የኢራኑን ፕሬዝዳንት ታሪካዊ የተባለ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በኬንያ ጀመሩ

የፎቶው ባለመብት, Presidential Press Unit - Kenya
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በአፍሪካ ታሪካዊ የተባለውን ጉብኝታቸውን በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ከኬንያ ጀመሩ።
ፕሬዝዳንቱ መጀመሪያ ያቀኑት ወደ ኬንያ መዲና ናይሮቢ ነው።
ናይሮቢ የሚገኘው ስቴት ሐሃውስ በተሰኘው የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ለኢራኑ ፕሬዝዳንት አቀባበል 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።
አልፎም የኢራኑ ፕሬዝዳንት የኬንያ አቻቸው በተገኙበት ወታደራዊ ትዕይንት ተካሂዷል።
ራይሲ ከኬንያው መሪ ዊሊያም ሩቶ ጋር ስለሁለትዮሽ ግንኙነት ከመከሩ በኋላ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
ሁለቱ አገራት በኢንፎርሜሽን፣ በኮሚዩኒኬሽን እና በቴክኖሎጂ፣ በዓሳ ሃብት ልማት፣ በእንስሳት ጤና እና እርባታ ዘርፎች አብረው ለመሥራት ስምምነት ደርሰዋል።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት የኬንያ ቆይታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ኡጋንዳ እና ዚምባብዌ ለማቅናት አቅደዋል።
የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን ወደ አፍሪካ መጥቶ ጉብኝት ሲያደርግ ይህ ከአሥር ዓመት በኋላ የመጀመሪያው ነው።
ፕሬዝዳንት ራይሲ ማክሰኞ ወደ ናይሮቢ ከማቅናታቸው በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከአፍሪካ አገራት ጋር ግንኙነት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጠዋል።
ራይሲ አገራቸው ከአህጉረ አፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነት በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት የተቀዛቀዘ እንደነበር አልካዱም።
በለተያዩ ዘርፎች ከአፍሪካ አገራት ጋር መሥራት ያዋጣናል እንጂ አይጎዳም የሚል ስሜት ያለው አስተያየትም ሰጥተዋል።
ኢራን ከአፍሪካ አገራት ጋር አብራ ለመሥራት ጉጉት አላትም ብለዋል።
ነገር ግን የፖለቲካ ተንታኞች ከምዕራባውያን ጋር መልካም ያልሆነ ግንኙነት ያላት የኢራንን ጉብኝት በበጎ አይመለከቱትም።
እርግጥ ነው ኢራን ከምዕራባዊያን እየደረሰባት ካለው ማዕቀብ እና ጫና አንፃር ከተቀረው የዓለም ክፍል ጋር ያላትን ግንኙነት ትሻለች።
ምዕራባውያን የኢራን አስተዳደር ቀጣናዊ ሰላም ያናውጣል፣ ሽብርተኝነትን ይደግፋል፣ ብሎም ሰብዓዊ መብት ይጥሳል ሲሉ ይወቅሳሉ።
ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿ ኢራን ባለስቲክ ሚሳዔል እና ኒውክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታ ታካሂዳለች ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጣሉ።
ፕሬዝዳንት ራይሲ በአፍሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት ምዕራባውያን በዐይነ ቁራኛ እንደሚመለከቱት እሙን ነው።












