፖሊስ መግለጫ።
የፖሊስ መኮንኖች ከዘፋኙ መኖሪያ ቤት ቁሳቁስ ይዘው ሲወጡ ታይተዋል።
ሾን ኪንግስተን እና በኢንስታግራም ስሟ ማማ ኪንግስተን በመባል የምትታወቀው የዘፋኙ እናት ለመገናኛ ብዙኃን ቃላቸውን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
“እኔ ደኅና ነኝ። እናቴም ደኅና ናት” ሲል ኪንግስተን ስለእሱ እና እናቱ እሥር ምላሽ ሰጥቷል። አክሎ ጠበቆቹ ጉዳዩን እየተመለከቱት እንደሆነ አሳውቋል።
ኪንግስተንን እና እናቱን የወከሉት ጠበቃ ሁለቱ ግለሰቦች ክስ እንደቀረበባቸው አረጋግጠው “ጉዳዩን በፍርድ ቤት የምንመለከተው ይሆናል። ውጤታማ መፍትሔ እንደሚገኝለት እንተማመናለን” ሲሉ ለኤፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ቢቢሲ የተመለከተው የፍርድ ቤት መዝገብ እንደሚጠቁመው ቬር ቬር ኢንተርቴይንመንት የተባለው ኩባንያ፤ ሾን ኪንግስተን “መስከረም 2023 በማኅበራዊ ሚድያ አማካይነት 223 ኢንች መጠን ያለው ቴሌቪዥን እና ስፒከር ሊገዛን ጠይቆናል” ይላል።
ኩባንያው እንደሚለው ዘፋኙ “ሐሰተኛ ማስረጃዎችን በማቅረብ” እንዲሁም ከጀስቲን ቢበር ጋር በመተባበር ማስታወቂያ እንደሚሠራላቸው በመናገር ቴሌቪዥኑን “በአነስተኛ ቀብድ” ገዝቷል።
ነገር ግን ኩባንያው ቴሌቪዥኑን ወስዶ የዘፋኙ መኖሪያ ቤት ከሰቀለ በኋላ ኪንግስተን መክፈል የሚገባውን ቀሪ ሒሳብ ባለመክፈሉ ስምምነት በመጣስ እና በማጭበርበር ከሶታል።
ቬር ቬር ኢንተርቴይንመንትን የወከሉ ጠበቃ ለአካባቢው መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት ኩባንያው ከፖሊስ ፍተሻ በኋላ ቁሳቁሱን መልሶ ለማግኘት ተስፋ አድርጓል።
“ንብረታችን እዚህ ቤት እንዳለ እናውቃለን። ፖሊስ ፍተሻውን ከጨረሰ በኋላ ባለሙያዎች ልከን ንብረታችንን ነቅለን እንወስዳለን።”
የ34 ዓመቱ ሾን ኪንግስተን ቢዩቲፉል ገርልስ፣ ፋየር በርኒንግ እንዲሁም ከጀስቲን ቢበር ጋር በተጫወተው ኢኒ ሚኒ በተሰኙ ዘፈኖቹ እውቅናን አትርፏል።












